Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ወደ ሞት እየተገፋ ያለው ዝዋይ ሐይቅ

በመልካሙ ተክሌ

የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሲሳይ መሆን ይችል የነበረው ሐረማያ ሐይቅ አብዛኛው ክፍል ደርቆ የከብቶች መሰማርያ መስክ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ ተደረገለት በተባለ የአካባቢ ጥበቃ አገገመ ሲባልም ተሰማ ፡፡ይሁንም እንጂ ውኃው በሞተር እየተሳበ ጫት እየለማበት ነው፡፡ በዚህ ድርጊት እየተደጋገመ መሔድም ሐይቁ ጨርሶ  እንዳይደርቅ ያሠጋል፡፡

የዝዋይ ሐይቅም እጣ ይኸው ይመስላል፡፡ እንዲያውም የዚህኛው እጅግ በጣም የከፋ ነው፡፡ የሐይቁ ይዞታ እንደነበር የሚያስታውቅ ዳርቻው ደርቆ አሁን በሳር የተሸፈነ መስክ እየሆነ ነው፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ገዳም ባለበት በኩል ያለው ዳርቻው አጠገብ ደግሞ የአበባ እርሻ ይገኛል፡፡ እርሻው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀምበትን ውኃ የሚወስደው ከሐይቁ ነው፡፡ ለዚህ አገልግሎት የሚውል ውኃ መሳቢያ ሞተርም ከሐይቁ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ድንጋይ ከሐይቁ ቢወረወር አበባ እርሻውጋ ለመድረስ የወንጪፍ እገዛ አያስፈልገውም፡፡ የአበባ እርሻዎች ለአበባ ምርት ኬሚካል እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ ኬሚካል በዚህ መልኩ መጠቀም ደግሞ የሐይቁን ሥነ ምሕዳር ያፋልሳል፡፡ በዚህ ቀጥታ ተጽዕኖ ከሚያርፍባቸው መካከል ዓሶች እና አዕዋፍ ይገኙበታል፡፡ በሞተር ከሚሳበው በተጨማሪ የመስኖ ልማትም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገበት የሐይቁን ጨዋማነት በማዛባት አሉታዊነቱ እንደሚያመዝን እሙን ነው፡፡

ዝዋይ ሐይቅ ካሉት ደሴቶች አንዱ የወፍ ደሴት በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ በዚህ ደሴት ላይ እጅግ በርካታ ስደተኛና ስደተኛ ያልሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ደሴቱ ዘወትር በወፍ አጥኚዎችና አድናቂዎች እንደተጨናነቀ ነው፡፡

ከአዕዋፍ ሌላ ሐይቁ በርካታ ጉማሬዎችን እና የዓሣ ዝርያዎችንም የያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያየኋቸው ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሐይቁ በዓመት 2454 ቶን ዓሣ ይመረታል፡፡ በልጅነቴ (ከሁለት ዐሠርታት በፊት) ከዝዋይ ሐይቅ 300 ኪሎሜትር ያህል በሚርቅ ቦታ ላይ የዝዋይን ዓሣ መብላቴን አስታውሳሁ፡፡ አሁንስ የዝዋይ ዓሣን ያን ያህል ሩቅ እስከሆነ ቦታ ማግኘት ይቻላልን?

ከአበባ እርሻ የከፋ ዝዋይ ሐይቅን ወደ ሞት እየገፋ ያለው ደግሞ በእኔ አስተያየት ከፍተኛ የኬሚካል ፍሳሽ ሳያጣሩ የሚለቁ ፋብሪካዎች መበራከት ነው፡፡ ይህም የሐይቁን አካባቢ እና ገባር ወንዞች በመበከል ወደ ሐይቁ የሚያመራ ነው፡፡

መቂን ጨምሮ ሁለት ዋና ዋና ወንዞች ሐይቁን ይመግቡታል- ወደ ሐይቁ ይፈስሳሉ፡፡ እንደ ቡልቡላ ያለ ወንዝ ደግሞ ከዝዋይ ሐይቅ ተነስቶ ይፈስሳል፡፡ ጥልቀት ከሌላቸው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አንዱ የሆነው ዝዋይ የተመዘገበ ስፋቱ 434 ኪሎሜትር ስኩዌር ነበር፡፡ በአንድ ጥናት መሠረት ደግሞ 1.1 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይዟል ተብሎም ነበር፡፡ ይህ እየተመናነመነ መሔዱን የዓይን እማኞች ይመሰክራሉ፡፡ ሐይቁ እየደረቀ ነው፡፡

ከዚህ ብዙም ሳይርቅ በዝዋይ (ባቱ) ከተማ የተከፈቱ መዝናኛ ስፍራዎችና ሆቴሎች በዝዋይ ሐይቅ ላይ አፍራሽ ተጽእኖዎቻቸውን እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከእንደዚህ አይነት ማዕከላት የሚወጣው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻም ሐይቁን እየገደለው ይመስለኛል፡፡ የከተማዋ ቆሻሻ አወጋገድ አለመዘመን በዚህ ላይ ሲጨመር የሐይቁን ሞት አያፋጥንም ትላላችሁ?

አሁን ሐይቁን ወደ ሞት እያቀረብነው ከሔድን ነገ ዝዋይ የሚባል ሐይቅ አይኖረንም፡፡ የሐይቅ ንጹሕ ውኃ የነበረው ቦታ ሜዳና ሸለቆ በመሆን ግፋ ቢል የግጦሽ ሳር እንጂ ዓሣ አያቀርብልንም፡፡ እንደልጅነት ጊዜዬ በመቶዎች ኪሎሜትሮች ተጓጉዞ ባይበላም አሁን ላይ ውስን የዓሣ ምርት አለው፡፡

ዓሣውን እየተመገቡ የሚኖሩ በርካታ የወፍ ዝርያዎችም አሉት፡፡ ይሁንም እንጂ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለአበባ የሚውለው ኬሚካል የአዕዋፍ ቁጥርንም እንደሚያመናን በዳርዊን ፕሮጀክት የተጠና ጥናት ያሳያል፡፡

ዝዋይ ከሌለ ቡልቡላም ሟች ነው፡፡ ዝዋይ ከሞተ መቂም ይሞታል፡፡ የሐይቁን ውኃ አረም እየዋጠው፣ ኬሚካል እየበከለው፣ ሰው እየገደለው ከሔደ የዝዋይ ሐይቅነት በታሪክ ማኅደር ብቻ ያለ ይሆናል፡፡ ሐይቅ ሲሞት ወንዝ ይሞታል፡፡ ዓሣ ይሞታል፡፡ ወፍ ይሞታል፡፡ በመጨረሻ ሰውም ይሞታል፡፡

ስለዚህ ሐይቁን ተንከባክቦ በሕይወት ማቆየት የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የዞኑ፣ የወረዳው፣ የግለሰቦች ብቻ አይደለም፡፡ የሁሉም ኃላፊነት ነው አንጂ፡፡ ዝዋይን ከሞት መታደግ ከተፈለገ ‹‹የሚመለከተው አካል›› ተብሎ ለአንድ ወይ ለሁለት ተቋማት ብቻ የሚተውም አይሆንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles