Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት ከመንግሥት እጅ መውጣቱ የሚያስከትለው ሥጋት

በደረጀ ሽመልስ

መንግሥት በቅርቡ በብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት ውስጥ ያለውን ወደ 31 በመቶ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻን ለጃፓን ዓለም አቀፍ የትምባሆ ድርጅት (ጄቲአይ) በመሸጥ ከትምባሆ ንግድ ውስጥ ለመውጣት የወሰደው ውሳኔ በመልካም ጎን የሚታይ ነው፡፡ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰዎች ሕይወትን እየቀጠፈ ያለውን የትምባሆ ምርት መንግሥት ለራሱ ዜጎች እንዳያመርትና እንዳይሸጥ የሞራል ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ውሳኔ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2014 በአዋጅ ያፀደቀችውን የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለማስፈጸምም ይረዳል፡፡ በተጨማሪ መንግሥት የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች በሚዘጋጁበት እንዲሁም በሚፈጸሙበት ወቅት ከትምባሆ ኢንዱስትሪውና ከኢንዱስትሪው የንግድ ጥቅሞች የመጠበቅና የመከላከል ግዴታው እንዳለበት የሚደነግገውን የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ስምምነት አንቀጽ 5.3 በአግባቡ ለመፈጸም ይረዳዋል፡፡

በብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት አስተዳደር ውስጥ የመንግሥት ተወካዮችና ድርሻ ለረዥም ጊዜ መኖሩ  ያለምንም ጥርጥር ድርጅቱ አሳሳች የሆነ የገበያና የሽያጭ ሥልቶችን በመጠቀም ትርፍ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግ ድርጅት እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ግን እጅግ የተለየ ነው፡፡ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት የውስጥ አሠራር ከመንግሥት ዓይንና ጆሮ ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ ዓለም አቀፍ ልምድ ላለውና ግዙፍ ለሆነው ለጀቲአይ መሸጡ ኅብረተሰብ ጤና በርካታ ተግዳሮቶችን የሚያስከትል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይ ዕድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳጊዎች ከትምባሆ ምርት አደገኛ ሱስ አስያዥነት፣ በትምባሆ አማካይነት ከሚመጣ ሞት፣ በሽታና ትምባሆ ከሚያጣቸው ሌሎች ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ችግሮች እንዲጠበቁ የማድረግ በዋነኛነት የሕግ አመኔታ የተጣለበት የፌዴራል መንግሥት አካል ለሆነው ለኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

ጄቲኤይ 70 በመቶ የሚሆነውን የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት የሞኖፖል የባለቤትነት ድርሻ የገዛ ሲሆን፣ በቂ ቁጥጥር ካልተደረገ ድርጅቱ በተሰጠው የሞኖፖል መብት በጥቂት ዓመታት ውስጥ መዋለ ንዋዩን መልሶ ለማግኘት ሲል ተዘዋዋሪ ማስታወቂያን ጨምሮ ተቀባይነት የሌላቸውን የገበያና የሽያጭ ሥልቶችን ሊጠቀም ይችላል ብሎ ማሰብ ስህተት አይሆንም፡፡ ከዚህ ጋር በሚያያዝ የሌሎች አገሮች መንግሥታት የትምባሆ ሞኖፖልን ለግል ባለሀብቶች ካዘዋወሩ በኋላ ያስከተለውን ኢኮኖሚያና የኅብረተሰብ ጤና ተፅዕኖ የተገመገመበት ጥናት እ.ኤ.አ. በ2005 ላይ በዓለም ባንክ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት የተለያዩ አገሮች የትምባሆ ሞኖፖል ለግል ባለሀብቶች ከተዘዋወሩ በኋላ ስፋት ያለውና ውጤታማ የሆነ የትምባሆ ምርቶች ማስተዋወቂያና የሽያጭ ሥልቶች እንደታዩና እነዚህ ማስተዋወቂያና የሽያጭ ሥልቶች በእጅጉ ወጣቶችንና ሴቶችን ዒላማ ያደረጉ እንደነበርና በእነዚህ አገሮች የትምባሆ አጫሾች ቁጥር እንደጨመረ ያብራራል፡፡   

ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ አትራፊ በሆነ የግል ባለሀብቶች መያዙም ወደፊት በትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች አወጣጥ፣ የማፅደቅ ሒደት እንዲሁም አፈጻጸም ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የማሳደር ሙከራ የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው የትምባሆ ሕገወጥ ንግድ ምጣኔ ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሳይ (የተጋነነ ሊሆን በሚችል ሁኔታ) እና ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግ ሕጉ ውጤታማ እንደማይሆን በተለያዩ ሚዲያ ሲነገር ነበር፡፡ በቂ የሆነ ቁጥጥር እንዳይደረግና የትምባሆ ዋጋ እንዳይጨምር ለማድረግ ከፍተኛ ምጣኔ ያለው ሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ስለመኖሩ የመከራከሪያ ነጥብ መፍጠር የትምባሆ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ሥልት መሆኑን ዓለም አቀፍ ትምባሆ ቁጥጥር ልምዶች ያሳያሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ሥልት የሕግና ፖሊሲ አውጪዎችን አስተሳሰብ በማዛባት ጠንካራ የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲ እንዳይወጣ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ የተለያዩ አገሮች ልምዶች ያሳያሉ፡፡

ጄቲአይ የመንግሥትን የተቀሩ አክሲዮኖች ከብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ለመግዛት መደራደር ከጀመረበት ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. በፊት እኔ በግል የማውቀው ምንም ዓይነት የአቻ ግምገማ የተደረገበት ጥናት፤ ገለልተኛ የሆነ ሪፖርት ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ምጣኔ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች በወጣው መጠን መሆን  የሚያሳይ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አልነበረም፡፡ ጄቲአይ 31 በመቶ የሚደርሰውን የመንግሥታት ድርሻ ከሁለት ሳምንት በፊት ከገዛ በኋላ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌቱ ዓለማየሁ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ምጣኔ 44 በመቶ እንደሆነና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ደግሞ 90 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ፎርቹን ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ ወደ 50 በመቶ የሚጠጋው የኢትዮጵያ ገበያ በሕገወጥ ትምባሆ የተያዘ እንደሆነ በማብራራት መንግሥት የኅብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ የሚያወጣው ጠንካራ ሕግ ስኬታማ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ሰዎች በግላቸው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ለማሳመን የሚጠቀሙበትን ሌላ መረጃም ወይም አኃዝ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ 

የትምባሆ ኢንዱስትሪ ተወካዮች እጅግ ከፍተኛ ነው ብለው የሚያስተጋቡት የሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ምጣኔ ከመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ከአገር ደኅንነትና የአሸባሪ ቡድኖች ተጠቃሚነት ጋር በማያያዝ የሕግና ፖሊሲ አውጪዎችን ማስደንገጥና ጉዳዩን ተራና ለጤና እጅጉን ጎጅ ከሆነው የትምባሆ ምርት ያለፈ እንደሆነ በማስመሰል ጉዳዩን አጉልቶ ለማውጣት የሚደረገው ሙከራ የኢንዱስትሪው የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ ተመሳሳይ የሆነ የክርክር ነጥቦችም ከላይ በጠቀስኳቸው የሪፖርተርና አዲስ ፎርቹን ዜናዎች ላይ በትምባሆ ኢንዱስትሪ ተወካዮች ተንፀባርቀዋል፡፡ ለአንዳንድ ሰዎች የትምባሆ ኢንዱስትሪው የሚያስተጋባው ይህ የተጋነነ ትርክት ኃላፊነት ከሚሰማው ድርጅት የመጣ እንደሆነና የሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ምጣኔው 44 በመቶ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች 90 በመቶ ነው የሚባለው የጥናት ግኝት በቀላሉ ሊረጋገጥ የሚችልና ተቀባይነት ያለው የጥናት መንገድ ተከትሎ የተሠራ ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በሕዝብና የፖለቲካ አስተያየት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር በዓለም ላይ ያሉ በርካታ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ከላይ የተገለጹትን ሥልቶች ይጠቀማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ሥልት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ትምባሆ ከሚያመጣው ሞትና ብዛት ያላቸው የካንሰር ዓይነቶችን ጨምሮ ሌሎች ገዳይ በሽታዎች ለማትረፍ የታቀደን የትምባሆ ቁጥጥር ሕግ ቢቻል ለማስቀልበስ ካልተቻለ ደግሞ ለማዳከም የታቀደ ስትራቴጂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገሮች  በተደጋጋሚ ሁኔታ እንዳየነው ኢንዱስትሪው በትምባሆ ላይ ሊደረግ የታሰበን የታክስ ጭማሪ ለማስቀረት፣ በትምባሆ ምርት ላይ ሥዕላዊ የጤና መግለጫ እንዳይደረግበት ለማድረግና በዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ሥር የተካተቱ የኅብረተሰብ ጤናን የሚያስጠብቁ  የትምባሆ ቁጥጥር ድንጋጌዎች በበቂ ሁኔታ እንዳይተገበሩ ለማድረግ የሕገወጥ ንግድ ምጣኔን በእጅጉ በማጋነን እንደሚያቀርቡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ ከትንባሆ ኢንዱስትሪ ወይም በኢንዱስትሪው የገንዘብ ድጋፍ የሚሠሩ ጥናቶች አስተማማኝነት በከፍተኛ ጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ በተለይም ፖሊሲና ሕግን በሚያወጣው የመንግሥት አካል በኩል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢንዱስትሪው ሕገወጥ በሆነ መልኩ ገበያ ውስጥ የሚገኘው የትምባሆ ምርት 50 በመቶ እንደሚጠጋና ጠንካራ የትንባሆ ቁጥጥር ዕርምጃዎች ሕገወጥ ነጋዴዎችን ብቻ እንደሚጠቅም በተለያየ መንገድ መልዕክት እያስተላለፈ መሆኑን ከተለያዩ የሚድያ ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡ በመጀመርያ ደረጀ መረጃው ሳይንሳዊ ሒደትን ተከትሎ የተሠራና በአግባቡ የታተመ ቢሆን የመረጃውን ተዓማኒነት ለመመርመር፣ ምን ዓይነት ሳይንሳዊ የጥናት መንገድ እንደተጠቀመ እንዲሁም የመረጃውን ምንጭና ጥራት ለማወቅ የሚረዱ ጉዳዮችን ለማየት ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ አልሆነም፡፡ ጥናቱ እነዚህንና ሌሎች መሠረታዊ የጥናት ተዓማኒነት መሥፈርቶችን የሚያሟላ ነው ብዬም አላምንም፡፡ በተጨማሪ የትምባሆ ኢንዱስትሪው በሌሎች አገሮች እንደተለመደው ሥልታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ፈቃደኛ በሆነ የአማካሪ ድርጅት፣ የጥናት ቡድን ወይም በራሱ አጥኝዎች ጥናትን ሊያካሂድ ስለሚችል በዚህ መንገድ የሚገኝ ተያያዥ አኃዝ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ እንዲሁም የጥናት ውጤት ማረጋገጭ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡

ለምሳሌ እንግሊዝ አገር በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ባዝ አማካይነት የተደረገ የገለልተኛ አካል ግምገማና  እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2014 በብሪቲሽ የሚዲካል ጆርናል ላይ በወጣው ጥናት ላይ በርካታ ዓለም አቀፍ የትንባሆ ድርጅቶች ሕገወጥ የሆነ የትምባሆ ንግድን ሥጋት በእጅጉ በማጋነን የሕግ አውጭዎችና የመንግሥት ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በትንባሆ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄዱ ጥናቶችም ከፍተኛ የሆነ ክፍተትና ጥቅም ግጭት እንደተገኘባቸው ያመለክታል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት እ.ኤ.አ. በ2017 ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገውን የእንግሊዝ የትምባሆ ምርት አስተሻሸግ ደረጃን ለመወሰን የወጣ ሕግን ለማስቀረት የታቀደ ነበር፡፡ እነዚህ ዓይነት መረጃዎች በአብዛኛው ተዓማኒነት የሌላቸውና ወደ ተሳሳተ የፖሊሲ ውሳኔ የሚመሩ ሐተታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪ በ2016ቱ የኢትዮጵያ አዋቂዎች የግሎባል ትምባሆ ጥናት መሠረት ትልቁን ገበያ ድርሻ የያዘው የኒያላ ሲጋራ (ከ87 በመቶው) ሲሆን፣ የፓኬቱ ነጠላ ዋጋም ከ16 እስከ 18 ብር ነው፡፡ ይህ ዋጋ በዓለም ላይ በጣም ርካሽ ዋጋ ካላቸው አገሮች ውስጥ የሚያስመድበን ሲሆን፣ አገራችን ያላት የትምባሆ ተጠቃሚም አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ አነስተኛ ስለሆነ የሕገወጥ ትምባሆ ንግድ ኢንዱስትሪው በሚለው መጠን እጅግ ከፍተኛ አኃዝ ነው ለማለት የሚያዳግት ነው፡፡  

በሌላ  በኩል ኢንዱስትሪው የሚያቀርበው ሌላ የመከራከሪያ ነጥብ ጠንካራ የሆነ የትምባሆ ቁጥጥር ሕግ የታሰበውን ያክል ስኬታማ እንደማያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መረጃዎች እንዲሚያሳዩት የትምባሆ የግብር ክፍያ መጨመር የትምባሆ ፍጆታን በእጅጉ እንዲቀንስና የመንግሥትን የግብር ገቢ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት ይህ በቀጥታ የሕገወጥ የትምባሆ ንግድ እንዲጨምር አያደርግም፡፡ የአገሪቱ የትምባሆ የግብር ክፍያ ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይልቁንም የሕገወጥ የትምባሆ ንግድ የሚጨምረው በይበልጥ ከድንበር አስተዳዳርና ከሕግ አስፈጻሚዎች አቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት አሠርታት ብቻ ከመቶ የሚበልጡ አገሮች በትምባሆ ምርት ላይ ግብር ለመጨመር ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን የወሰዱት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ሕገወጥ የሆነ ትምባሆ ንግድን በተመለከተ ተዓማኒነት ያለው መረጃን መሠረት ያደረገ የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎችን የመቀነስ ዕርምጃ ጨምሮ መንግሥት የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ፕሮቶኮል መፈረሙ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

በተጨማሪ በዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች የትምባሆ ቁጥጥር ዕርምጃዎችን ሁሉም ሳይንሳዊ በሆኑ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የትምባሆ ምርቶችን አስተሻሸግ በሥዕል የተደገፈ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲኖረው ማድረግ የትንባሆ አጫሽ ቁጥርን ለመቀነስና በመንግሥት ላይ ምንም ዓይነት ወጪ ሳያስከትል የኅብረተሰብ ጤና ማስጠንቀቂያንና ትምህርትን ለመስጠት የሚያስችሉ እጅግ ውጤታማ መንገዶች ናቸው፡ በኦክቶበር 2016 የካናዳ ካንሰር ማኅበር ባወጣው ሪፖርት መሠረት 105 አገሮች ይህንን ዕርምጃ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 15 የአፍሪካ አገሮችም በሥዕል የተደገፈ የጤና ማስጠንቀቂያን የሚያስገድዱ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡

መንግሥት በሁሉም ደረጃ በትምባሆ ኢንዱስትሪ የሚወጡ ሥልቶችን በቂ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ በኢንዱስትሪው አማካይነት ሊመጡ የሚችሉ የማታለል ተግባርን ለማስወገድ የሚያስችል መንገድ በመንግሥት እጅ አለ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 አገራችን የተቀበለችውን የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ማድረግ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው  ቴድሮስ  አድሃኖም (ዶ/ር) እና  የኡራጓይ ፕሬዚዳንት ታቤር ቫስኩዊዝ የትምባሆ ኢንዱስትሪን አሠራር በሚመለከት በቅርቡ በጋራ ባሳተሙት ጽሑፍ ላይ እንዳሉት ኢንዱስትሪው ባለፉት ጊዜያት የሚታመን አልነበረም፡፡ ወደፊትም ትክክለኛ ሥራ ይሠራል ተብሎ አመኔታ የሚጣልበት ተቋም አይደለም በማለት ጥሩ በሆነ ሁኔታ ገልጸውታል፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው የጤና ሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles