Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለ13 ዓመታት የአንበሳ አውቶቡስን አንበሳ የሣለችው  አርቲስት

ለ13 ዓመታት የአንበሳ አውቶቡስን አንበሳ የሣለችው  አርቲስት

ቀን:

‹‹ዘመን›› የተሰኘው የዓይናለም ገብረማርያም የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ የሠዓሊቷን የ40 ዓመታት ሥነ ጥበባዊ ጉዞ ያስቃኛል፡፡ በአዲስ አበባ ሙዚየም ከጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለ15 ቀናት ይታያል፡፡ ሠዓሊቷ እንደምትናገረው፣ በ1970ዎቹና 80ዎቹ በ90ዎቹም የሠራቻቸው ሥራዎች በምን ሒደት እንዳለፉ የምታሳይበት ዐውደ ርዕይ ነው፡፡ ‹‹የ40 ዓመታት ጉዞዬን ሕዝቡ እንዲያይ እፈልጋለሁ፡፡ በየወቅቱ ያለው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ማሳያም ነው፤›› ትላለች፡፡

ሥራዎቿ የየዘመኑ ገጽታ ነፀብራቅ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ የደርግን ወቅት  ከሚያሳዩ ሥራዎቿ ‹‹ወዛደር››ን ትጠቅሳለች፡፡ የአንድ ወዛደር ምስለ አካል (ፖርትሬት) ሲሆን፣ ቁጭት፣ ብሶትና ተስፋ መቁረጥ ከፊቱ ይነበባል፡፡ ቀድሞ፣ በተፈጥሮ መንፈስን ለማደስ ከከተማ ብዙ መራቅ አያስፈልግም ነበር፡፡ አሁን ግን የከተሞች መስፋፋት ተፈጥሮን ከከተማ አርቋል፡፡ ይኼ ወቅታዊ ሁኔታም በሥራዎቿ ይንፀባረቃል፡፡

‹‹ተማሪ ሳለሁ የምታወቀው መልክዓ ምድር በመሥራት ነበር፡፡ አሁንም ተፈጥሯዊ ሥዕሎች እወዳለሁ፤›› ትላለች፡፡ በሥራዎቿ የሴቶችን ሕይወትም ታሳያለች፡፡ ከቤት ውስጥ የሥራ ኃላፊነት ጀምሮ በርካታ ጫና ያለባቸው ሴቶችን የዕለት ከዕለት ሕይወት በሸራዋ ታሰፍራለች፡፡ ‹‹የሴቶችን ጥንካሬ ማሳየት እፈልጋለሁ፤›› ትላለች፡፡ የሥነ ጥበቡ ዓለም ሴቶች በብዛት ስለ ሴቶች ይሥላሉ የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ መሰንዘሩን ገልጻ ‹‹የምናውቀውን ዕውነት እናሳያለን፤›› በማለት ታስረዳለች፡፡

- Advertisement -

ስለ ብርቱ ሴቶች በሥነ ጥበብ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የጥበብ ውጤቶች ሲወሳ ትደሰታለች፡፡ አሁን ካለውም በላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ በጉልህ ሊነገርላቸው እንደሚገባም ትገልጻለች፡፡ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩና በከፍተኛ ጫና ሥር ያሉ ሴቶችን ሕይወት በሥዕል ታሳያለች፡፡ ‹‹በዘመናዊ መንገድ ከምንኖረው ሴቶች በበለጠ ከከተማ ውጪ ያለው ኑሮ ይማርከኛል፤›› ትላለች፡፡ በጥቅጥቅ ደን እንጨት ለቅማና ጀርባዋ እስኪጎብጥ ተሸክማ ለዕለት ጉርስ ደፋ ቀና የምትል ሴት ከሥዕሎቿ በአንዱ ይታያል፡፡

በሪያሊስቲክ (እውናዊ) አሣሣል ዘዬ የምትታወቀው ዓይናለም፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ሴቶች ያለው አመለካከት እምብዛም ባይለወጥም ‹‹ጭላንጭል አለ›› ትላለች፡፡ ሥራዎቿን የሚመለከቱ ሰዎች፣ ከመጎብኘት ባሻገር ማስተላለፍ የፈለገችውን መልዕክት እንዲገነዘቡ ትጠብቃለች፡፡ ‹‹ወንዶች፣ በሴቶች ላይ ያለውን ጫና ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ ሆኖም ሥነ ጥበብ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ያነሳሳል፤›› ትላለች፡፡

ለ13 ዓመታት የአንበሳ አውቶቡስን አንበሳ የሣለችው  አርቲስት

ሠዓሊቷ እንደምትለው፣ በሴትነቷ የደረሰባት ማኅበረሰባዊ ጫና በሁለት ሴት ልጆቿ እንዳይደገም ለማድረግ እንደሞከረችው ሁሉ፣ ወደፊት የሚመጣው ትውልድም ከአሁኑ በተሻለ ንቁ ይሆናል፡፡ የሠዓሊያት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ስትሆን፣ ማኅበሩ ሴት ሠዓሊያንን ወደ መድረክ ያመጣል ትላለች፡፡ ‹‹ሥራዎቻችንን ስናሳይ፣ በየቤታቸው ያሉ ሴቶችን ይኮረኩራል፡፡ በጓዳ ያሉት ሠዓሊዎችም ይወጣሉ፤›› ስትል ተስፋዋን ትገልጻለች፡፡

‹‹ጥበብ ለሴት ቅርብ ናት፤›› በማለት ሴቶች በዘወትር ሕይወታቸው የሚያከናውኑትን እንቅስቃሴ ትገልጻለች፡፡ ስፌት፣ ጥልፍና ሌሎችም የዕደ ጥበብ ውጤቶችን የሚሠሩ ቀደምት እናቶችና አያቶች መደበኛ ትምህርት አለመቅሰማቸው ዓይነ ግቡ ጥበባዊ ውጤቶች ከማበርከት አልገደባቸውም፡፡

እንደ ዓይናለም መልክዓ ምድርን መነሻ ለሚያደርጉ ሠዓሊዎች አዲስ አበባ ምቹ አይደለችም፡፡ ተፈጥሯዊ አካባቢዎች እየወደሙ በሰው ሠራሽ ቁሳቁስ እየተተኩ ይገኛሉ፡፡ ለአርቲስቶችና ለተቀረው ሕዝብም መንፈስ የሚያድስ አረንጓዴያማ አካባቢ ማግኘት ህልም እየሆነም መጥቷል፡፡ ‹‹ሁኔታው አዕምሮ ያስጨንቃል፡፡ ሁሌ አንድ ነገር ማየት ያሰለቻል፡፡ የግንቦቹ ቀለሞች እንኳን ልዩነት የላቸውም፣›› ትላለች፡፡

በካሜራዋ ቀርፃ ማስቀረት የምትፈልገው ተፈጥሯዊ ፎቶ ነው፡፡ ቀለምን ከሸራ ለማገናኝት የሚያነሳሳትም ተፈጥሮ ነው፡፡ ‹‹አረንጓዴ ነገር አዕምሮ ያሳርፋል፡፡ ለጤና አስፈላጊም ነው፡፡ አሁን መናፈሻዎች እየተነሱ ግንብ እየተሠራባቸው ነው፤›› ስትል ነባራዊውን ሁኔታ ታብራራለች፡፡ ‹‹አረንጓዴ ነገር ማጣት በአስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ራቅ ተደርጎ እንዳይታሰብ ያግዳል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ልጆቻችን አረንጓዴ ነገር ምንድነው? ብለው እንዳይጠይቁ እሠጋለሁ፤›› ትላለች፡፡

ሠዓሊቷ ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከተመረቀች በኋላ፣ ከ1970ዎቹ ከሦስት ሠዓሊዎች ጋር ያደረገችውን ዐውደ ርዕይ ዛሬም ታስታውሳለች፡፡ ዐውደ ርዕዩ በእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መከፈቱም ያኮራታል፡፡ ሴት ሠዓሊያንን ያጎሉ ዐውደ ርዕዮች ተካፋይ በመሆኗም ደስተኛ ናት፡፡ ‹‹የሴቷ አሻራ በሥነ ጥበብ›› እና ‹‹ሴትነት በሥነ ሥዕል ውስጥ›› ከተሳተፈችባቸው ዐውደ ርዕዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ በሴኔጋልና በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ መካከል ትስስር ለመፍጠር በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይም ሥራዎቿን አቅርባለች፡፡

‹‹ሥነ ጥበብ ዝም ብሎ የሚጮህ ቅርስ ነው፤›› ትላለች፡፡ ሥነ ጥበብ ግዑዝ ቢሆንም፣ የሚያስተላልፈው መልዕክት ህያው ያደርገዋል፡፡ የየዘመኑ ገጽታ መስታወትም ነው፡፡ ‹‹ጥንት አያቶቻችን በዋሻ ውስጥ የሣሉትን ሥዕል እንደምናደንቀው የኛ ሥራም ለወደፊቱ ትውልድ ቅርስ ነው፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡ ስለዚህም የሥነ ጥበብ ቅርስ መጠበቅ እንዳለበት ትናገራለች፡፡

በሥነ ጥበቡ የሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢጨምርም ዛሬም በኅብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ክፍተት አለ፡፡ ‹‹ሴቶች ሥነ ጥበብ እንዳይማሩ ጫና በሚደረግባቸው ወቅት ሰብረው የወጡ እንደ ደስታ ሐጎስ ያሉ ሠዓሊያን እኛን አፍርተዋል፡፡ እኛም ተከታዮች ማፍራት አለብን፤›› ትላለች፡፡ የሥነ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ሴቶች የሚወገዙበት ሳይሆን የሚበረታቱበት አገር ለመፍጠር መረባረብ እንደሚያሻም ታክላለች፡፡ ሙያተኞችና መገናኛ ብዙኃን ስለ ሥነ ጥበብ ኅብረተሰቡን በማስተማር እንዲገፉበትም ታሳስባለች፡፡ ‹‹ቤተሰብ ልጆቹን ሥነ ጥበብ ተማሩ ብሎ የሚገፋፋበት ጊዜ ላይ እንደምንደርስ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ትላለች፡፡

በእርግጥ በዘርፉ መፈታት ያለባቸው ችግሮች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው የግብዓት  ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ትኩረት ቢሰጠው ወይም አንድ ባለሀብት ቢነሳ የሚፈታ ችግር ነው፤›› ስትል ዓይናለም ትገልጻለች፡፡ ሥነ ጥበብ እንዲስፋፋ ከተፈለገ፣ በቋሚነት ግብዓት የሚያቀርቡ ተቋሞች መኖር አለባቸው፡፡ ግብዓቱ ለሽያጭ የሚቀርብበት ዋጋም ፍትሐዊ መሆን ይገባዋል፡፡

የ61 ዓመቷ ሠዓሊት ዓይናለም ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ነው፡፡ በልጅነቷ፣ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የሰፈሯ ወንዶች አበባ እንድትሥልላቸው ተራ ይይዛሉ፡፡ በወቅቱ አበባውን አሳምሮ ከመሣል በዘለለ ሕይወቷን በሥነ ጥበብ እንደምታሳልፍ አላሰበችም፡፡ ተማሪ ሳለች የፊዚክስና ባዮሎጂ ሳይንሳዊ ቁሳቁሶችን ለክፍሏ ተማሪዎች በመሣል ትታወቃለች፡፡ ‹‹በየቀኑ የተማሪ ደብተር ሰብስቤ ቤት እወስድና ቴስት ቲዩብ ስሥልላቸው አድራለሁ፤›› ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች፡፡

በክረምት እጅጋየሁ ተስፋዬ ከምትባልና ዛሬ እንደሷው ሠዓሊት ከሆነች ጓደኛዋ ጋር የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት በተባለ ተቋም ነፃ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ አንድ ክረምት በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ለመግባት ተስማሙ፡፡ ሥልጠና ወስደው ሲፈተኑ ጥሩ ውጤት ሲያመጡ በትምህርት ቤቱ እንዲቀጥሉ ተጠየቀ፡፡ ያለምንም ማንገራገርም ገፉበት፡፡

ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መግባቷን ያወቁት አባቷ በሁኔታው ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ትምህርቷን እንድታቋርጥ በተደጋጋሚ ቢነግሯትም አልተቀበለችም፡፡ በወቅቱ ‹‹የሴቶች ሥራ›› የሚባለው ነርስነት በመሆኑ ቤተሰቦቿም ነርስ እንደትሆን ይፈልጉ ነበር፡፡ ከአባቷ ጋር የተፈጠረው መቃቃር ከወራት አላለፈም፡፡ እሷም የአምስት ዓመቱን ትምህርት ጨረሰች፡፡

‹‹ከአምስት ዓመት ትምህርት በኋላ በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ጋሞጎፋ የምትገኝ ገረሴ የምትባል ቦታ ዘመትኩ፤›› ትላለች፡፡ በአንድ ዓመት ቆይታዋ ከቤተሰቦቿ ጋር በወር አንድ ጊዜ ደብዳቤ ከመጻጻፍ ባለፈ ከማንም አትገናኝም ነበር፡፡ ‹‹በየወሩ ደመወዝ የሚከፍል መኪና ደብዳቤ ይዞ ስለሚመጣ የመኪናውን ድምፅ ስንሰማ ልዩ ደስታ ይሰማን ነበር፤›› ስትል ታስታውሳለች፡፡

በዘማቾችና በፖሊሶች መካከል አለመግባት ተፈጥሮ ወደ አርባ ምንጭ በእግራቸው ለመሸሽ ተገደዱ፡፡ ‹‹መኪና ተከራይተን ‹ፋኖ ተሰማራን› እየዘፈንን ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፤›› ትላለች፡፡ ችግሩ ከተፈታ በኋላ ዘማቾቹ ወደ ገረሴ ተመልሰው ለተጨማሪ አንድ ዓመት አስተማሩ፡፡ በማስከተል ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቃ ደብረዘይት መምህርት ሆነች፡፡

በወቅቱ ሥነ ጥበብ ካስተማረቻቸው መካከል በቀለ መኰንን (ረዳት ፕሮፌሰር) እና ጌታ መኰንን ይገኙበታል፡፡ ‹‹ዘመን›› የተሰኘውን ዓውደ ርዕይ በእነዚህ ሠዓሊያን ማስከፈት እንደምትፈልግም ትናገራለች፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰች በኋላ ሕዝብ ማመላለሻ መሥሪያ ቤት ገባች፡፡ ለ13 ዓመታት ያህል በአንበሳ አውቶቡስ ላይ ያለውን አንበሳ የሣለችውም እሷ ናት፡፡

‹‹በየጊዜው አዳዲስ መኪና ሲመጣ አንበሳውን በግራና በቀኝ በኩል እሥል ነበር፤›› ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች፡፡ አዳዲስ መኪና ሲመጣ ወይም የአንበሳው ሥዕል በተለያየ ምክንያት ሲፋቅ ትሥላለች፡፡ ‹‹ከተማ ውስጥ ባለው አውቶቡስ የሚታዩት የኔ የአንበሳ ሥዕሎች ናቸው፡፡ አንበሳው ግርማ ሞገስ ስላለው ደስ ይለኛል፤›› ትላለች፡፡

አሁን ድርጀቱ የአንበሳውን ሥዕል ከቻይና ስቲከር አሠርቶ እንደሚያስመጣ ትናገራለች፡፡ ‹‹በአገሪቱ ሠዓሊ ሳይጠፋ እንደዚህ በመደረጉ እናደዳለሁ፤›› ስትልም ታስረዳለች፡፡ አንበሳ የአገሪቱ ኩራት የሆነ እንስሳ ሆኖ ሳለ፤ በአውቶቡሱ ላይ ከአንገቱ በታች ተቆርጦና ከአሽከርካሪው በተቃራኒው አቅጣጫ ተለጥፎ ሲታይም ለምን? ብላ መጠየቋ አልቀረም፡፡

‹‹አንበሳ በሰንደቅ ዓለማችን ላይ እንዳልተንጎማለለና አንበሶቹ ሞላና መኩሪያ ኤርፖርት ሰው እንዳልተቀበሉ አንገቱ የተቆረጠ አንበሳ ማየት ያናድዳል፤›› ትላለች፡፡ ሠዓሊቷ በአንበሳ አውቶቡስ ከመሣል በተጨማሪ በጫማ ሶል ገበር (ራበር) የተለያየ ቅርፅ በማውጣትና ቀለም በመንከር ታትማለች፡፡ በጨርቅ የምታትማቸውን ቅርፆች ለገበያም ታቀርብ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ዶሮ እያረባች ሥጋውንና እንቁላል ትሽጥ ነበር፡፡

ላለፉት 15 ዓመታት ሙሉ ጊዜዋን በቤቷ በሚገኝ ስቱዲዮ በመሥራት አሳልፋለች፡፡ የቤተሰብ ኃላፊነት በሠዓሊነት ላይ ሲጨመር ቢከብድም፣ በጥንካሬ እየተወጣችው መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ‹‹ሥነ ጥበብን እየወደቅኩም እየተነሳሁም እመለስበታለሁ፤›› ትላለች፡፡ የሕይወቷን ውጣ ውረዶች የምትገልጽበትና ዘወትር እንደ አዲስ ሰው የምትታደስበት መሆኑንም ታክላለች፡፡ አሁን የሁለት ሴት ልጆች እናትና የአምስት ልጆች አያት ስትሆን፣ ‹‹ሥነ ጥበብ ሕይወቴ ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍዬበታለሁ፡፡ በውስጤ ስላለ ልርቀው አለችልም፤›› በማለት ሙያዋን ትገልጻለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...