Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በስድስት የተለያዩ መጠለያ ካምፖችና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሰላማዊ ሠልፍ ባካሄዱበት ወቅት

ትኩስ ፅሁፎች

ራሴን አጥቼ

ራሴን አጥቼ

ፍለጋ ወጥቼ

ሰው መሀል ገብቼ፣…

የሰው ጫካ ውጦኝ

የሰው አረግ ጠልፎኝ

የሰው ዳገት ዳግቶኝ

የሰው ድጥ አድጦኝ

ራሴን አዙሮ፡-

ከሰው ጉድባ ጣለኝ፡፡

ከዚያ የሰው ጉድባ

ድሄ ተነስቼ

ዳገቱን ቧጥጬ

አፋፉን ወጥቼ

በሰው ሽምጥ አጥር

በቀጋው ደማቼ

በሰው በተቦካ

የሰው ማጥ ጨቅይቼ

ተመልሼ ገባሁ፡-

ፍለጋ የወጣ ራሴን አጥቼ፡፡

  • ጌትነት እንየው ‹‹እውቀትን ፍለጋ›› (2004)

* * *

አነጋገር የቀየረው ቀዶ ጥገና

የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሊሳ አላሚያ ተወልዳ ያደገችው አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ ሲሆን፣ በቅርቡ አገጯ ላይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጐላታል፡፡ ቀዶ ጥገናው ሲጠናቀቅ ግን እሷና ቤተሰቧ እንዲሁም ሐኪሞቹ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ የቴክሳስ ተወላጆች የሚታወቁበትና ሊሳም ለዓመታት ትጠቀመው የነበረችው የአነጋገር ዘዬ (አክሰንት) ተቀይሮ ንግግሯ የእንግሊዛዊ ሆኗል፡፡ የአሜሪካው ስካይ ኒውስ እንደዘገበው፣ በዓለም ላይ ባለፉት አሥርታት ወደ መቶ ሰዎች ከቀዶ ጥገና በኋላ ይህ ዓይነቱ የንግግር ዘይቤ ለውጥ ገጥሟቸዋል፡፡ ፎሬይን አክሰንት ሲንድረም (የሌላ ሀገር ንግግር ዘዬ የመያዝ ችግር) የገጠማት ሊሳ፣ የንግግር ዘይቤዋ መለወጥ ማኅበራዊ ሕይወቷ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እንዳሰጋት ተናግራለች፡፡ ‹‹ሕይወቴን ሙሉ የሚያውቁኝ ሰዎች በእንግሊዛዊ አነጋገር ዘይቤ ሳወራ ሲሰሙኝ ምን እንደሚሉ አላውቅም፤›› ብላለች፡፡ ቴክሳስ ተወልዶ ያደገ ሰው እንዴት እንደ እንግሊዛዊ ይናገራል? ያሉት ልጆቿም ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡ የንግግር ዘይቤዋን ስላልለመዱት ለመግባባትም ተቸግረዋል፡፡ ሐኪሞቿ ከሚሊዮኖች በአንድ ሰው ላይ ሊከሰት የሚችለው የአነጋገር ዘይቤ ለውጥ እንዴት እንደተከሰተባት ማወቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

* * *

የአባቱን ቀይ መብራት መጣስ ያጋለጠው ሕፃን

አንድ ወንጀል ሲፈጸም ጥፋተኛውን ከሚያጋልጡ ሰዎች መካከል የወንጀለኛውን ቤተሰቦች ማግኘት የተለመደ አይደለም፡፡ ስካይ ኒውስ ያስነበበው ዘገባ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ማስቹተስ ከተማ ውስጥ 911 የአደጋ ጊዜ ጥሪ ይደወላል፡፡ ደዋዩ የስድስት ዓመት ሕፃን ሲሆን፣ አባቱ ቀይ መብራት ጥሶ ማለፉን ለፖሊሶች አሳውቋል፡፡ ‹‹አባዬ ቀይ መብራት ጥሶ አልፏል፤ መኪናው ጥቁር አዲስ ብራንድ ነው፤›› በማለት ነበር ልጁ አባቱን ያጋለጠው፡፡ ጥቆማው የደረሳቸው ፖሊሶች እስካሁን በአሽከርካሪው ላይ የወሰዱት እርምጃ ባይኖርም፣ ልጁ የትራፊክ ሕግጋትን ማወቁ ሲጣስም ማሳወቁ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

* * *

አስገራሚ የእንስሳት ባህሪያት

  • አፍሪካን ሲቬት – ይህ እንስሳ ጭራው አካባቢ በሚገኙ ሁለት እጢዎች ዘይት የመሰለ ፈሳሽ ያመነጫል፡፡ ይህ ፈሳሽ ለሽቶ ኢንዱስትሪው ዓይነተኛ ግብአት ይሆናል፡፡
  • የመሬት ትል – ይህ ደቃቃ የመሰለ ፍጥረት አምስት ጥንድ ልቦች አሉት ቢባል የሚታመን አይመስልም፡፡ ልቦቹም ከላይኛውና ከታችኛው የደም ቬስል ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ የመሬት ትል የወንድና የሴትም ፆታን የያዘ ነው፡፡
  • ሎብስተር – ሎብስተር ጥፍሩን ወይም እግሩን በተለያዩ ምክንያቶች ቢያጣ አዲስ ሊበቅልለት ይችላል፡፡ ምግቡን የሚፈጨው በስድስት ጥንድ መንጋጋ መሳይ ነገር ሲሆን እስከ 100 ዓመት መኖርም ይችላል፡፡
  • አልቅት – ይህ ትንሽ ፍጥረት ከክብደቱ አምስት ጊዜ የሚበልጥ ደም መምጠጥ የሚችል ሲሆን ያለ ምግብም ለ18 ወራት መቆየት ይችላል፡፡ አንድ የጎለመሰ አልቅት የወንድና ሴት ፆታን ስለሚይዝ ራስ በራሱ መራባት ይችላል፡፡
  • የአውሮፓውያን ካት ፊሽ – ይህ ዓሳ አንዳንዴ ዌል በሚል መጠሪያም የሚታወቅ ሲሆን ሦስት ሜትር ርዝመትና 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን በመሆኑ በውኃ ውስጥ ከሚገኙ የዓሳ  ዝርያዎች ትልቁ አድርጎታል፡፡
  • ግመል – የግመል እበት ምንም መድረቅ ሳያስፈልገው እንደ ነዳጅ መጠቀም ይቻላል፡፡
  • ኮራን – ይህ ሥጋ በል እንስሳ በአሜሪካ ይገኛል፡፡ ያደነውን ምግብ ከመብላት በፊት ውኃ ውስጥ እየደጋገመ በማውጣትና በማስገባት ይደፍቀዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ይህ እንስሳ ምግቡን ለምን ምክንያት እንደሚያጥብ ሁነኛ መልስ አለመገኘቱ ነው፡፡
  • የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን መጽሔት፤

(መጋቢት 2005)

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች