Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠልና ውዝግቡ

የብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠልና ውዝግቡ

ቀን:

ብሪታንያ በአውሮፓ ኅብረት አባልነት ለመዝለቅ ካልሆነም ለመገንጠል የሕዝበ ውሳኔ ያካሄደችው ባሳለፍነው ሳምንት ሲሆን፣ ውጤቱም በአውሮፓ ኅብረት መቆየት 48.1 በመቶ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠል 51.9 በመቶ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ የብሪቴናውያኑ በአብላጫ ድምፅ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠልን መምረጥ ለብሪታንያ፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ አደጋ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ብሪቴናውያኑ ግን ላለፉት 25 ዓመታት ሲያብላሉት የኖሩትን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር መኖር ወይም መገንጠል የሚለውን ሐሳብ በመገንጠል ቋጭተዋል፡፡ ብሪቴናውያኑ የሚጠብቃቸው ቀጣዩ ነገር፣ ከመገንጠል በኋላ በምን አኳኋን ከአውሮፓ አገሮች ጋር እንሠራለን የሚለው ነው፡፡ ከእነሱ ውጭ ባሉት የአውሮፓ አገሮች ብሎም በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ውስጥም ሌላ ውዝግብ ተጭሯል፡፡ ለብሪቴን ከኅብረቱ መገንጠል የአገሪቱ ጠቅላይ ማኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የቅስቀሳ ድክመት መሆኑን የሚያነሱም አሉ፡፡ ከእሳቸው ይልቅ የዩኬ ኢንዲፔንደንት ፓርቲ ባደረገው ጠንካራ የእንገንጠል ቅስቀሳ ብሪቴን ከአውሮፓ ኅብረት ተገንጥላለች፡፡ ለዚህም የፓርቲው መሪ ኒጌል ፋራጅ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል የሚሉም አልጠፉም፡፡

ብሪቴን ለምን ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠልን መረጠች?    

ብሪቴናውያን በታሪካቸው ያለጥርጣሬና ያለገደብ የሚቀበሉት ስምምነት የላቸውም፡፡ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች እንኳን ከብዙኃኑ ትንሽ ልዩነት አድርገው ነው ወደ ስምምነት የሚያመሩት፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2008 ዓለም በገንዘብ ቀውስ በተመታችበትና የአውሮፓ ኅብረት ከቀውሱ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ጀምሮ ብሪቴን ጥርጣሬዋን አጠናክራ ቆይታለች፡፡

ብሪቴን የአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚዩኒቲን እ.ኤ.አ. በ1973 እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረትን በ1990 ተቀላቅላለች፡፡ ሆኖም ብሪቴን መቼም ቢሆን የአውሮፓ ኅብረት በብሪቴን ላይ የሚኖረውን የበላይነት እንደ ሌሎቹ አባል አገሮች ሙሉ ለሙሉ ተቀብላ አታውቅም፡፡ በዚህ ረገድ የሸንገን ቪዛ ማለትም የአባል አገሮቹ ዜጐች በነፃነት ከአገር አገር የሚዘዋወሩበት ቪዛ እንዲሁም የአውሮፓ አባል አገሮች መገበያያ የሆነውን ዩሮ አለመቀበሏ እንደምሳሌ ይነሳል፡፡ ከ2008 ወዲህ በብሪቴን እየተቀጣጠለ የመጣው ከአውሮፓ ኅብረት የመገንጠል ጥያቄም ኅብረቱ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ካስመዘገበው ደካማ ውጤት ላይ የመነጨ እንደሆነ፣ ከብሪንተን መገንጠል በኋላ የተሰጡ አስተያየቶች ያሳያሉ፡፡

በ2008 የገንዘብ ቀውስ አሜሪካ ተመታ የነበረ ቢሆንም እንደ አውሮፓ የከፋ አልነበረም፡፡ የአውሮፓ አባል አገሮች በማገገም ፋንታም አሽቆልቁለዋል፡፡ ይህ አገሮች ወደ በጀት ቅነሳ ቀመር እንዲገቡም አስገድዷል፡፡ በወቅቱ የነበረው የገንዘብ ቀውስ የአሜሪካ ሴንትራል ባንክንም ሆነ የአውሮፓ ሴንትራል ባንክን ያሽመደመደ ቢሆንም፣ በአሜሪካ ኢኮኖሚውን ለማነሳሳት በተደረገ ርብርብ ኢኮኖሚው ከ2010 በኋላ መልሶ ሲያንሰራራ፣ በአውሮፓ ኀብረት ባንክ ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰደው የወለድ መጠንን የመጨመር አካሄድ፣ መፍትሔ ሳይሆን ችግርን አጠናክሯል፡፡ በተለይ በግሪክ የተፈጠረው ቀውስ የአውሮፓ ኅብረትን ውድቀት ያሳየ ነበር፡፡ የገንዘብ ቀውሱ ብሪቴንን ብዙም አልጐዳትም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የአባል አገሮቹ በዩሮ ለመገበያየት ሲስማሙ፣ አልቀበልም ማለቷ ነው፡፡ ይህም እንግሊዛውያን የኅብረቱ አባል መሆን አደጋ አለው በሚለው አመለካከታቸው እንዲፀኑ አስችሏቸዋል፡፡ በአውሮፓ የተከሰተው የገንዘብ ቀውስና የብሪቴን ከችግሩ ማምለጥ ብዙዎች በአውሮፓ ኅብረት አባልነት ላይ ያላቸውን የዓመታት ጥርጣሬ ገፍተው እንዲያወጡት አስችሏል፡፡

ቀድሞም የነበረው ውዝግብ ተጠናክሮ በ2012 አጋማሽ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባ ጥያቄ ከፓርላማቸው ቀረበ፡፡ የራሳቸው ወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት በአውሮፓ ኅብረት መቆየት ወይም መገንጠል የሚለው ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም ጠየቁ፡፡ ማኒስትሩ ካሜሩንም፣ በ2013 በሰጡት መግለጫ ከ2015ቱ የብሪቴን ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ሪፈረንደሙ እንዲካሄድ እንደሚያደርጉ ተናገሩ፡፡

ብሪቴን ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠል ያዋጣታል?

ለብሪቴን ከኅብረቱ መገንጠል ሁለት አበይት ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ በየአባል አገሮቹ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የተሰጠው መብት የሚፈጥረው የውስጥ ፍልሰትና በአውሮፓ ኅብረት በስፋት የሚተገበረው የኢኮኖሚ ትብብር ይነሳሉ፡፡ ወግ አጥባቂው ቦሪስ ጆንሰን፣ የአውሮፓ ኅብረት ጫና ፈጣሪነትን በመቃወም ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የአውሮፓ ኅብረት ብዙ በሠራና አባላት ላይ ብዙ ግዳጆችን በጣለ ቁጥር አገሮች በብሔራዊ ደረጃ ውሳኔ የሚሰጡበት አጀንዳ ያጣሉ፡፡ ኅብረቱ አገሮች መቀልበስ የማይችሏቸውን ሕጐች ያወጣል፡፡ አባል አገሮች የተሻለ ሥርዓት አለኝ ቢሉም ተቀባይነት አያገኙም፡፡ በአውሮፓ ደረጃ መሠራት አለበት ይባላል›› ሲሉ ኅብረቱ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን ይተቻሉ፡፡

የሉዓላዊነት ጥያቄም ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ የአንድ አገር ሉዓላዊነት የሚከበረው በማን ነው? በአውሮፓ ኅብረት ወይስ የአገሪቱ? የሚለውም መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡

ብሪቴን ከኅብረቱ በመገንጠሏ ይገጥማታል ተብለው የተገመቱ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ዘዊክ እንደዘገበው፣ ብሪቴን ከአውሮፓ ኅብረት በመገንጠል ለአባልነት የምትከፍለውን ገንዘብ ታስቀራለች፡፡ ብሪቴን ባለፈው ዓመት ብቻ ለኅብረቱ 13 ቢሊዮን ፓውንድ ከፍላለች፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን 4.5 ቢሊዮን የሚያወጣ ገቢ አግኝታለች፡፡

ንግድን በተመለከተ በኅብረቱ አባል አገሮች መካከል በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ ታሪፍ የለም፡፡ ስካይ ኒውስ እንደሚለው፣ ብሪቴንም ከ50 በመቶ በላይ የወጪ ምርቷን ለአባል አገሮቹ በመላክ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ ኅብረቱ ከሌሎች የበለፀጉ አገሮች ጋር በነበረው የንግድ ስምምነትም ተጠቅማለች፡፡ ኅብረቱ ከአሜሪካ ጋር በዓለም ትልቅ የሚባለውን ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት በስምምነት ላይ ሲሆን፣ ይህም ብሪቴንን ተጠቃሚ ያደርጋት ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ በኋላ እንደ አንድ አገር ሌሎች የንግድና የፖለቲካ ስምምነቶችን ካልተፈራረመች በቀደሙት ስምምነቶች መሥራት አትችልም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ከኢንቨስትመንት ጋር በተየያዘ ከኅብረቱ ጋር መቆየት አለባት የሚሉ ወገኖች፣ ብሪቴን ከኅብረቱ መገንጠሏ ትላልቅ የገንዘብ ተቋማቷን ያሽመደምዳል ሲሉ፣ በመገንጠሉ የሚስማሙት ደግሞ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠል ብሪቴን የራሷን ኢኮኖሚ ራሷ እንድትመግብ ያስችላታል ይላሉ፡፡

ሌሎች ዜጐችን ማስተናገድ

ብሪቴን በኅብረቱ ሕግ መሠረት የአባል አገሮችን ዜጐች በአገሬ አላስተናግድም፣ ሥራ አልሰጥም የማለት መብት አልነበራትም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ስታትስቲክስ ቢሮ እንዳሰፈረው፣ በብሪቴን 942,000 ምሥራቅ አውሮፓውያን፣ ሮማኒያውያን እንዲሁም ቡልጋሪያውያን በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ በአውሮፓ በተከሰተው የስደተኞች ፍሰት ደግሞ የቤትና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማቅረብ አዳጋች ሆኗል፡፡ ሆኖም ብሪቴን ከኅብረቱ ብትገነጠልም በአገሪቱ የአባል አገሮች ዜጐችን መቀበል በአንዴ ልትገታው አትችልም፡፡ የመገንጠል ደጋፊዎች አቀንቃኙ ሚስተር ፋራጅ ግን፣ የኢሚግሬሽን ጉዳይ በአንዴ እንዲዘጋ ይፈልጋሉ፡፡

የደኅንነት ጉዳይን በተመለከተ፣ በብሪቴን በሠራተኛና ጡረታ ቢሮ ሴክሬታሪ በመሆን ያገለገሉት አያን ስሚዝ፣ ብሪቴን የኅብረቱ አባል በመሆኗ በሯን ለሽብር አጋልጣለች ብለው ያምናሉ፡፡ በተለይ ለአባል አገሮቹ ክፍት የተደረጉ ድንበሮች የአገርን ደኅንነት ሥጋት ላይ ይጥላሉ ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የወታደራዊ ክፍሉ አመራሮች፣ ከስሚስ በተቃራኒ የኅብረቱ አባል መሆናቸው ለደኅንነታቸው ዋስትና መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የብሪቴን መከላከያ ሴክሬታሪ ሚካኤል ፋሎን፣ ብሪንቴን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጠቃሚ እንደሆነች ሁሉ፣ ከኅብረቱ ተጠቃሚ ነበረች፡፡ በኅብረቱ መሆን ወንጀለኞችን ለመቀያየር የመንገደኞችን ሪከርድ ለመያዝ እንዲሁም ሽብርን በጋራ ለመከላከል ወሳኝ ነበር ብለዋል፡፡

በብሪቴን ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠል ወይም አብሮ መኖር በሚለው ላይ ክርክር ሲደረግ፣ ጥቅሙና ጉዳቱ ሲመዘን የሰነበተ ሲሆን፣ የሪፈረንደሙ ውጤት መገንጠልን አሳይቷል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፣ ከኅብረቱ መገንጠል የለብንም የሚል አቋም ሲያንፀባርቁ የከረሙ ቢሆንም፣ ተሸናፊ ሆነዋል፡፡ ከሪፈረንደሙ በኋላ በሰጡት መግለጫም በጥቅምት 2016 ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታውቀዋል፡፡ የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጄላ መርክል የብሪቴንን ከኅብረቱ መገንጠል ‹‹ታላቅ ፀፀት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ከኅብረቱ መገንጠልን ሲደግፉ የቆዩ ብሪቴናውያንም፣ ከኅብረቱ አባል አገሮች ጋር መልካም ጐረቤት ሆነን እንሠራለን ብለዋል፡፡ ስለመገንጠል ሲወተውቱ የከረሙት ሚስተር ፋራጅ ‹‹ለብሪቴን የነፃነት ቀን›› ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት 28 የአውሮፓ አገሮችን በአባልነት ይዟል፡፡ የአባል አገሮቹ ዜጎች ንግድ እንዲለዋወጡ፣ ከአገር አገር ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል የ‹‹አንድ አገር›› ስሜትነት አለው፡፡ ከአባል አገሮቹ 19ኙ ብቻ በጋራ የሚገበያዩበት ገንዘብ ወይም ዩሮ ያለ ሲሆን፣ የራሱ ፓርላማም አለው፡፡ በቅርቡ ደግሞ የአካባቢ አየር ንብረት ጥበቃ፣ ትራንስፖርት፣ የሸማቾች መብት እንዲሁም ከሞባይል አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ሕጐችን አውጥቷል፡፡ እነዚህ አዳዲስ ሕጐች ያልተመቻቸው ብሪቴናውያን በአውሮፓ ኅብረት ለመቆየት ወይም ለመገንጠል ካነሳሳቸው ዋና ምክንያቶችም የእነዚህ  ተጨማሪ ሕጐች መውጣት ይጠቀሳሉ፡፡ ብሪታንያ የአውሮፓ ኅብረት አባልነት አልተመቸኝም ባሉ ዜጐቿ አብላጫ ድምፅ ከኅብረቱ ተገንጥላለች፡፡ የብሪታንያ ከኀብረቱ መገንጠል ለአውሮፓ ኅብረት ብሎም በኃያላኑ አገሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጐቶች ላይ ምን ተፅዕኖ ይፈጥር ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...