Monday, October 2, 2023

በዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ውጥረት ትኩረት የተነፈጋቸው አፍሪካዊ ስደተኞችና መጪው ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኛንጊድ ኮማኑዶ የሁለት ዓመት ተኩል ጨቅላ ሕፃን ልጇን ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ገላውን በማጠብ ላይ ነች፡፡ በቅርቡ ስድስት ዓመት የሞላት የመጀመሪያዋ ሴቷ ልጅ ውኃ በማቀበል ታግዛለች፡፡ ሁለተኛው ልጇ ከእናቱ ጀርባ ይጫወታል፡፡

ይህችው እናት ከሦስት ዓመት በፊት ያደረገችውን አስከፊና ስቃይ የተሞላበት ጉዞ ስትገልጽ ‹‹ይህችኛዋን (ትልቋን ሴት ልጇን) በጀርባዬ አዝዬ፣ ትንሹን በፊት ለፊት ደረቴ ላይ አዝዬ፤ ይኸኛውን የመጨረሻውን ልጅ የስድስት ወር እርጉዝ ሆኜ በሆዴ ይዤ ነበር የመጣሁት፤›› ብላለች፡፡ በሱዳን እ.ኤ.አ. በ2013 ዳሬሰላም በሚባል የብሉናይል ግዛት አካባቢ የተቀሰቀሰውን ጦርነት በመሸሽ ከ13 ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ በቤንሻንጉል በኩል ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

ቀድሞ ዳሬሰላም በሚባለው ስፍራ በከፊል በግብርና በከፊል በአርብቶ አደርነት ኑሮዋን ትመራ የነበረችው ይህችኛው የሦስት ልጆች እናት፣ ተስፋ በቆረጠ ስሜት እንደምትኖር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በስደተኞች ካምፕ በሚደረግላት እንክብካቤ ራሷንና ልጆቿን በሕይወት ማቆየት በመቻሏ የተፅናናች መሆኗን ትገልጻለች፡፡

‹‹እዚህ በሚሰጡን ዕርዳታ ውለን እናድራለን፡፡ ትልቋም ልጄ እንደነገሩ እያስተማሯት ነው፤›› በማለት አሁን ያለችበትን ሁኔታ በመጣደፍ ገልጻለች፡፡ ጥድፊያዋም የመጣው በዕለቱ የዓለም የስደተኞች ቀን የሚከበርበት ቀን ስለነበር በጣቢያ ውስጥ በነበረው አከባበር ለመሳተፍ ከመፈለግ ነበር፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ከሚገኙት አምስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አንዱ የሆነው የሶሬ የስደተኞች ጣቢያ ከአሥር ሺሕ በላይ የሱዳንና ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞችን ይዟል፡፡ ይኸው ጣቢያም የዘንድሮው የስደተኞች ቀን በዓል የተከበረበት ሲሆን፣ በስፍራውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችና ለጋሽ አገሮች ተወካዮች የታደሙበት ነበር፡፡ ተሳታፊዎች በሥነ ሥርዓቱም ላይ በጣቢያው ለስደተኞች የሚደረጉትን የዕርዳታና የእንክብካቤ ሥራዎች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፣ ከተለያዩ ስደተኞች ጋር በግንባር ተገናኝተው ያሉበትን ሁኔታዎች ማስተዋል ችለዋል፡፡

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን አከባበር ለጋሽ አገሮችና መንግሥታት፣ የረድኤት ድርጅቶችና ዘርፈ ብዙ ተቋማት ስደተኞችን መርዳትና መንከባከብ እንደ ሰብዓዊና ሞራላዊ ግዴታ አድርገው እንዲቀበሉት ለማነሳሳት ያለመ ነበር፡፡ ለዚሁም መሳካት ደግሞ ‹‹ከስደተኞቹ ጎን በጋራ እንቆማለን›› በሚል መርህ ዘመቻ ማካሄድ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን የዩኤንኤችሲአር ኃላፊዎች በሶሬ ስደተኞች ጣቢያ በነበረው የአከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል፡፡

የክብረ በዓሉ መርህ ተደርጎ የተመረጠው ኃይለ ቃል የተለመደውን ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ ወይም በዘፈቀደ የተመረጠ የዕርዳታ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ ያለመ እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡ ይልቁንም ዛሬ በዓለማችን የተከሰቱ እውነታዎችን በመረዳት ለዕርዳታ እጅ ከመዘርጋት ባለፈ መንግሥታት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የስደተኞች ቁጥርና ስቃያቸውን ለመቀነስ ጥረት እንዲያደርጉ ለመቀስቀስ ያለመ ነበር፡፡ በመሆኑም መንግሥታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን በማሳየት የማንኛውን አገር ስደተኞች ጉዳይ እንደራሳቸው ጭምር በማየት ወገንተኝነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸውም ለመወትወትና ለማሳሰብ በዓሉ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ እስከ ባለፈው ወር ግንቦት መጨረሻ ድረስ በመላው ዓለም የስደተኞችና ተፈናቃዮች ብዛት 65.3 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ይህ ቁጥር ደግሞ የፈረንሳይን የሕዝብ ብዛት የሚያህል ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ያልተከሰተና በታሪክ ትልቁ የዓለም ሕዝብ የተፈናቀለበት ክብረወሰን ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በሌላ አነጋገርም የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከተመሠረተ ቢሞላው የ50 ዓመት ቢሆንም፣ በታሪኩም ይህን ያህል ቁጥር አስተናግዶ እንደማያውቅ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ይህ የስደተኞች ቀውስ ደግሞ ሁሉንም አኅጉራት ሲያዳርስ ከፍተኛው ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማመንጨት ቅድሚያ የያዙት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሲሆኑ፣ የአፍሪካ አገሮች ተከታዩን መያዛቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ነገር ግን የዚሁን ቀውስና ጫና በመሸከም ረገድ ትልቁ ሸክም የወደቀው በድሃ አገሮች መሆኑም ተመልክቷል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች መመንጫ የሆኑ አገሮችን በተናጠል ሲታይ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩክሬን፣ ብሩንዲ፣ የመን፣ መካከለኛዋ አፍሪካ ሪፑብሊክና ሌሎች አገሮች በቅደም ተከተል ደረጃውን በመያዝ ይጠቀሳሉ፡፡

በተለያዩ አገሮች በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በድንበር ዘለል ግጭቶች፣ በሽብርተኞች እንዲሁም በአምባገነን መንግሥታት ከተፈጠሩ ቀውሶች ራሳቸውን ለማዳን ዜጎች ወደ ተለያዩ ጎረቤት አገሮች መጠለያ በመፈለግ እንዲነጉዱ ያስገድዳሉ፡፡ እንዲሁም በከፍተኛ አደጋ በተሞላባቸው ሁኔታዎች ሚሊዮኖች በረሃ አቋርጠውና ምንም ዓይነት ዋስትና በሌለው የጀልባ ጉዞ በመቅዘፍ ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና እስያ አገሮች እየፈለሱ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በእያንዳንዱ ስደተኛ ላይ እየፈጠረ ካለው ስቃይ፣ እንግልትና ስደት በተጨማሪ ስደተኞች ለማስተናገድ በራቸውን ከፍተው በሚቀበሉ አገሮች ላይም እያስከተለ ያለው ጫናም ከባድ እየሆነ እንደመጣ ተወስቷል፡፡

ለአብነትም ያህል ከፍተኛውን ቁጥር ያለው ስደተኞችን በመያዝ ቱርክ በዓለም ካሉ አገሮች በአንደኝነት ስትጠቀስ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም በአምስተኛ ደረጃ በአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ከሆነች ሁለት ዓመታት አልፈዋል፡፡

ቱርክ 2.5 ሚሊዮን፣ ፓኪስታን 1.6 ሚሊዮን፣ ሊባኖስ 1.1 ሚሊዮን (ከሕዝቧ ቁጥር በላይ)፣ ኢራን 979,400፣ ኢትዮጵያ 737,979፣ ዮርዳኖስ 664,100፣ ኬንያ 553,912 እንዲሁም ኡጋንዳ 477,187፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ 381,100 እና ቻድ 369,540 የሚደርሱ የሌሎች አገሮች ዜጎች የሆኑ ስደተኞችን በማስተናገድ የዓለም አሥሩ ቀዳሚ አገሮች ተደርገው ተለይተዋል፡፡

እነዚህ አሥር አገሮች ከሚያስተናግዷቸው የስደተኞች ቁጥር ቀዳሚውን በመያዝ ይጠቀሱ እንጂ በመላው ዓለም 87 የሚደርሱ አገሮች እንዲሁ መጠናቸው የተለያዩ ስደተኞች እንደሚያስተናግዱ ኮሚሽኑና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አረጋግጠዋል፡፡

ይህን ችግር አንዳንዶች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተ ትልቁ የሰብዓዊ ቀውስ ይሉታል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከሰተ ከፍተኛው ቀውስ በማለትም የሚገልጹት አሉ፡፡ የዚህ ሰብዓዊ ቀውስ ክስተት ለምድራችን እየተከሰቱ ካሉት ቀውሶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ ከሞላ ጎደል ሁሉንም እያስማማ የመጣ ቢመስልም፣ የዓለም አገሮችም ሆኑ መንግሥታቶቻቸውና ለጋሾች ግን የችግሩን ግዝፈት በሚመጣጠን መልኩ ትኩረት እንዳልሰጡት እየተነገረ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ ደግሞ በዘንድሮው የስደተኞች ቀን አከባበር ላይ በስፋት ተስተጋብቷል፡፡ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ኮሚሽኑና የተለያዩ በሰብዓዊ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ በተመድ ሥር ያሉ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶች ጩኸታቸው ከፍ አድርገው ለማሰማት ሲሞክሩ ተሰምቷል፡፡

የዓለም አቀፉንም ትኩረት ለመሳብም ሲባል በኮሚሽኑና በሌሎች አገር ድርጅቶች የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ታዋቂ የሆሊውድ ስመጥር ተዋናዮችና ባለሙያዎች፣ ታዋቂ አቀንቃኞች፣ የሥነ ጽሑፍ ባለሟሎች፣ ስፖርተኞችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ የተለያዩ አገሮች ዝነኞችን ጭምር በመጠቀም ሰፊ ዘመቻ ተካሂዷል፡፡ በመላው ዓለም የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳያገኝ ካደረጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ የዓለም የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ትኩረቱን በአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳ በተለይም የዶናልድም ትራምፕ አወዛጋቢነት፣ የታላቋ ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ፖለቲካ፣ የአውሮፓውያን ብሔርተኝነትና የድንበር ቁጥጥር በማጥበቅ ከስደተኞች ጋር የሚደረጉ ግብግቦች ናቸው፡፡ 

ይህ ጉዳይ ደግሞ ኮሚሽኑንና አጋሮችን ከፍተኛ ሥጋት ላይ የጣለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አገሮች ውስጥ ያሉ ስደተኞች ያገኙት ትኩረት ከሌላው ዓለም አንፃር አነስተኛ መሆኑ አሳሳቢነቱን የከፋ አድርጎታል፡፡ ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ባለው የሶሬ ጣቢያ በዓሉ በተከበረበት ወቅት የተስተጋባውም ይኸው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ዋና ተጣሪዋ ክሌሜንቲን ንክዌታ ሳላሚ፣ በዚህ ዓመት የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ካለፉት አሥርት ዓመታት ከተከሰቱ እውነታዎች ሁሉ ባልተለመደ ሁኔታ አስደንጋጭ ሆኖ ሳለ ሰብዓዊ ቀውሱን ምላሽ ለመስጠት የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘቱም ፈታኝ ሆኗል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በስደት የሰው ልጅ እየተጠቃ ነው፡፡ በዓለማችን ከ113 ሰዎች ቢያንስ አንድ ሰው ለስደት የተጋለጠ ነው፡፡ በየአንድ ደቂቃው 24 ሰዎች ይሰደዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ አዋቂ ሰው የመተንፈሻ ጊዜ የፈጠነ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 33.9 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸው ታሪክ ዘግቦታል፡፡ ዛሬ ግን ይኸው ቁጥር ወደ 65.3 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልግ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁ ቀውስ ውስጥ መግባቱና አገሮችም የገንዘብ ድጋፉን በመለገስ በጋራ ለመሥራት ያላቸው ተነሳሽነትም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፤›› በማለት ተጠሪዋ የጊዜውን ፈታኝነት ገልጸዋል፡፡

የሰብዓዊ ቀውሱ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና አገሮች ትልቅ ሥጋት እንደሆነ ያወሱት ሳላሚ፣ አገሮች ከስደተኞች መብዛት የተነሳ የደኅንነት ሥጋታቸውንም ሆነ ስደተኞችን በመንከባከብ ችግሩን ለመቀነስ በተናጥል በራቸውን (ድንበራቸውን) ከመከርቸም ይልቅ በወገናዊነትና በኃላፊነት ስሜት በጋራ መቆም ብቸኛው መፍትሔ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም በርከት ያሉ የአውሮፓ አገሮችን ጨምሮ የተለያዩ ምዕራባውያን ለጋሽ አገሮች ስደተኞችን ለመደገፍ ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ ድንበሮቻቸውን ለመዝጋት በማስቀደማቸው ሰብዓዊ ቀውሱ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ምክንያት ከሆነው ባልተናነሰ እየተስተዋለ መሆኑን ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡

በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሃ አገሮች ምንም እንኳ የራሳቸው የውስጥ ሰብዓዊ ቀውስ ጋር እየታገሉም ቢሆንም፣ ለተፈናቃዮች በራቸው ከፍተው ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› በማለት አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን አወድሰዋል፡፡ ‹‹በአፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር ያለውን ስደተኛ እያስተናገደች በአንደኝነት ተቀምጣ፣ ከዓለም ቢሆን ከፍተኛ አስተናጋጅ አገሮች አንዷ ሆናም ለስደተኞች ያላትን ክፍት ፖሊስ ኢትዮጵያ ቀጥላበታለች፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካስጠለለቻቸው 738,000 ስደተኞች ውስጥ 57.2 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤት ሊላኩ ሲገባቸው ወደ ስደት ጣቢያ እንዲታጎሩ መገደዳቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹አሳዛኙ ነገር እዚህ በጣቢያዎች ያሉ ሕፃናት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት ትምህርት እያገኙ አይደለም፡፡ ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባት ያለን የሀብት አቅም አገልግሎቱን መስጠት አላስቻለንም፤›› ሲሉ ሰላሚ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ጥሪያቸው ኢትዮጵያ ላስጠለለቻቸው ስደተኞች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ለተጠቁ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ለጋሽ አገሮችና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ነበር ጥሪ ያቀረቡት፡፡

‹‹በእኛ ሥር የምናስተዳድራቸው ስደተኞችን ድጋፍ እንዲያገኙ ስንማጸን በኤልኒኖ ምክንያት በድርቅ የተጠቁ ኢትዮጵያውያንንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታውን እንዲያደርግም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ ከ70,000 በላይ የሚደርሱ ስደተኞች በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግሥት በሚደረግላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ያሉ መሆናቸውን ልገልጽ እወዳለሁ፤›› ሲሉ ሰላሚ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስደተኞች ጣቢያዎችን በበላይነት ከኮሚሽኑ ጋር የሚያስተዳድረው የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ባለሥልጣን በአገሪቱ የስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ ቢመጣም ለስደተኞች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች አለማሟላታቸውን በመግለጽ በተመሳሳይ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል ‹‹ምግብ፣ መጠለያና የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ያልተሟሉ በመሆናቸው አስቸኳይ ዕርምጃ ካልተወሰደ ወደ ባሰ ሁኔታ መግባታችን አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስደተኞች አብዛኞቹ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚፈልጉና ልጆቻቸውን ማስተማር የሚፈልጉ ቢሆኑም፣ አቅማችን ውስን ነው፤›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሶሬ የስደተኞች ጣቢያ የስደተኞችን ሁኔታ ተዘዋውረው ከጎበኙ እንግዶች አንዷ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት ፖለቲካ ጉዳይ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አይሻ አብዱላሂ ‹‹እነዚህ ስደተኞች ያሉበት ጉዳይ አስደንጋጭ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ በተለይ በርካታ ሕፃናት የትምህርት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ካስተዋሉና በስደተኞች ኮሚሽኑና አጋሮች የትምህርት አቅርቦት ለማድረግ ያለባቸው የሀብት ውሱንነት በመገንዘብ በኅብረቱ ስም የ20,000 ዶላር የገንዘብ ዕርዳታ አበርክተዋል፡፡

ኮሚሽነሯም እንደ ኮሚሽኑ ተጠሪ ሁሉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለስደተኞችም ሆነ በኢትዮጵያ ድርቅ ተጠቂዎች ትኩረት አለመስጠቱን በማንሳት ጥሪያቸውን ደግመው አቅርበዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት ድግፋቸውን ካልለገሱ አብዛኞቹ ስደተኞችን የባሰ ሥጋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አቶ ዘይኑ አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን የጎረቤት አገሮች ዜጎች የከፋ ስደት እስካፈናቀላቸው ድረስ በሯን ከፍታ በመቀበል አፍሪካዊ ወገንተኝነቷን ትገፋበታለች ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ሀብታም አገሮች በራቸውን ሙሉ ለሙሉ ላለመክፈት እየታተሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ስደተኞች ወደነሱ አገር በማጓዝ የሚፈጥሩትን ጫና ለመቀነስ በአፍሪካ አገሮች ስደተኞችን በዚያው ለማስቀረት ሲያደርጉት የነበውን ድጋፍም የዘነጉት ይመስላል፡፡

እንደ ኛንጊዲ ኩማኑዶ የመሳሰሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካዊ ስደተኞች ከአገራቸው ተፈናቅለው በጎረቤት አገሮች ለጊዜውም ተጠልለው ሕይወታቸውን ማቆየት ቢችሉም፣ ነገ ሌላ ፈተና እንዳይገጥማቸው ሥጋት አጭሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -