Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሎጂስቲክስ እጥረት 200 ሺሕ ቶን ማዳበሪያ እስካሁን ወደ አገር አልገባም

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በርካታ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸውና የደረሱትን ዕቃዎችም በፍጥነት ማንሳት ባለመቻሉ በ2008 ዓ.ም. የግብርና ምርት ዘመን የሚያስፈልገው ማዳበሪያ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠቃሎ አለመግባቱ ተገለጸ፡፡

ለ2008 ዓ.ም. ምርት ዘመን 852 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል፡፡ በየቀኑ 70 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ በየብስ ትራንስፖርት በማጓጓዝ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ለአርሶ አደሩ ለማሠራጨት ታቅዶ ነበር፡፡

ነገር ግን በርካታ ዕቃዎች በአንድ ጊዜ ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸውና የሎጂስቱክስ አቅርቦት እጥረት በመፍጠሩ በዕቅዱ መሠረት ለምርት ዘመኑ ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው አገር ውስጥ መግባት እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብዓት ግዥ ቡድን መሪ አቶ ዘላለም አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተገዛው ማዳበሪያ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ተጠቃሎ መግባት እንዳለበት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ሁለት መርከብ ማዳበሪያ ወደ አገር አልገባም፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እስካሁን 650 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ አገር ውስጥ እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ መቶ ሺሕ የሚሆነው በሱዳን ወደብ በኩል ወደ አገር መግባቱንም ተናግረዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መንግሥት ከራሱ የገንዘብ ምንጮች ወጭ በማድረግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት የውጭ ምንዛሪ ለንግዱ ማኅበረሰብ እንዲቀርብ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

እነዚህ ሁለት ከፍተኛ ግዥዎች ከማዳበሪያ ግዥ ጋር ተዳምረው የጂቡቲ ወደብን ማጨናነቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ይህንን መጨናነቅ ለማስቀረት የሱዳንና የበርበራ ወደቦች መጠቀም የጀመረ ሲሆን፣ ለአማራና ትግራይ ክልሎች የሚውል 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በሱዳን በኩል መግባቱን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር ምክንያት ማዳበሪያ በወቅቱ ማንሳት አለመቻሉን፣ ወደ አገር የገባውም ቢሆን መንግሥት ቅድሚያ እንዲሰጥ በመወሰኑ ሊገባ እንዳልቻለ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡

የማዳበሪያ መዘግየት ችግር እንዳይፈጥር በተቻለ መጠን ቅድሚያ የሚፈልጉትን አካባቢዎች በመለየት በተመጣጠነ መልኩ እንዲሠራጭ መደረጉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች