የዓድዋ የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. ትምህርት መስጠት እንደሚጀምር የዩኒቨርሲቲው አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፡፡ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በዓድዋ ከተማ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ዩኒቨርሲቲው፣ የሕንፃ ዲዛይኑ እንደተጠናቀቀና ግንባታው በቀጣይ ሁለት ዓመታት እንደሚገባደድ ኮሚቴው አስታውሷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ይሠራል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ መዘግየቱ ጥያቄ ቢያስከትልም፣ በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት እየተቀረፀ መሆኑን የኮሚቴው አባል አየለ በከሪ ዶ/ር ገልጸዋል፡፡ ቀዳሚ ትኩረቱን በፓን አፍሪካን ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የሰብአዊ ሳይንስ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ሌሎችም ትምህርቶች ከድኅረ ምረቃ ጀምሮ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚቴው ጥር 7 እና 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የሚያደርገውን አገራዊ ጉባዔ በተመለከተ ጥር 2 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ቢተው በላይ እንደተናገሩት፣ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የመላው አፍሪካውያን በመሆኑ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ድሉ በተገኘበት ቦታ በዓድዋ መቋቋሙ ዘግይቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ምሥረታ በማስታከክ በሚካሄደው ጉባዔ፣ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ስላለው አስተዋፅኦ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ‹‹ድሉ የዓለም ቅርስ ነው፡፡ ታሪኩ የተሠራው በአገራችን ሕዝቦች ቢሆንም፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ተስፋ የፈነጠቀ ነው፤›› ሲሉ አቶ ቢተው ገልጸወል፡፡ ይኼንን ታሳቢ በማድረግም ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ የፓን አፍሪካን ጉዳዮች ምሁራን የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከሁለት ወር በኋላ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ያለውን ሚና የሚመጥኑ ሥራዎች አለመሠራታቸውን የተናገሩት የኮሚቴው አባል ሙሉጌታ አበበ (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ማዕከል በመሆን ክፍተቱን ይሞላል ብለዋል፡፡ በየዓመቱ የዓድዋ ድልን ዘክሮ ቀጣዩ ዓመት እስከሚመጣ ምንም ሳያከናውኑ ከመጠበቅ ዘላቂነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
ጉባዔው በዩኒቨርሲቲው ግንባታ ሁሉም ዜጎች እንዲሳተፉ ለማነሳሳት ያለመ መሆኑን የኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡ ጉባዔውን ከዚህ ቀደም ለማዘጋጀት ቢያስቡም በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ወደዚህ ወር ለማስተላለፍ መገደዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተማሪዎች ቅኝ ግዛትና ባርነትን ስላማከሉ ጉዳዮች የሚያጠኑበት ከመሆኑ ባሻገር ስለ አፍሪካ ሕዝብ ባህልና ታሪክ እንደሚጠናበትም ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ሐሳቡን እየደገፉ እንደሚገኙ አቶ ቢተው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የፓን አፍሪካ ጥናቶች መዲና ይሆናል ብለዋል፡፡ ብዙዎች ዩኒቨርሲቲው በተያዘለት ጊዜ ስለመጠናቀቁ ጥያቄ ቢኖራቸውም፣ የኮሚቴው አባላት በ2012 ዓ.ም. ትምህርት እንደሚጀመር አስረግጠዋል፡፡