Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናማረሚያ ቤት አስተዳደር በእነ አቶ በቀለ ገርባ አቤቱታ ላይ መልስ እንዲሰጥ ታዘዘ

ማረሚያ ቤት አስተዳደር በእነ አቶ በቀለ ገርባ አቤቱታ ላይ መልስ እንዲሰጥ ታዘዘ

ቀን:

  • ዓቃቤ ሕግ በቅድመ ክስ መቃወሚያ ላይ መልስ ሰጠ

በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፤ እነ አቶ በቀለ ገርባ ታስረው የሚገኙበት የፌዴራል ማረሚያ ቤት የተለያዩ በደሎችን እየፈጸመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት በማመልከታቸው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ  ሰጠ፡፡

እነ አቶ በቀለ ገርባ በተመሠረተባቸው ክስ ላቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ የከሳሽ ዓቃቤ ሕግን ምላሽ ለመቀበል ሰኔ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ለተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ በድጋሚ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በማረሚያ ቤቱ እንደተገለሉ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ብሎ በነበራቸው ቀጠሮ እየደረሰባቸው የነበረውን በደል ማለትም ጥቁር ልብስ አትለብሱም መባልና በቀጠሯቸው ቀን የተለያዩ ምክንያቶች በመስጠት ፍርድ ቤት አለማቅረብን ጨምሮ ሌሎች እየደረሰባቸው ያለውን በደል በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡ ቢሆንም፣ በተጨማሪ እየተበደሉ መሆኑን ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

አሁን በማረሚያ ቤት ያሉት ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ተገልለው መሆኑን፣ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሲውሉም ሆነ ክስም ሲመሠረትባቸው የተገለሉ መሆኑን እንደተገነዘቡ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተለየ ጫና አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው  ተናግረው ኃላፊነት ስላለበት ማረሚያ ቤት ተገኝቶ ያሉበትን ሁኔታ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የታራሚዎችንና የተጠርጣሪዎችን የአያያዝ ሁኔታ የመጎብኘትና ደኅንነታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት ተከሳሾቹ፣ እነሱ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ተገኝቶ ያሉበትን ሁኔታ እንዲጎበኛቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡ ሌላው ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ክስ የተጠቀሱ የሕግ አንቀጾች ከባድ ቅጣት የሚያስቀጡ ከመሆኑ አንፃር፣ የክርክር ሒደቱ በግልጽ ችሎት መደረግ እንዳለበትና ቤተሰቦቻቸውም ተገኝተው እንዲከታተሉት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ላቀረቡት አቤቱታ በሰጠው ምላሽ በማረሚያ ቤቱ እየደረሰባቸው የሚገኘውን በደል በሚመለከት በጽሑፍ ማቅረባቸውን ጠቁሞ በአቤቱታው መሠረት ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል፡፡ የችሎት ሒደቱን በሚመለከት በተለየ ሁኔታ በሕግ ክልከላ ከተጣለባቸው የወንጀል ድርጊቶች ውጭ የሆኑ ክሶች በግልጽ ችሎት እንደሚካሄዱ አስታውቆ፣ የእነሱም ክስ በግልጽ ችሎት የሚታይ በመሆኑ ማንም ታድሞ መከታተል እንደሚችል ገልጿል፡፡ ቀደም ብለው አመልክተው ቢሆን ኖሮ በተመሳሳይ ቀን ቀጠሮ ያላቸውን ተከሳሾች አስቀድሞ በመሸኘት የእነሱን ክስ መከታተል የሚፈልጉት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ይችል እንደነበር በመጠቆም፣ በዕለቱም ያልገቡት ተከልክለው ሳይሆን ቦታ ጠቦ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት የአያያዝ ጉድለትን በሚመለከት የማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዕለቱ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ባቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቤ ሕግ የሚሰጠውን ምላሽ ለመቀበል መሆኑን ተከትሎ ዓቃቤ ሕግ በቅድመ ክስ መቃወሚያው ላይ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን እንደሌለውና ክሱ ድርጊቱ ተፈጽሟል በተባለበት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት የሚችል መሆኑን በሚመለከት ላቀረቡት መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስና ያቀረቡት የሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ ግንኙነት ስለሌለው ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ በወንጀል ሕግ አንቀጽ ሁለት መሠረት ሕገወጥ መሆኑን የገለጹት የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔን ጠቅሰው መሆኑን ያስታወሰው ዓቃቤ ሕግ፣ የተከሳሾቹ መቃወሚያና የሰበር ችሎት ውሳኔ ግንኙነት እንደሌለው የተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊት በሕግ የተደነገገና ሕጋዊ የሆነን የሕግ መርሕ በመጣስ የተፈጸመና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን የጣሰ በመሆኑ መቃወሚያቸው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ የሽብር ድርጊትን በሚመለከት የመዳኘት ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑ በአዋጁ ስለተደነገገም የዳኝነት ሥልጣንን በሚመለከት የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡

በአጠቃላይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾች ባቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ ላይ ባቀረበው የመቃወሚያ ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ ተከሳሾች በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ 130 ላይ ከተመለከተው ውጭ ዝርዝር ፍሬ ነገርና ግንኙነት የሌለው መቃወሚያ መሆኑን ገልጾ ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን መቃወሚያዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...