Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመንግሥትን ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው የኢንዱስትሪ ዘርፍ

  መንግሥት ባለፉት 15 ዓመታት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲቀየር ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ አሁን ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ በዚህ ረገድ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ወደ አገሪቷ መምጣት ተችሏል፡፡ ለምሳሌ ያህል በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በሲሚንቶ፣ በፋርማሲውቲካልስ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰዋል፡፡ በዚህ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ በዋነኝነት ቻይና፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ እንግሊዝና ሌሎችም አገሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  እንደ ኃይጇን ያሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችለዋል፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ የሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 20 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘርፉን 25 በመቶ ለማሳገድ ተልሟል፡፡ ነገር ግን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁንም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር ከአምስት በመቶ ፈቅ ማለት አልቻለም፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ የአገሪቷን ኢኮኖሚ መምራት ያለበት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ነው ቢልም፣ ዕቅዱና ትግበራው ሲታይ ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው፡፡ ይልቁንም የአገልግሎት ዘርፉ ከመንግሥት እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ ሳይደረግለት የአገሪቷን ኢኮኖሚ የአንበሳ ድርሻ ከግብርናው ዘርፍ በመረከብ እየመራው ይገኛል፡፡

  ለኢንዱስትሪው ዘርፍ አለማደግና አለመጠናከር በርካታ የሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡ በዋነኝነት ግን የሚጠቀሰው መንግሥት በወረቀት ላይ ያሰፈራቸውን አጓጊ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች ብሎም የኢንቨስትመንት ማትጊያ መሣሪያዎች በቅጡ መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚጠቀሱት የኃይል አቅርቦት ችግር፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች ደካማ መሆን በአብዛኛዎቹ የባለድርሻ አካላት በዘርፉ ላይ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡ መንግሥት እነዚህን መሠረታዊና ለዘርፉ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት ቃል ቢገባም፣ በተተበተበ የቢሮክራሲ ሥርዓት፣ ሙስና፣ በአስተዳደራዊ መነቆዎች ምክንያት እነዚህን አገልግሎቶች በብቃት መስጠት አልቻለም፡፡

  በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ችግሮች በተቀናጀ መልክ ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ ፓርክን የማልማት ስትራቴጂን መርጦ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ግዙፍ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገነቡ ሲሆን፣ በመገንባት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ ሥራ ከጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የቦሌ ለሚና የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ ተጨማሪም በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባሻገር፣ ቦሌ ለሚ ሁለት፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህር ዳርና መቐሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሊገነቡ ታቅደዋል፡፡

  መንግሥት ለእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከዓለም አቀፉ የሶቭሪን ቦንድ ገበያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል፡፡ ይህንን ገንዘብ አገሪቷ በውጭ ምንዛሪ መልሳ የምትከፍለው ሲሆን፣ እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በፍጥነት ወደ ሥራ ገብተው ከሚገኘው ገቢ ብድሩ መመለስ አለበት፡፡ መንግሥትም በተለይ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገባደጃው ላይ በመድረሱ፣ እንደ ፊሊፕስ ቫን ሁዩዝን ያሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎችን መሳብ ችሏል፡፡ ከዚሁም ዘርፍ መንግሥት በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዷል፡፡ በተመሳሳይ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዷል፡፡

  ሆኖም ግን በመገንባት ላይ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ የግንባታ ግድፈት እየታየባቸው ሲሆን፣ ይህም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተስፋ ላይ ጥቁር ጥላ አጥልቶበታል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በፓርኮቹ ውስጥ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሞራል ድቀት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ሰሞኑን በቦሌ ለሚ አንድ የኢንዱስትሪ ዞን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተዘዋውረው እንዳዩትና ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ ከውኃ አቅርቦት ጀምሮ ሌሎች አገልግሎቶች በቅጡ አለመሰጠታቸው ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡

  አልፎ ተርፎ መንግሥት በራሱ ግድፈት በተከሰቱ ችግሮች ኩባንያዎቹን ለኪሳራ እየዳረጋቸው ነው፡፡ በዚሁ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው አንድ የውጭ ኩባንያ በግንባታ ችግር ምክንያት ለሚያፈስ ውኃ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ክፍያ የተጠየቀ ሲሆን፣ እዚህ ጋር የሚያሳዝነው ነገር ስህተቱ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋሙ እንደዚህ ዓይነት የተጋነነ የውኃ አገልግሎት ክፍያ ለመጠየቅ አለማንገራገሩ ነው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢንዱስትሪ ፓርኩን የገነቡት የአገር ውስጥ ተቋራጮች እንደገና የጥገና ሥራ እንዲሠሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ይህ በሥራ ፍሰቱ ላይ የሚያመጣው መስተጓጐል ከፍተኛ ነው፡፡

  በሌላ በኩል በቀደምትነት የኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን የተቀላቀሉት እንደ አይካ አዲስ ያሉ ኩባንያዎች በዓለም ገበያው ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዳቃታቸው እየገለጹ ይገኛል፡፡ ይባስ ብሎ በየዓመቱ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን እንዲሁም ሌሎች መሰል አምራቾች ደግሞ መክሰራቸውንና ንብረታቸው ላይ ሐራጅ መውጣቱ እንዲሁም ኩባንያዎቹ ለመፍረስ ቋፍ ላይ መሆናቸውን እየተገለጸ ነው፡፡

  ከጥቂት ወራት በፊት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ጋር በተያያዘ ተነስቶ የነበረው ውዝግብ የሚታወስ ሲሆን፣ በጊዜውም የአገር ውስጥ የግንባታ ተቋራጮች በልማቱ ላይ ዕድል አልተሰጠንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም ሲሰማ የነበረው ምላሽ የአገር ውስጥ የግንባታ ተቋራጮች የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን የማልማት አቅም የላቸውም የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች እንዳሉበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት በዕቅድ ደረጃ ያስቀመጠውን ማለትም አገሪቷን በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ እምብርት የማድረግ ዕቅድ፣ ለማሳካት ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶታል፡፡

  እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ዋነኛ ጉዳይ በዘርፉ ላይ የሚታዩት ችግሮች በጊዜ እልባት ካልተበጀላቸው፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን የውጭ ኩባንያዎች የሚያሸሽና ወደ አገሪቷ ለመምጣት የሰቡትን ሌሎች ኩባንያዎች የሚያስቀር መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥት ዕቅድ ፍሬ አልባ ከማድረጉ ባሻገር፣ አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋታል፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ትኩረት ይሻል፡፡

        

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...