የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማ ውስጥ ለብስክሌት መጋለቢያ እንዲሆን ያሠራውን ማካፈያ ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲገለገልበት አሳስቧል፡፡
* * *
በጨዋታ መካከል ፈስተሃል ተብሎ ተጫዋቹ በቀይ ተባረረ
ሊጃርና ኤስኬ ተከላካይ ሆኖ የሚጫወተው አዳም ሊዲን ሊጀንቪስት ሜዳ ላይ ፈስተሃል በመባሉና ይህንንም ያደረገው ዳኛውን ለማስቆጣት ነው ተብሎ በመታመኑ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ መደረጉን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ በዚሁ ምክንያት ሁለተኛ ቢጫ በማየት ከሜዳ የወጣው ተጫዋቹ ሆዱን አሞት እንደነበር በመግለጽ ዳኛው የጣለበት ቅጣት እንዳበሳጨው ተናግሯል፡፡ ‹‹ሁለት ቢጫ ካርዶች አየሁኝ ከዚያም ቀይ፡፡ በሁኔታው በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ ይህ በእግር ኳስ ሜዳ ተመልክቼ የማላውቀው ፍጹም እንግዳ ነገር ነው፤›› በማለት በትንሹ እንኳን ጋዝ ማስወጣት አልችልም ወይ? የሚል ጥያቄ ለዳኛው ማቅረቡን ዳኛውም አትችልም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተጫዋቹ ዳኛው ምናልባትም ሆነ ብሎ እሱ ላይ የፈሳ ሳይመስለው እንዳልቀረ ጥርጣሬውን ገልጿል፡፡ ‹‹በፈስ አንድ ሰውን ለማበሳጨት መሞከር የተለመደም አሪፍም አይደለም፤›› ብሏል ተጫዋቹ፡፡
ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን ሰድበዋል የተባሉት የዩኒቨርሲቲ መምህር ተባረሩ
በቱርክ ቤልጂ ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኒኬሽን መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዛይፕ ሳያን በክፍል ውስጥ በማስተማር ላይ ሳሉ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን ሰድበዋል በሚል ዩኒቨርሲቲው እንዳባረራቸው የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡ ጉዳዩን የሰማው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መምህሯን ወዲያው ሲያባርር ሁኔታው በአጠቃላይ ተመርምሮ በፕሮፌሰሯ ላይ በቀጣይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ መመርያ አስተላልፏል፡፡ ሁኔታው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው መምህሩ የሰጡት ሌክቸር በዝርዝር ማኅበራዊ ድረገጽ ላይ መለቀቁን ተከትሎ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ይህን ከተመለከቱ በኋላ የፕሮፌሰሯ ተግባር ያልተገባ ነው በማለት አውግዘዋል፡፡ በቱርክ አገሪቱን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ወይም ተቋማትን መስደብ ወንጀል ነው፡፡ ይህን ያደረጉ ደግሞ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ፡፡
ኑሮ እጅግ ውድ የሆነባቸው 19 የዓለም ከተሞች
የኢንቨስትመንት ኮንሰልተንሲ የሆነውና የዚህን የፈረንጅ የዓመት የኑሮ ወጪ ዳሰሳ የሠራው ሜርሰር የተሰኘው ድርጅት ኑሮ የሚቀመስ አይሆንም ያለባቸውን 12 ከተሞች ለይቷል፡፡ ምንም እንኳ የምዕራባውያን ከተሞች ኑሮ እጅግ ውድ የሚሆንባቸው ናቸው ተብሎ ቢታሰብም ኮንሰልታንሲው ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት መሠረት አድርጐ ባወጣው ዝርዝር ግን የደቡብ ምሥራቅ እስያና የአፍሪካ ከተሞች መጉላታቸው ተዘግቧል፡፡ በዳሰሳው አዳዲስ የገበያ ዕድሎች፣ የውጭ ምንዛሪ መዋዠቅ፣ መሠረታዊ ቁሶች ላይ የሚታየው የዋጋ ውድነት በተለይም እንደ መኖሪያ ያሉን የመግዛትና የመከራየት አቅም ታይተዋል፡፡ ኑሮ እጅግ ውድ ይሆንባቸዋል የተባሉት በቅደም ተከተል ከመጀመሪያ የቻይናዋ ሆንግኮንግ፣ የአንጐላዋ ሉዋንዳ፣ የስዊዘርላንዷ ዙሪክ፣ ሴንጋፑር፣ የጃፓኗ ቶኪዮ፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ የቻይናዋ ሻንጋይ፣ የስዊዘርላንዷ ጄኔቫ፣ የቻዷ ንጃሚና፣ የቻይናዋ ቤጂንግ፣ ኒውዮርክ፣ የቻይናዋ ሻን ዞን የስዊዘርላንዷ በርን፣ የናይጄሪያዋ ሌጐስ፣ የደቡብ ኮሪያዋ ሶል፣ የሲሼልሷ ቪክቶሪያ፣ ለንደን፣ የቻይናዋ ጓንጁና የእስራኤሏ ቴልአቪቭ ናቸው፡፡
* * *
ጤናህን ምጠይቅ…
‹‹እንዴት ነህ?›› የምለው
የገዛ ሕይወቴ እያሳሰበኝ ነው
ይህ ማለት ምንድን ነው?
‹‹ደህና ነኝ›› ስትለኝ
በሌላ አነጋገር
ደህና ነኝ ማለት ነው!
(ምልእቲ ኪሮስ)