Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቅዱስ ያሬድ ከተማ

የቅዱስ ያሬድ ከተማ

ቀን:

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስተን ለአንድ ሰዓት ከተጓዝን በኋላ የአንዲት ታሪካዊ ከተማ ስም በመጥራት፣ ‹‹የአየር ሁኔታው በጣም አሪፍ ነው›› የሚለው ጎርነን ያለው የፓይለቱ ድምፅ ሰማን፡፡

ብዙዎቹ ለከተማዋ ዕንግዶች ይመስላሉ፡፡ በመስኮት አሻግረው በቴሌቪዥን የሚያውቋቸው ሐውልቶችን እየተመለከቱ ነው፡፡ ከአጠገባቸው አንድ በግሩም ኢንጂነር የተሠራ የሚመስል ግዙፍ ቤተክርስቲያን ይታያል፡፡ የከተማዋ ስፋት እንደ ስሟ የገነነ ባይሆንም በኢትዮጵያ የቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ ከሆኑት ተጠቃሽ ናት፡፡

አሻግረው ከተመለከቱ ከቤተክርስቲያኒቱና ከሐውልቶቹ ውጪ ትንሽ ራቅ ብለው  በሰው የተሠሩ የሚመስሉ የተራራ ሰንሰለቶች ያስተውላሉ፡፡ ለቦታው እንግዳ የሆኑ ተራሮቹን ይለዩዋቸው አይለዩዋቸው ማወቅ ባይቻልም ተራሮቹ በጉልህ ተጠቅሰዋል፡፡ በታሪክ የጣልያንና የኢትዮጵያ ወታደሮች የተዋደቁባቸው እነዚህ ተራሮች በውስጣቸው አምቀው የያዙት የምዕተ ዓመት ታላቁ የዓድዋ ድል፣ የተደረገባቸው ናቸው፡፡

ማረፊያችን ከሆነችው አክሱም ከተማ በ10 እና በ15 ኪሎ ሜትር ርቀትላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በከተማዋ ከሚታዩት የታቦተ ፅዮን ውብ ቤተ ክርስቲያንና ሐውልቶች ውጪ ሰፊውን የአካባቢው አድማስ ከሰማይ አዘቅዝቆ ለሚመለከት ሰው ተራሮቹ ቦታውን ግርማ ሞገስ አላብሶታል፡፡

የያሬድ ከተማን በጨረፍታ

በአራተኛው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ከተሰየመው አውሮርላን ማረፊያ ደርሰን ወደ መውጫው አካባቢ ስንጠጋ ከርቀት የሚሰሙ ሁለት ዜማዎች ይስባሉ፡፡ እምቢልታውና ማሲንቆው በጣም ይሰማል፡፡ ከተጫዋቾቹ ሁለቱ የ‹‹ሞዓ አንበሳ›› ቅርፅ ያረፈበት ካባ ከጀርባ ጣል አድርገዋል፡፡

በአንድ እጃቸው ጎራዴ በሌላኛው ጋሻ ይዘው ይሸልላሉ፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ ከፍታ ላይ ለቆዩት ዕንግዶች የመጀመርያ እፎይታ የሰጠ መጠነኛ ትርዒት ይመስላል፡፡ ከከተማዋና ከትግራይ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ የተገኙ ኃላፊዎችም ሰላምታ እየሰጡ ዕንግዶቻቸውን ይቀበላሉ፡፡

ጥንታዊቷ አክሱም ላይ ያረፈችው የዛሬዋ አክሱም በአብዛኛው በፕላን ተስተካክላ የተሠራች በቂ መተላለፊያ ያላት ዘና ያለች ከተማ ነች፡፡ አሁን በመሠራት ላይ ያሉ ሕንፃዎች ግን ዓይን የማይማርኩና በሥነ ሕንፃ ቴክኖሎጂዎች የምትታወቀው ጥንታዊ አክሱምን፣ ስም ለማጥፋት የተሠሩ ይመስላል፡፡ አንድም የሚያምር ዲዛይን ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል፡፡

በአክሱም ቆይታችን እንደታዘብነውም የከተማዋ ዕድገት እስከዚህም ይመስላል፡፡ አልፎ አልፎ የውጭ አገር ዜጎች ይታያሉ፡፡ የአክሱምን ታሪክ የሚያስታውሱ ቅርፃ ቅርፆች የሚሸጡባቸው ሱቆች እንዲሀም የአገር ባህል ልብስ (ጥለት) ሥራዎች በብዛት ይታያሉ፡፡ አልፎ አልፎም የጀበና ቡና የያዙ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሞቅ ያለች ከተማ አይደለችም፡፡ የተዘጉ የንግድ ቤቶች ይበዙባታል፡፡ እንደ ዋነኛ የቱሪስት መስህብነቷም ሞቅ ደመቅ ያለ እንቅስቃሴ ሊታይ ቀርቶ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያ ቦታዎችና አገልግሎቶችም እንደሚጠበቀው የሚገኙበት አይመስልም፡፡

ከአየር መንገዱ የተጀመረው የባህላዊ ሙዚቃ ድግስ ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት በከተማዋ እምብርት ላይ በምትገኘውና ለከተማዋ ትልቅ ግርማ ሞገስ በምትሰጠው ዳዕሮዒላ (ትልቅ ዋርካ) ሥር የሙዚቃ ድግስ እየተጠበቀ ነው፡፡

የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው አጭር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አራተኛው የሙዚቃ በዓል በዚችው ታሪካዊ ከተማ እንዲከበር መወሰናቸው እንዲሁም ለኢትዮጵያም ብሎም ለዓለም የሙዚቃ ዕድገት ትልቁ ድርሻ ባለው በቅዱስ ያሬድ ስም በመደረጉ በትግራይ ክልል መንግሥትና በሕዝቡ ስም አመስግነው፣ ዕንግዶቹ በቆይታቸው እንዲደሰቱና የሚጎበኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ግልጽ አድርገዋል፡፡

አክሱምና ያሬድ

አክሱምን በአካል ለማያውቃት ጥንታዊ ታሪኳ ምናልባት ከሐውልቶቿ በላይ አይዘልም፡፡ የአክሱም ጥንታዊ ታሪክ ግን ከሐውልቶቹ ስርም ጭምር ነው፡፡ በጠንቃቃ ጠራቢ መሠራታቸው የሚያሳብቁት ውብ ሐውልቶቿ በቁጥር ሰባት ሲሆን፣ ትልቁና 500 ቶን የሚመዝነው ባልታወቀ ምክንያት ወድቆ ይታያል፡፡ ከተቀሩትም ዋናዎቹ ሁለት ሲሆኑ፣ አንደኛው በቅርቡ ከሮም ከስልሳ ዓመት በኋላ የተመለሰ ነው፡፡ ለሁለትና ሦስት ተቆራርጦ እንዲመጣ የተደረገው ሐውልት ነበረበት ተብሎ በጥናት በተደረሰበት ቦታ ላይ እንዲቆም የተደረገ ቢሆንም እዚሁ በቆየው ላይ አደጋ ሳያደርስበት አልቀረም፡፡ በተከላው ሒደት ላይ የመነቃነቅ ሁኔታ ስላጋጠመው እስከ ዛሬ ተጠግኖና ተደግፎ ይታያል፡፡ ድጋፉ መቼ እንደሚነሳ ለሚያቀርብ ጥያቄ ምላሽ ሰጪ የለም፡፡ ጎብኚዎቹ ገና በግቢው ውስጥ ያሉት ቤተ መንግሥትና የውስጥ ክፍሎችን ሳያዩ ሐውልቶቹን እያዩ ይገረማሉ፡፡ ከሐውልቶቹ በስተ ምሥራቅ ከወደቀው ታላቁ ሐውልት አጠገብ የሚገኘው ግዙፍ አለት ሥር ግን ምን እንዳለ ገና ምርምር ያልተደረገበት ስፍራ አሾልኮ (አሻግሮ) ማየት ይቻላል፡፡

ምንም የረባ አጥር እንኳን አልተሠራለትም፡፡ ከግቢው በስተደቡብ የቆርቆሮ በር ገንጠል እያደረግን ነበር እኛም የገባነው፡፡ የረባ ፍተሻም የለም፡፡ ብዙዎቹ በዚህ ሳይደመሙ አልቀሩም፡፡ በእርግጥ መግቢያው አካባቢ በቅርበት የሚከታተሉ የታጠቁ ጠባቂዎች ይታያሉ፡፡

ለሁለት የተከፈለው የጎብኚ ቡድን፣ በሁለት አስጎብኚዎች ማብራርያ እየተሰጠው በሁለት አቅጣጫ እየጎበኘ ነው፡፡ በስተደቡብ የአጥሩ ጥግ ሲሄዱ የውሸት በር (False Door) የሚባል መዝጊያ ቆሞ ይታያል፡፡ ይህንን በዓለም በተለያዩ በሮች ቅርፅ የሚታየው ግማሽ ክብ ቅርጽ ያለው በመጀመርያ እዚሁ መፈልሰፉ ይነገራል፡፡

አስጐብኚው በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ሳንቲም ላይ የራስን ምስል በማድረግ የመገበያያ ገንዘብ የዘየዱት ስማቸውን እየጠየቀሰ ምስሎች ያሳየናል፡፡ ሳንቲሞቹ ላይ የሚታየው ቅርፅ በዘመናችን የተሠራ እንጂ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ በፊት እንዲህ ዓይነት ጥበብን ለማመን የሚከብድ ነው፡፡

የሚረግጡት ግቢው ሙሉ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ በስተደቡብ ቆሞ በሚታየው የውሸት በር በሚባለው በር አልፈው ደረጃዎች ወርደው፣ በሌላ በር ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ግን ለማመን ይገደዳሉ፡፡

ንጉሦቹ በስማቸው፣ በቁመታቸውና በጎን ስፋታቸው ልክ ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ ውብ የሬሳ ማስቀጫዎች ይመለከታሉ፡፡ በርካታ የተከፋፈሉ አንድ ዓይነት መጠንና ቅርፅ ያላቸው ውብ ክፍሎችም ይምለከታሉ፡፡ ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ ውብ የሬሳ ሳጥኖች ያሉባቸው ክፍሎች ግን ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌለው ወርቅና አልማዝ እንደነበርና በጦርነቱ ጊዜና በአጥኚዎቹ ሳይዘረፍ እንዳልቀረ አስጎብኚዎቹ ያብራራሉ፡፡

ተአምር በሚመስሉ ቅርፃ ቅርፅና ውቅር ድንጋዮች፣ ብዙዎቹን የሚገርመው በየትም ቦታ ምንም መዛነፍ (Almost No Error) የማይታይ ሲሆን፣ ይኼ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ጐብኚው ሲገረም ሳለ አስጎብኚያችን አንድ ነገር ያሳየናል፡፡ በወቅቱ አክሱማዊያን ይጠቀሙበት የነበረውን ሜትር፡፡ ይኼው ትንሹ መለኪያ እምብዛም ብዙ ሰው ልብ የማይለው ረግጦት ሊያልፈው የሚችል ነው፡፡ በዚህ ከተገረሙ መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተመራማሪ ዶ/ር ብርሃኑ ግዛው አንዱ ነበሩ፡፡ ‹‹ይኼ ግሩም ነገር ነው›› ይላሉ፡፡ ከአጠገቡ ደግሞ እነዚህ ረዣዥም ድንጋዮች ተፈልፍለው ‹‹ህድሞ›› የሚመስሉ ቤቶች የተሠሩባቸው ድንጋዮች እንዴት እስከ ዛሬ ይቆያሉ በማለት የጀርመን ሳይንቲስቶች ሲያጠኑ፤ ንጣፍ ድንጋዮቹን አንዱ ከሌላው የተያያዙበት የቀለጡ ብረቶች አግኝተዋል፡፡

አስጎብኚያችን ይህንን የሚታይበት ስፍራ የወሰደን ሲሆን፣ በዚህም እጅግ ጠንካራ የሚባሉት እነዚህ የግራናይት ድንጋዮች ለመጥረብ የተጠቀሙበት የብረት ዓይነት እስከ ዛሬ ማግኘት ያልተቻለ ቢሆንም፣ ብረትን በየዓይነቱ ያቀልጡ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ፡፡

እንዲህ እንዲህ እየተዘዋወርን እየተገረምን በዘመኑ የተገኙት ቅርፃ ቅርፆችና የቤት ቁሳቁሶች የሚገኙበት ሙዚየምም ጎብኝተናል፡፡ በእያንዳንዱ ንጉሥ ጊዜ የተሠሩ ጌጦችና ሌሎች ይመለከታሉ፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ታሪክን ይመለከታሉ፡፡

አስጎብኚያችን እንደነገረን ቆመው በየቦታው የሚታዩ ሐውልቶች የኃያላን የአክሱም ንጉሦች መቃብር ምልክት ሲሆኑ፣ ሐውልቶቹን የሚያሠሩዋቸው በራሳቸው በንግስና ዘመን እንደነበረም ነግሮናል፡፡ የሐውልቶቹ ግዙፍነትም የሚያሠራው ንጉሥ የግዛት ኃያልነት እንደሚያመለክት ይነገራል፡፡ የአክሱም ዘመነ መንግሥት የተመሠረተበት ዘመን በውል የማይታወቅ ቢሆንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 1000 ዓ.ዓ. በንግሥተ ሳባ እንደተቆረቆረ ይነገራል፡፡ በተለይ ከአራተኛው ክፍለ ዘመንም በዓለም ኃያላን ከሚባሉ ሦስት ግዛቶች መካከል እንደነበር መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ እስከ ዛሬ የተጠናው ግን አምስት ፐርሰንት መሆኑና ገና ብዙ ያልተገለጸ ምስጢር እንዳለ አጥኚዎበች ይገምታሉ፡፡  

ቅዱስ ያሬድ የተገኘው በዚሁ የአክሱም ዘመነ መንግሥት የላቀ ከፍታ ላይ በነበረበት በአምስተኛ ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ለአክሱም የባህልና የሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ይገለጻል፡፡

ጥናታዊ ምርምሮችና የቅዱስ ያሬድ ዜና መዋዕል እንደሚገልጹት፣ ቅዱስ ያሬድ የተወለደው መጋቢት 14 ቀን 497 ዓ.ም. በአክሱም ከተማ ሲሆን፣ 60 ዓመት በሕይወት ከቆየ በኋላ ግንቦት 11 ቀን 563 ዓ.ም. አርፏል፡፡

ቅዱስ ያሬድ የተወለደው የአክሱም ኃያላን ነገሥታት መካከል ከሆኑት በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡    

ከአክሱም በስተሰሜን የሚገኘው የአፄ ገብረ መስቀል ቤተ መንግሥትን የጎበኘን ሲሆን፣ ከሌሎች በተለየ ይኼው ቤተ መንግሥት ምንም ፍርስራሽ የሌለበትና በነበረበት የሚገኝ ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ ኮረብታ ላይም በመሆኑ እምብዛም አልተደፈነም፡፡ ከፍተኛ ቁፋሮ ማድረግም አላስፈለገም፡፡ ይኼው ገና በመጠናት ላይ ያለው ቤተ መንግሥት ከሌሎች በተለየ ሙዚቃና ማህሌት ሲደረግበት የነበረው ስፍራ በዘመኑ እንደየዛሬው የኳስ ሜዳ ዕንግዶች ተቀምጠው የሚመለከቱበት ስፍራም ይገኝበታል፡፡ በዚሁ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሐውልቱ ዙርያ የታዘብነውን ዓይነት ክፍልፍል ያለ ሲሆን፣ 17 ደረጃዎች ተወርዶ የሚገኝ ነው፡፡ ሕንፃው እምብዛም የደረሰበት ጉዳት ስለሌለ ለጥናት አመቺ የሆነ ይመስላል፡፡ የጀርመን ተመራማሪዎች ጥናት እየሠሩበት ይገኛል፡፡ ከዘመኑ ሲሚንቶ ተመሳሳይነት ያለው ነገርም ይስተዋላል፡፡

ያሬድና ማይከራሕ፡-

ከአክሱም ሳንወጣ በመጨረሻ ቅዱስ ያሬድ ትእምርት ያየበት ስፍራ የተጓዝን ሲሆን፣ ከዚሁ ከአፄ ገብረ መስቀል ቤተ መንግሥት በስተምሥራቅ ትንሽ ወረድ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለረዥም ጊዜ ትምህርት  አልገባ ብሎት፣ በተደጋጋሚ የተባረረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ተስፋ ቆርጦ ለመጥፋት ሲጓዝ አንድ ስፍራ የምትገኝ ዛፍ ጥላ ስር ዕረፍት ያደርጋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እንደተላከች የሚታመንባት አንዲት ትል ወደ ዛፉ ለመውጣት ሰባት ጊዜ ሞክራ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ተሳክቶላት ስትወጣ ዓይቶ ትምህርት መውሰዱ ይነገራል፡፡ ከዚያ በኋላ ተመልሶ ትምህርቱን በመከታተል ታላቅ ሊቅና የሙዚቃ ፈላስፋ ለመሆን በቅቷል፡፡ ግእዝ፣ እዝልና አራራይ የተባሉት የዜማ ዓይነቶችን መፍጠሩም ይታወቃል፡፡ ንጉሥ ገብረ መስቀልም፣ በያሬድ ሥራ እጅግ መደነቁ ይነገራል፡፡

ያሬድ ይህንን ትምህርት ያገኘበት ስፍራ የነበረው ዛፍ ዘር እንደሆነ የሚታመንበት ግዙፍ ዛፍ አሁንም የሚገኝ ሲሆን፣ በሥሩም ነዋሪው ከተለያዩ በሽታዎች የሚፈወስበት ፀበል ይገኝበታል፡፡ በቦታውም ቤተክርስቲያን የሚገነባ ይሆናል፡፡ አስጎብኚው ስለ ቅዱስ ያሬድ ሲያብራራልን፣ ‹‹በ60 ዓመቱ ሞተ›› የሚለውን በመቃወም በስሜት ምላሽ የሰጡ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ‹‹ተው ተው አልሞተም፤ ማነው እንደሱ ያለህ?›› በማለት ገስጸውታል፡፡ የሚባለውም ‹‹ተሰወረ›› ነው፡፡  

ታሪካዊውን የይሓ ግንብ ጎብኝተን ወደ ዓዲግራት ያመራን ሲሆን፣ በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደማቅ አቀባበል ተደርጎልናል፡፡ ከአዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ስኬታማ መሆኑን በመንግሥት የታመነበት ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዓለም መሥራቱ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው ስኬትም ብዙዎቹ ተደስተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኪነጥበብ ቡድንም ዝግጅት ቀርቧል፡፡ በገዛ ገርላስ ባህላዊ ምግብ ቤት ለዕንግዶች ዝግጅት ያደረገልን ይኸው ዩኒቨርሲቲ፣ በአካባቢው በቅድመ አክሱም የነበረውን ሥልጣኔ ለማጥናት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተገልፆልናል፡፡ አንዳንድ በቁፋሮ የተገኙትንም ጎብኝተናል፡፡

ዓዲግራት ከመድረሳችን በፊት የደብረ ዳሞ ገዳምን የጐበኘን ሲሆን፣ ጥቂቶች በገመድ ታስረው በመውጣት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ክርስትናን ካስፋፉ ዘጠኙ ቅዱሳን መካከል አንዱ የሆኑት አቡነ አረጋዊን ፀበል ተካፍለዋል፡፡

መቐለ ከመድረሳችን በፊት በውቅሮ የተከፈተውን አዲስ ሙዚየም የጎበኘን ሲሆን፣ እዚህ ውስጥም በምርምር ከአክሱም ሥልጣኔ በፊት መሠራታቸውን የተረጋገጠ እጅግ ድንቅ የሆኑ መሰውያና የንግሥቲቱ በርካታ ጌጣጌጦች ተመልክተናል፡፡

ዕንግዶች በተመለከቱት እጅግ የተደነቁ ሲሆን፣ በመቐለ ከተማ አክሱም ሆቴል በተደረገው የማጠቃለያ ዝግጅት ታዋቂው የማስታወቂያ ባለሙያ ውብሸት ወርቅአለማሁ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ግዛው፣ ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ እንዲሁም ሰርፀ ፍሬስብሐት በቅዱስ ያሬድ የትውልድ ዘመን፣ ትክክለኛ ስሙና አማሟትና የመሳሰሉ ውዝግቦችን አስመልክተው ተወያይተዋል፡፡ በቂ ጥናት እንዲደረግበትም መክረዋል፡፡ ውብሸት ‹‹በሕይወት ዘመኔ በትምህርት ካገኘሁት ሁሉ ዛሬ ተዘዋውሬ ያየሁት ይበልጣል›› ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል በቅርስ አያያዝና ምርምር በማድረግ ዙሪያ ከዚህ በበለጠ እንዲሠራ አስተያየቶች ተሰንዝሯል፡፡ ምርምሮቹ ከውጭ አገር ተማራማሪዎች ጥገኝነት እንዲላቀቁና በኢትዮጵያውያን ምርምር እንዲደረግም ጠይቀው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ ለዚሁ ዝግጅት አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ መቐለ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ትብብር ያደረጉ ሲሆን፣ በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ ከመካከላቸው ሞገስ ተካ፣ ግርማ ተፈራ፣ ቴዎድሮስ መኰንን (ቴዲ ማክ)፣ ፀደንያ ገብረማርቆስ እና  በተለምዶ ቱፓክ የሚባለው ማሲንቆ ተጨዋች እንዲሁም ኪሮስ ኃይለሥላሴ፣ ገብሩ ፋኖን ጨምሮ በርካታ የትግርኛ ዘፋኞች ተገኝተዋል፡፡     

የአልባብ ፕሮሞሽን ባለቤት አቶ ተስፋዓለም ተአምራትና የኢራ ፕሮሞሽን ባለቤት አቶ ኃይላይ ታደሰ ዝግጅቱን ካስተባበሩት መካከል ነበሩ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...