የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ክራውን ሆቴልና ክራውን ፕላዛ በሚለው መጠሪያ ስያሜና የንግድ ምልክት ላይ ምርመራ አድርጎ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ፣ በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ተወስኖ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የፀናው ውሳኔ እንዳይፈጸም የሰጠው ውሳኔ ‹‹ተጥሷል›› በሚል ማመልከቻ ቀርቦለት ሌላ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
ሰበር ሰሚው ችሎት ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. የሰጠው የእግድ ትዕዛዝ መጣሱን በመግለጽ ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ለችሎቱ አቤቱታ ያቀረበው ክራውን ሆቴል ነው፡፡
የሆቴሉ ባለቤት ወ/ሮ ዘውዲቱ መስፍን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ ክራውን ሆቴልንና ክራውን ፕላዛን በሚመለከት ለሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበው አቤቱታ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ያስቀርባል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚው ችሎት መርምሮ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይፈጸም ታግዶ እንዲቆይ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በተለያዩ ጊዜያት ቀጠሮ እየተሰጠ ቢሆንም፣ ተለዋጭ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ለአምስተኛ ጊዜ ለሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቶ እየተጠባበቁ መሆኑን በማመልከቻቸው ላይ አብራርተዋል፡፡
ሰበር ሰሚው ችሎት ወደፊት ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ትዕዛዝ መስጠት አለመስጠቱ ወይም ተጨማሪ ቀጠሮ መስጠት አለመስጠቱ ሳይታወቅ፣ CROWNE PLAZA (ክራውን ፕላዛ) የሚባለውን ስምና የንግድ ምልክት የማስተዳደር ውል፣ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ (Six Continents Hotels Inc) ጋር መዋዋሉን የሚገልጸው ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠውን የእግድ ትዕዛዝ መጣሱን ክራውን ሆቴል ያቀረበው ማመልከቻ ያስረዳል፡፡
ፀሜክስ ሆቴሎችና ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በልደታ ክፍለ ከተማ ልደታ ኮንዶሚኒየም የጋራ ቤቶች መሀል ላይ እያስገነባ ባለውና ክራውን ፕላዛ ተብሎ ይጠራል በሚባለው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ፕሮጀክት ውስጥ፣ ለአብነት የሠራው ክፍል (MOCKUP ROOM) ሰኔ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚያስመርቅና ለሆቴሉ አስተዳደር እንደሚያስረክብ በመግለጽ፣ የክራውን ፕላዛን የንግድ ምልክትና የፀሜክስን የንግድ ምልክት በመጠቀም፣ ለተጠሪዎች ደብዳቤ መበተኑን በመጠቆም፣ ድርጊቱ ሕገወጥና የፍርድ ቤቱን የእግድ ትዕዛዝ የጣሰ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚው ችሎት ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የፈጸመው የፍርድ ቤት እግድን የመጣስ ሕገወጥ ተግባር በአፋጣኝ እንዲያስቆምለት ክራውን ሆቴል ማመልከቻውን ለሰበር ሰሚው ችሎት አቅርቧል፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ክራውን ሆቴል ያቀረበውን ማመልከቻ የተመለከተው ችሎቱ፣ ሲክስ ኮንቲኔንትስ ሆቴልስ ኢንክና ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ክራውን ሆቴል ባቀረበው አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ አዘጋጅተው ሰኔ 20 ቀን 2008 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ሁለቱ ተከራካሪዎች ውዝግብ የጀመሩት በ2005 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራበት ክራውን ፕላዛ የሚለውን የንግድ ምልክት እንዲመዘገብለት፣ ለኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ያመለክታል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የተጠየቀው የንግድ ምልክት በጽሕፈት ቤቱ ተመዝግቦ ከሚገኘው ፕላዛ ሆቴል ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመግለጽ፣ ጥያቄውን ወድቅ አድርጎታል፡፡ ቀጥሎ ፀሜክስ ሆቴሎችና ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በአዲስ አበባ ሊገነባ ላቀደው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የንግድ ምልክትነት ክራውን ፕላዛ እንዲመዘገብለት ያቀረበውን ጥያቄ፣ ጽሕፈት ቤቱ ተቀብሎ የንግድ ምልክቱን መጠቀም እንደሚችል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ክራውን ሆቴል የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረበው የይግባኝ ክርክር ተቀባይነት አጥቶ የጽሕፈት ቤቱ ውሳኔ ፀንቷል፡፡ ክራውን ሆቴል በጽሕፈት ቤቱና በፍርድ ቤቱ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል በማለት ሰባት መሠረታዊ የሕግ ጥሰቶችን ገልጾ በዝርዝር በማስረዳት፣ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ የሥር ፍርድ ቤቱ ውሳኔዎች ታግደው እንዲቆዩ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡