በስድስት የተለያዩ መጠለያ ካምፖችና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት በመደገፍና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኤርትራ መንግሥት ላይ የተጠናከረ ጫና እንዲያሳርፍ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሠልፍ አካሄዱ፡፡
አዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከገነት ሆቴል ተነስተው ወደ አፍሪካ ኅብረት በማምራት የኮሚሽኑን ውሳኔ በመደገፍ ድምፅ ያሰሙ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት በኤርትራ መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሠልፈኞቹ በሠልፉ ወቅት ‹የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደግፋለን›፣ ‹ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ይቀረቡ›፣ ‹ስደትና ሞት ይብቃ› የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማሰማት በአፍሪካ ኅብረት መግቢያ በር ላይ ሠልፋቸውን አድርገዋል፡፡
ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ዶ/ር ንኩሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ እሳቸው ለሥራ ከአዲስ አበባ ውጭ በመሆናቸው የኅብረቱ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊነትና የስደተኞች ጉዳዮች ተወካዮች በጽሑፍ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብለው ለኮሚሽነሩ እንደሚያደርሱ ቃል ገብተዋል፡፡
ሠልፈኞቹ መፈክሮችን ከማሰማት በተጨማሪ በኤርትራ እየደረሰ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዜጎች አያያዝ ሁኔታ የሚያሳይ ድራማም አቅርበዋል፡፡
በሠልፉ ላይ የተሳተፉት ሠልፈኞች በአብዛኛው ወጣት ወንዶች ሲሆኑ፣ ቁጠራቸው መጠነኛ የሆኑ ሴቶችና የዕድሜ ባለፀጎች እንዲሁም ጥቂት ሕፃናት የሠልፉ ተካፋዮች ነበሩ፡፡
በሠልፉ የተሳተፉት አቶ በሽር ኢስሃቅ የተባሉ ኤርትራዊ ለሪፖርተር ‹‹የዛሬው ሠልፍ ዓላማ የኮሚሽኑን ሪፖርት ለመደገፍና በኤርትራ መንግሥት ላይ ግፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጩኸታችንን ሰምቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ነው የምንፈልገው፣ ከሪፖርቱ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኢሳያሳይ ለዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ እንዲቀርቡ የምናደርገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍና ድምፃችንን ለማሰማት ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
የተመድ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ማለቱና የፖለቲካና መሪዎችም ጉዳያቸው ለዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲታይ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡