Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመዲናችን ጎዳናዎችና የእንፉቅቅ ጉዟችን

የሥራ ነገር ሆኖ በየቀኑ ከአንደኛው የአዲስ አበባ ክፍል ወደ ሌላኛው መንቀሳቀስ ግድ የሚሆንብን በርካታ ነዋሪዎች አለን፡፡ ከመኖሪያ ቤት ተነስቶ ወደ ቢሮ ወይም የዕለት ሥራ ወደሚከናወንበት ሥፍራ መጓዝ የዘወትር ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖ እኔና መሰሎቼ በምናደርገው እንቅስቃሴ አንጀታችንን ባያርሱም አልያም በአገልግሎታቸው ባንረካም ከተማዋ ያፈራቻቸውን የተለያዩ የመጓጓዣ አማራጮች እንጠቀማለን፡፡

እንደ ሁኔታው ታክሲ፣ አውቶብስና ባቡር እንጠቀማለን፡፡ በመሥሪያ ቤት መኪናም እንቀሳቀሳለን፡፡ አንዳንዴም ታክሲ ተኮናትሮ የዕለት ሥራን መከወን   ግድ የሚልባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ በዚህ የዘወትር እንቅስቃሴያችን የከተማችንን የትራንስፖርት እንቅስቃሴና ጥቅል ባህሪይ በተወሰነ ደረጃ  እንድናውቅ ዕድል ይሰጠናል፡፡

ከዘወትር ተገልጋይነታችን አንፃር መቼና በየትኛው ቦታ መደበኛ ታክሲ መጠቀም እንዳለብን በተወሰነ ደረጃ ግንዛቤ ያገኘን ደንበኞች አንጠፋም ብዬ አምናለሁ፡፡ ለከተማችን እንግዳ በሆነው የቀላል ባቡር አገልግሎት መጠቀም አዋጭ የሚሆንበትን ጊዜ በተወሰነ ደረጃ ለመረዳት ጥረት ማድረጋችንም አይቀርም፡፡ አንዳንዴ ለአጭር ጉዞም ቢሆን ያለኮንትራት ታክሲ መጓዝ የማይቻልበት መስመር እንዳለም በተገልጋይነታችን ሒደት የምንረዳበት አጋጣሚ ፈጥሮልናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ባህሪያት በማጥናት የተሻለ ይሆናል የተባለውን አማራጭ በመጠቀም በአፋጣኝ ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ እንሞክራለን፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንልኝም በአዲስ አበባ ከተማ በየትኛውም መስመር ዘወትር ሰኞ ቀን የሚፈጠረው የትራንስፖርት ችግር እንዳያውከኝ በማሰብ ማልዶ ከቤት መውጣት ብቸኛ አማራጭ ካደረጉ ተገልጋዮች አንዱ ነኝ፡፡ እንዲህ ማድረግ ካልተቻለ የሰኞ ሥራ አጓጉል ይሆናል ማለት ነው፡፡

ለማንኛውም ስለ አዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርትና በመንገድ ማኔጅመንት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመምዘዝ መናገር ይቻላል፡፡ ይሁንና ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ እየታየ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ከዚህ ቀደም በመፍትሔነት ስጠቀምባቸው የነበሩ ዘዴዎችን ፉርሽ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ችግር የእኔ ብቻ ሳይሆን የግል ተሽከርካሪ ላለውም  በሕዝብ በትራንስፖርት የሚገለገለውም ነዋሪ ራስ ምታት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በተለያዩ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በመጠቀም ልምድ ያለን ሰዎች የሰሞኑ የትራፊክ ጭንቅንቅ አሳስበናል፡፡ ፈታ ያለ የትራፊክ ፍሰት ይታይባቸው የነበሩ መስመሮች ሳይቀሩ በአነስተኛና ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ተሞልተው፣ እንቅስቃሴያቸው የኤሊ ሆኖ በተፈለገው ሰዓትና ከተፈለጉበት ቦታ መድረስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በእንፉቅቅ የሚደረገው ጉዞ እንደቀድሞ  ጊዜ የማይመረጥ ሆኗል፡፡ በከተማዋ አደባባዮች ላይ እየታየ ያለው መጨናነቅ ብሶበታል፡፡ ለወትሮ በአሥር ደቂቃ መድረስ የሚቻልባቸው ቦታዎች ዛሬ በአንድ ሰዓት ከተደረሰ ዕድለኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡

በዚህ ላይ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ውኃ የሚቋጥሩት የከተማዋ መንገዶች ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እያረጉት ኑሯችንን አክብደውታል፡፡ ለመኪና መንሸራሸሪያነት የተሠሩት አንዳንድ ጎዳናዎቻችን ውኃ የማቆር ሥራ እንዲሠሩ የተበጁ አስመስሏቸዋል፡፡ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ እየተመለከትን ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ትዕግሥትን ያስጨርሳል፡፡ በዝናብ የሚታጀቡት መጪዎች ወራቶች ሲታሰቡ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ሊባባስ እንደሚችል እንገምታለን፡፡

የከተማዋን መንገዶች ጭንቅ ጥብብ የሚያደርገው ከዝናብ ጋር የተያያዘው ችግር ግን አሁን የመጣ ሳይሆን ለዓመታት የዘለቀ ነው፡፡ መፍትሔ ሳይበጅለትም ይኸው እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡

ችግሩ እየባሰበት ቢመጣም መፍትሔ ሊገኝለት አለመቻሉ ያሳዝናል፡፡ ውኃ የሚያቁሩ መንገዶች ያሏቸው የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ከሥራ ውጭ መሆኑ እየታወቀ መላ የሚያበጁ ባለሙያዎች ወይም አስፈጻሚዎች በአገር እስኪመሰል ድረስ ተዘንግተዋል፡፡ በጊዜያዊነትም ቢሆን መፍትሔ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት የለም ያስብላል፡፡

ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ውቅንቅጡ መጥፋት ሌሎች ምክንያቶችንም መዘርዘር የሚቻል ሲሆን፣ መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው በአንዳንድ መንገዶች ላይ የተተከሉት የትራፊክ መብራቶች ሳይቀሩ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ነገሩን እያባባሱት መሆኑን እየመለከትን ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን ያሳልጣሉ ተብለው የተተከሉት የትራፊክ መብራቶች ተሽከርካሪዎችን እንዳመጣጣቸው ከማሳለፍ ይልቅ አጋች የመሰሉት ቀይ መብራቶቻቸው ማሳለጥን የረሱ ይመስላሉ፡፡ አንድ ወይም ሁለት መብራት ለማለፍ ከአሥር እስከ ሃያ ደቂቃዎች ቆሞ መጠበቅ ግድ እየሆነ ነው፡፡ ሲከፋም ቆሞ መጠበቁ ከዚያ በላይ ሊረዝም ይችላል፡፡

አንዳንዶቹ  ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር የተያያዙ ችግሮች በጥሩ የትራፊክ ማኔጅመንት የሚፈቱ ቢሆኑም፣ የትራፊክ መጨናነቅን ለማርገብ የከተማዋ ትራፊኮች አገልግሎት አሰጣጥም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል፡፡

ከተማዋ እንዲህ ያለ የትራፊክ መጨናነቅ እየታየባት ቢያንስ ችግሩ በሚብስባቸው አካባቢዎች የትራፊክ ፖሊሶቻችን ተሽከርካሪዎች ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲስተናገዱ የሚያደርጉት ጥረት እየደበዘዘ በመሆኑ ለችግሩ መባባስ አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡ እኔ እስከሚገባኝ የትራፊክ ፖሊሶቻችን አንዱ ሥራ ይህ ቢሆንም አሽከርካሪዎች ከሥርዓት ውጭ ለመጨናነቁ ምክንያት ሲሆኑ የሚቆጣጠራቸው መጥፋቱ ትልቅ ችግር ሆኗል፡፡ ጉልበተኛው መንገድ ይዘጋል፡፡ ለውጥረቱም መባባስ ምክንያት ሲሆን ሃይ የሚለው ስሌለ ችግሩ ብሶ ይገኛል፡፡

ስለዚህ በአንዳንድ መስመሮች ላይ የትራፊክ ፖሊሶችን በተለይ መጨናነቅ የሚታይባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት  ቁጥጥር የማድረጉ ልምድ ሊታሰብበትና ቸል ሊባል የማይገባው ነው፡፡  ዘላቂ መፍትሔ ባይሆን እንኳ የከተማዋን የትራፊክ ችግሮች በመከታተል በሚዲያዎች መረጃ የመስጠት አሠራር ቢዘረጋ፣ ካለም ቢጠናከር መልካም ነው፡፡ ይህ መረጃ ከትራፊክ ፖሊሶች አገልግሎት ጋር ተያይዞ መሠራት ይኖርበታል፡፡

መጨናነቅ ያለበት ቦታ የቱ አካባቢ እንደሆነ በሚዲያ ገልጾ  ተሽከርካዎች አማራጭ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይበጃል፡፡ ይህም ሲሆን የትራፊክ ፖሊሶችን የማስተናበር ሥራን ያግዛል፡፡ ጭንቅንቁ አሽከርካሪዎችን ትዕግሥት የሚያሳጣ ስለሚሆን ተሽቀዳድሞ ለውጣት በሚደረግ ጥረት እንቅስቃሴውን የበለጠ እያቆላለፈው ስለሆነ የግድ የትራፊኮችን መኖር ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በየሰዓቱ  የከተማዋን ትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያሳይ፣ መረጃ የሚሰጥና ራሱን የቻለ ሬዲዮ ጣቢያ እያስፈለገን ነውና የተሻለ መፍትሔ እስኪመጣ እንዲህ ያሉ መፍትሔዎቻችንን በመቀጠም ተገልጋዩን መታደግ ያሻል፡፡

በአጠቃላይ የከተማችን መንገዶች ከሚገባቸው በላይ ተሽከርካሪዎችን እየተሸከሙ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ እየሆኑ ነው፡፡ አሁን ከምናየው ችግር አንፃር ቀጣዩ ጊዜ ከዚህም የከፋ እንደሚሆን ነው የአዲስ አበባ መንገዶች በየቀኑ የከተማዋን መንገዶች ከማቀላቀሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች አንፃር ተሰልቶ መንገዶች እየተሠሩ ባለመሆኑ ችግሩ የሁሉም ሆኗል፡፡

በጥቅል ሲታይ የአዲስ አበባችን ጎዳናዎች ዘና ብለን የምንጓዝባቸው እስኪሆኑ ድረስ የእንፉቅቅ ጉዟችን የሚያስከፍለን ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ የሚቃጠለው ጊዜና የሚጠፋው ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ በአንድ ሊትር በአማካይ አሥር ኪሎ ሜትር መሄድ እየተቻለ የእፉቅቅ ጉዞው ለአሥር ኪሎ ሜትር ጉዞ ከሁለት ሊትር በላይ እየጠየቀ መሆኑ ሲታሰብ፣ የሚባክነውን ነዳጅ ስናሰላ ማሳለጥ ያልቻልነው የትራፊክ እንቅስቃሴ ምን ያህል እዳከሰረን እንረዳለን፡፡ ችግሩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ስለሚያስከትል ከልብ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት