Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአልገባኝ ያለው የተመጣጠነና ያልተመጣጠነ የኃይል አጠቃቀም ነገር

አልገባኝ ያለው የተመጣጠነና ያልተመጣጠነ የኃይል አጠቃቀም ነገር

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የአገራችን ነባር ችግር ባለው ሥርዓት ውስጥ ሽፍጦች የሚታረሙበት አሠራር መጥፋቱ ነው፡፡ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ የምርጫ፣ የዳኝነት፣ የመንግሥት የቁጥጥር (ሬጉላቶሪ) አካላት ችግር መዋቅራዊ ነው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ምናልባትም ለመጀመርያ ጊዜ በ1966 ዓ.ም. (በልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜ) በሰኔ ወር የመርማሪ ኮሚሲዮን የተቋቋመው ሥርዓቱ መነቅነቅ፣ መነቃነቅ፣ መንቃትና መሰነጣጠቅ ጀምሮ ከዋለ ካደረ በኋላ ነው፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ከመጣ በኋላ እንዲህ ዓይነት ቀልድ አገር ያበላሻል ተብሎ ታወጀ፡፡ ደርግ የወሰደው ከዚህ ጋር የተያያዘ የመጀመርያው ዕርምጃ የመርማሪው ኮሚሲዮን ተመርማሪዎች የነበሩትን በሙሉ ከሌሎች ተደማሪ ‹‹ዕድለቢሶች›› ጋር መረሸን ነበር፡፡ የመርማሪ ኮሚሲዮኑም ፈረሰ፡፡ ኮሚሲዮኑ የተቋቋመው ለተወሰነ ጊዜ (ለሁለት ዓመት) ቢሆንም የፈረሰው ግን ተልዕኮውን ጨርሶ ሳይሆን ተልዕኮው አያስፈልግም ተብሎ ነው፡፡

የደርግ መንግሥት የመርማሪው ኮሚሲዮን ባለጉዳዮችና ተመርማሪዎችን በ‹‹አብዮታዊ ዕርምጃ›› ያስወገደው ያለ ሕግ፣ ያለፍርድና እብሪቱ የመራውን የዘፈቀደ ውሳኔ ተከትሎ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ‹‹ያለፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ የመውሰድ›› ድርጊት ዛሬ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር በሰብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል ይባላል፡፡ ክስ ማቅረብ በይርጋ የማይታገድበት፣ ይቅርታም ሆነ ምሕረት የማይደረግበት ወንጀል ነው፡፡ ይህ ድርጊት ራሱ በፍርድ ቤት የታየው በሽግግሩ ዘመን በተቋቋመው ልዩ ዓቃቤ ሕግ ከሳሽነት ነው፡፡ ከሥርዓት (ከመንግሥት) መለወጥ በኋላ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከ17 ዓመት በኋላ፤ ከዚያም ወዲህ ብዙ ጊዜ በቀጠሮ አድሮ የተመሠረተው ክስና፣ የተሰጠው ውሳኔ የልዩ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚለው ከሌሎች መካከል እንደዚያ ዓይነት ወንጀሎችን ‹‹ለመጪው ትውልድ በሀቀኛ መንገድ መዝግቦ ማቆየትና ዳግም የዚያን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም ማስገንዘብና ማስተማር…›› የቻለ ይህን የመሰለ ‹‹ትክክለኛ ታሪካዊ ግዳጅ›› የፈጸመ ስለመሆኑ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 28 እንደተደነገገው ያለፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ የመውሰድ ድርጊት በሰብዕና ላይ የሚፈጸም ብርቱ ወንጀል ነው፡፡ በይርጋ ሕግ እንዲሁም በምሕረትና በይቅርታ ሕግ የማይገዛ ወንጀል ነው፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለ ያለሕግና ያለፍርድ ግድያን ወንጀል አድርጎ የማቋቋም፣ የመከላከል፣ ተፈጽሞ ሲገኝም የማጣራትና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለፍርድ የማቅረብ፣ ተበዳዮችን የመካስ፣ ድርጊቱ ዳግም እንዳይፈጸም ማድረግ የሚያስችል ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡

በደርግ ዘመን በአገሩ ሁሉ የሚያዝዘው እስከ ቀበሌ ድረስ ዝቅ ብሎ በተዋቀረው አስተዳደር የተሰገሰገው የታጠቀ ኃይልና በሱ ላይ ማዘዝ የሚችል ሁሉ ነበር፡፡ መድረሻ ለማሳጣት፣ ድራሽ ለማጥፋት ‹‹በለው በለኝና…›› ማለት እንኳን የቀረበት፣ ‹‹ገድሏል፣ ገድሏል ዝናሩ ጎድሏል›› ማለት ብሔራዊ መዝሙር የነበረበት ‹‹ገዳይ እወዳለሁ ተኳሽም አልጠላ!›› ብሎ ሙገሳ የጦር ግንባር ወግ ብቻ መሆኑ የቀረበት ዘመን ነበር፡፡

ድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ ይህንን ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቀረት፣ ከዚህ ሁኔታ ጋር ጨርሶ መቆራረጥ ነበረባት፡፡ ብዙ ችግር የነበረበትን በተወራውና በተፈራው አንፃር ደግሞ አገሪቷን ከምጥ የገላገላትን (እንደተፈራው ያለ እልቂት አልነበረም) የግንቦት 20 ሰሞንና የተከታዩን የ‹‹ሰላምና መረጋጋት›› ወቅት እንኳን ብናይ የ1984 የላንጌንና የወተርን ‹‹ጭፍጨፋ›› አለዚያም ግድያ እናገኛለን፡፡ ወተር ላይ ኦነግ ባነሳሳው ቁጣ ብዙ ሰው ተገደለ፡፡ ኦነግ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጩኸቱን ያደመቀበት፣ ኢሕአዴግ ደግሞ በሰልፈኛው ውስጥ ኦነግ ታጣቂዎቹን አስገብቶ በማስተኮስ ጉዳት እንዲደርስ አደረገ የሚል ማመሀኛ፣ መከላከያና መከራከሪያ ሰጥቶ እጄ ንጹህ ነው ያለበት ግድያ ነበር፡፡

የግንቦት 20 አንደኛው ዓመት በተከበረበት ሰልስት የበደኖን ዕልቂት ለማጣራት በሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት የተሰየመው ኮሚት ውሳኔ፣ ከግንቦት 25 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የምክር ቤቱ ውይይትና ውሳኔ በተከታታይ ቀርቦ ሲሰማ እንደ ተረዳነውና እንደተመዘገበው ያለሕግና ያለፍርድ ግድያና የኃላፊነት ወይም የተጠያቂነት ጉዳይ ለፈተና የቀረበበት የመጀመርያው ድኅረ ደርግ አጋጣሚ ነበር፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት በመደበኛ ውሳኔ ያቋቋመው የአጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ ሲቀርብ ኦነግ በዋነኛነት የበደኖን በደልና ግፍ ወደ ግለሰቦች እያንሸራተተ ተከራከረ፡፡ ድርጅታዊ መግለጫዎቹን የንፅህናውና የማንነቱ ማስረጃና ማረጋገጫ አድርጎ አቀረበ፡፡ ‹‹ከብሔራዊ ነፃነት ንቅናቄዎች፣ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች ተውጣጥቶ ከ87 በማይበልጡ አባላት›› የተመሠረተው የሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ አባል ኦነግ ነው፡፡ ባለ አሥር መቀመጫ ፓርቲ ነው፡፡ ኦነግ መጣራት ካለበት የላንጌና የወተር ጭፍጨፋም ይጣራ፣ አጣሪዎችም ኦነግና ኢሕአዴግ የሌሉበት ኮሚቴ ይሁን ቢልም፣ ከዚያም ኃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ወደ ግለሰቦች ማሳበብ ቢፈልግም፣ መፈናፈኛ የማይሰጥ ማምለጫ ያሳጣ መከራከሪያ አጋጠመው፡፡ ኢሕአዴግ በተለይም የኢሕአዴግ አመራር ተወካዮች ‹‹እንዴት ሆኖ? አንተ ባታጠፋ ጥፋቱ ሲፈጸም ምን የወሰድከው ዕርምጃ አለ?›› ብለው ኦነግንና የኦነግን መከራከሪያ ዋጋቢስ አደረጉት፡፡ የሽግግሩ ምክር ቤትም የበደኖ ግድያ ፈጻሚዎችን ኦነግ አሳልፎ እንዲያስረክብ፣ አጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግም ድርጅቱ ተጠያቂ መሆኑን በብሔር መብት ሽፋን የሌሎችን መብት መርገጥ የሚወገዝ መሆኑን ወሰነ፡፡

ይህን የመሰለው ክፉ አጋጣሚ ግን በጭራሽ ትምህርት አልሆነንም፡፡ የሥርዓት ግንባታችንን አላገዘንም፡፡ የላንጌም ሆነ የወተር ተቃውሞን በጥይት የማስተናገድ ሞያ እንዲሁም የበደኖ እልቂት ምንም አላስተማረንም፡፡ የሚገርመውና የሚደንቀው በበደኖ ግፍና እልቂት ኦነግን ያፋጠጡትና ማምለጫ ያሳጡት ተከራካሪዎች በተራቸው በወተር እልቂት ላይ ተጠያቂ መሆን ያለበት ተኳሽና አስተኳሽ አይደለም፣ ሕገወጡን ሰልፍ ያነሳሳው አካል ነው አሉ፡፡ ከ20 ሺሕ ገበሬ በላይ የተሳተፈበት ሰልፍ ፀረ ቻርተር፣ ፀረ ሕገ መንግሥት ነበር፣ ፀጥታ ለማስከበር የተላኩት ወታደሮች ቢሸሹ ተጠያቂ ይሆኑ ነበር እያሉ እልቂቱን ልክና ተገቢ አድርገው ተከራከሩ፡፡ በዚያው የበደኖ ውሳኔ ውስጥ ወተርን በተመለከተ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ኃይል መጠቀማቸው ተገቢ መሆኑ፣ ተገቢ ቢሆንም ከሚገባው በላይ ኃይል መጠቀም አለመጠቀማቸው እንዲሁም የሕገወጡ ሰልፍ አደራጅ ማን እንደሆነ እንዲጣራ የሚል ውሳኔ ተላለፈ፡፡

ይህ የ1984 ዓ.ም. አጋጣሚ ምንም ሳያስተምረን፣ የመሳሪያ ወይም የትጥቅ አጠቃቀም የሕግ ዳር ድንበር ሳይገባን፣ በቻርተሩ ቁጥር አንድ ላይ የተደነገገው ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በሰላም የመሰብሰብና የመቃወም ነፃነት ልክና ይዘት ሳይፍታታልን፣ ገዥው ፓርቲም ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ተለውጦ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ፣ ከተለመደው (እሱም አገሩም ከለመደው) የጦርነት ስልት መሸጋገር ሳይችል እነሆ 25 ዓመታት አልፎናል፡፡

በምንነጋገርበት ጉዳይ ላይ የተጋፈጥናቸውንና የደረሱብን አጋጣሚዎች፣ ፈተናዎችና አደጋዎች አለፍ አለፍ አድርገን የተቻለንን ያህል በቅደም ተከተል መለስ ብለን እንመልከት፡፡ አገር ካስመዘገበቻቸው በርካታ ያለሕግና ያለፍርድ ግድያዎች ውስጥ በዚያው በሽግግሩ ዘመን የተፈጸመው የታኅሳስ 26 ቀን 1985 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰልፍና ኢሕአዴግ ሕግን ተገን አድርጎ በከፈተው ተኩስ የደረሰው ጉዳት ይገኝበታል፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ‹‹ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን›› የተቋቋመበት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በወቅቱ ያቀረበው መከራከሪያና መከላከያ፣ ትናንት በ1984 ዓ.ም. በወተርም ላይ የቀረበው ዓይነት ነው፡፡ ከተማሪው ሰልፍ በስተጀርባ ሌሎች የተለጠፉ ኃይሎች የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ፣ የመንግሥትን የተቃውሞ ሰልፍ በሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ ነፃነት ዓይንና ማዕዘን ውስጥ የማስተናገድ ግዴታን ቀሪ የሚያደርግ ይመስል፣ አንዱ መከራከሪያው ይህ ነበር፡፡ ይህ ግን ኃይል የተጠቀሙ የመንግሥት የሥልጣን አካላትንና ባለሥልጣኖቻቸውን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ሊያደርጋቸው፣ ተጠያቂነቱንም ወደ ሌላ ወገን ሊያዘዋውረው አይችልም፡፡ በስፍራው የሠለጠነ ፖሊስ፣ እንዲሁም የውኃ መርጫ መኪና አለመኖርና አለመገኘቱ ተማሪዎቹ አስቀድመው ‹‹ፈቃድ›› አለማውጣታቸው እንዲተኮስባቸውና እንዲገደሉ ያዘዘውን መንግሥታዊ ክፍል ከተጠያቂነት የሚያድነው ይመልስ የመጀመሪያው ገለልተኛ ኮሚሽን የተቋቋመበት ጉዳይም አንዳችም ነገር ሳያስተምርና ሳያስመዘግብ ተድበስብሶና ጉዳዩን አድበስብሶ አለፈ፡፡

ጳጉሜን 1 ቀን 1985 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ 19 ሰዎች የሞቱበት፣ ብዙዎች የቆሰሉበት፣ በርካቶች ለእስራት የተዳረጉበት ጉዳይ ለምርመራ ወግ እንኳን የታደለ አልነበረም፡፡ ያኔም፣ ጉዳዩ ለምርመራ ባይበቃም፣ የቀረበው የመንግሥት መከራከሪያና መከላከያ በወንጀል የሚፈለጉ መነኩሴ ለመያዝ እንደነበር የሚገልጽና ተቃውሞን ከአሮጌው ሥርዓት ናፋቂዎች ትግል ጋር አዛምዶና አወሳስቦ ማቅረብ ነው፡፡

ነገሩን የሚመረምረው የሚያስተውለው ጠፍቶ እንጂ እንኳንስ የመቃወም መብት የሽግግሩ ቻርተር ቁጥር አንድ መብት ባደረገ አገር ቀርቶ ድሮም ቢሆን እንኳንስ በተራ ወንጀል የሚፈለግ ሰው፣ መንግሥትን ለመቃወም አድማ ሠርቶ ሳይሳካለት የቀረ ሰው፣ ደወል ደውሎ ቤተ ክርስቲያን ከገባ፣ ቤተ ክርስቲያንን በማክበር መንግሥት በአካባቢው ዝር እንደማይል የሚታወቅና የእምነት መብትና ሕግ ድጋፍ ያለው አሠራር ነበር፡፡ በተባለው ድርጊትና ወቅት ግን እንኳንስ ተፈላጊ የተባሉት ሰው ሊተው ሌሎች በምንም የማይጠረጠሩ ግለሰቦች የቤተ ክህነቱ ክብር እንዳይደፈር ስለተከላከሉ የሞት አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ዓይነት አካሄድ የጦር መሳሪያ አጠቃቀማችን፣ የሰልፍና የተቃውሞ መብት የመስተንግዶ ወይም አያያዝ አሠራራችንን የሚገዛው ሕግ ሳይኖርና ሳይጠራ እንዳፈተተ መጓዙን ቀጥሏል፡፡

በአገራችን ውስጥ ከሽግግር ዘመኑ ጀምሮ የመንግሥትን የመሳሪያ አጠቃቀም፣ የሰላማዊ ሰልፍና ተቃውሞ የማስተናገድ ሕጋዊነት ለጥያቄ የሚያቀርቡ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ከምርጫ 97 በኋላ የታየው ግን በጣም የተለየና የመንግሥትን ባህሪይና አሠራር ወደባሰና ወደለየለት ሥልጣንን የመከላከልና ሰላማዊ ተቃውሞን ጭምር የማጥፋት ዋነኛ ምናልባትም ብቸኛ ሥራ ቀይሯል፡፡

ድኅረ ግንቦት ሰባት ተቃውሞ ሌላው፣ ምናልባትም ሦስተኛው አጣሪ ኮሚሽን የተቋቋመበት ‹‹ሁከት›› ነው፡፡ የመጀመሪያው የታኅሳስ 1985 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ አጣራ የተባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የተከሰተውን ግጭት ያጣራ ዘንድ የተቋቋመው የ1996 ኮሚሽን ነበር፡፡ እስከዛሬ ድረስ የተቋቋሙ ልዩ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽኖች ሁሉ የሕግ አስከባሪ ኃይሎችን የኃይል አጠቃቀም ሕጋዊነት፣ የተወሰደውን ዕርምጃ ካስፈላጊው መጠን በላይ ወይም ከሁኔታው መጠን በላይ ያላለፈ መሆኑን ያጣሩ ዘንድ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡ ዛሬም ድረስ ከምርጫ 97 ወዲህ ሲቆጠር አሥር ዓመት ሙሉ ከመጀመርያው መርማሪ ኮሚሽን ጀምሮ ደግሞ እነሆ ለ25 ዓመታት ያህል የምንሰማው የማይገባን፣ አልገባ ያለን፣ ማንም ሊያስረዳንና ሊያስተምረን ያልተቻለው ‹‹የተመጣጣነ›› ወይም ‹‹ያልተመጣጠነ›› ኃይል ጉዳይ ሚስጥር መነሻ ይኸው ነው፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ ‹‹የተፈጠረውን ሁከት የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን›› በአዋጅ የተቋቋመበት ምክንያት በራሱ በሕጉ እንደተገለጸው፡፡

  • ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ ከጥቅምት 22  ቀን እስከ ኅዳር 1 ቀን 1998 ዓ.ም.፣ እንደዚሁም ከኅዳር 5 ቀን እስከ ኅዳር 7 ቀን 1998 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ተከስቶ የነበው ሁከት ያስከተለው ችግርና ሁከቱን ለመቆጣጠር በመንግሥት የተወሰደው ዕርምጃ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ አንፃር ያለውን ሁኔታ ማጣራት ተገቢ ስለሆነ፣
  • በአገራችን እየገነባ ያለው ሥርዓት የሕግ የበላይነት የሰፈነበትና ራሱን በራሱ እያረመ የሚሄድ በመሆኑ፣ ተከስተው የነበሩ ሁኔታዎችን ማጣራትና አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ እንዲቻል ትክክለኛውን ሁኔታ ለምክር ቤት የሚያቀርብ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም ለተጀመረው የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር በዋነኝነት የተከሰተውን ችግር ለመግታት በፀጥታ አስከባሪ ኃይል የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ፣ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሕገ መንግሥቱንና ሕጉን የተከተለ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ እንዲሁም በተከሰተው ችግር የደረሰውን የሕይወትና የንብረት ጉዳት ማጣራት ነበር፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ የተቋቋመው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለፓርላማው ሪፖርት ካቀረበና በዚሁ ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ከታወጀ በኋላ አባላቱም ተሰይመው፣ እንደገናም በተጓደሉ የኮሚሽኑ አባላት ምትክ ሌላ አዲስ አምስት አባላት ተሹመው የኮሚሽኑ የማጣራት ሪፖርት ለምክር ቤቱ የቀረበው ከብዙ ያልተጠበቁ ውጣ ውረዶች በኋላ ከሞላ ጎደል በዓመቱ በጥቅምት ወር 1999 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ቀን ማለትም ጥቅምት 1 ቀን 1999 ዓ.ም. የአጣሪ ኮሚሽኑ የሪፖርት መሸኛ ደብዳቤ ወጭ ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተላከበትን ቀን የሚያሳይ ነው፡፡

የኮሚሽኑን ሪፖርት የፈረሙት ከ11 አባላት መካከል ስምንቱ ብቻ ናቸው፡፡ ከተጓደሉት ሦስት አባላት መካከል ሁለቱ ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው ሲሆኑ፣ የኮሚሽኑ ሪፖርትን በጊዜያዊ ሰብሳቢነት የፈረሙት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሥልጣንና ተግባራቸው የተደነገገው ዋናው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳብው አይደሉም፡፡ ከተጓደሉት ሦስት የኮሚሽኑ አባላት መካከል ሁለቱ ሪፖርቱ ለምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ከአገር ወጥተው መግለጫ መስጠታቸው በሰፊው የተነገረላቸው የኮሚሽኑ ሰብሳቢና ሌላ የኮሚሽኑ ተራ አባል ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ውሳኔ በተከሰተው ችግር ውስጥ ቀድሞ በመንግሥት ከተገለጸውና ከታመነው በላይ የ193 ሲቪል ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ቢገልጽም፣ ‹‹የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በፀጥታ አስከባሪ ኃይል የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ›› የሚለው ለኮሚሽኑ ተዋቅሮ የተሰጠው ጭብጥ ግን ቀጥተኛ መልስ ለመስጠት፣ ለጥቅስ የሚበቃ መከራከሪያ ሆኖ የሚያገለግል የአገሪቷን የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀም ሕግና ባህል አፍታትቶ ለማቋቋም ሳይታደል የቀረ ውሳኔ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት የተከሰተውን ችግር ለመግታት በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ የቀረበለትን ጥያቄ የመለሰው መጀመሪያና ደግሞ ደጋግሞ የ‹‹ሁከቱን መጠነ ሰፊነት›› በመግለጽ ነው፡፡ ‹‹ሁከቱ መጠነ ሰፊ፣ ብዙ ሰዎች የተሳተፉበትና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በ204 ቦታዎች የተከሰተ ስለሆነ በወቅቱ ባይገታ ኖሮ ሊደርስ ይችል የነበረውን አደጋ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በዚሁ ሁከት የሕዝብን ሕይወትና ንብረት ከአደጋው ለመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለበት የፀጥታ አስከባሪ ኃይልም ፀጥታን በማስከበሩ ሒደት ሁከትን ከመግታት አልፎ የግለሰቦች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ሕገ መንግሥታዊ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ይህም ሲባል ሁከትን ለመግታት የሚያስፈልገው ኃይል እንደ ሁከቱ ስፋትና ክብደት እንዲሁም ሊደርስ ከሚችለው ጥፋትና አደጋ አንፃር የሚታይ ነው፤›› ይላል፡፡

እንደገናም ‹‹ሁከቱ መጠነ ሰፊና እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች የተሳተፉበት ለመከላከል የወጣውን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል በብዙ እጅ የሚያጥፍ፣ አንድ ቦታ ላይ የተገታ መስሎ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ እንደ አሸን እየፈላ፣ የፀጥታ አስከባሪውን ትዕግስትና ህልውና ክፉኛ የተፈታተነ ነበር፤›› እያለም ደግሞ ለጭብጡ ምላሽ የያዘውን መንደርደሪያ ያስተዋውቀናል፡፡ ይህንን መልሶ መላልሶ ደግሞ ደጋግሞ ካስታወቀ በኋላ ‹‹ማንኛውም በሕጋዊ መብት ላይ የተቃጣ ሕገወጥ ተግባር በሕጋዊ አካል መመከት እንዳለበት ሁሉ፣ በመመከቱ ሒደትም ሕገወጥ ድርጊትን ለመግታት የሚወሰደው ዕርምጃ በሕገወጡ ድርጊት ሊደርስ ይችል ከነበረው ጉዳት በላይ እንዳይሆን የፀጥታ አስከባሪው አካል ሕገ መንግሥታዊ ተጠያቂነት እንዳለበት የኮሚሽኑ እምነት›› መሆኑን ይገልጻል፡፡ የተከሰተውን ችግር ለመግታት በፀጥታ አስከባሪ ኃይል የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ መሆን አለመሆኑ የሚታየው ከዚሁ አንፃር ነውም ይላል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት በእነዚህ መካከል ሲመላለስና ሲዞር ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ‹‹…የተከሰተውን ሁከት ለመግታት የፀጥታ አስከባሪው ኃይል የወሰደው ዕርምጃ አዲሱን ሥርዓተ መንግሥት ለመከላከልና አገሪቷ ወደባሰ ምናልባትም ማለቂያ ወደሌለው ብጥብጥ እንዳትገባ የተወሰደ ሕጋዊና አስፈላጊ ዕርምጃ መሆኑን ኮሚሽኑ አምኖበታል፡፡ የተመጣጣኝነቱም ጉዳይ ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፤›› በማለት ሪፖርቱን ደምድሟል፡፡

ይህ ሪፖርት ከቀረበ፣ ቀርቦም በምክር ቤቱ ከፀደቀ እነሆ አሥር ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ ሪፖርቱና ውሳኔው ግን በዚህ ዙሪያ የሚነሱና የሚከሰቱ የንድፈ ሐሳብም ሆነ የተግባር ጥያቄዎች መፍቻና ማፍታቻ፣ የአገር የዓይን መብራት፣ የእግር መንገድ ሆኖ አላገለገለም፡፡ መንግሥት ራሱ እንኳንስ ሲጠቅሰው መጀመሪያም እሱ ነው ሲለው ሰምተን አናውቅም፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚዎችም፣ በመንግሥት ደረጃም የአገር አጋሮችና ወዳጆችም ይህ ሪፖርትና ውሳኔ ነገሩን ከተተው ብለው ጉዳዩን አልተውትም፡፡ ዛሬም እንደ ትኩስነቱ በየጊዜው የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

ለምሳሌ ያኔ በትኩስነቱ በ1998 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ አውሮፓን በሚጎበኙበት ወቅት ጋዜጠኞች ይህን ጉዳይ አንስተው ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ ለዚያውም ያኔ የሚታወቀው መንግሥት የተቀበለው የ35 ሲቪሎችና የሰባት ፖሊሶች ሞት ብቻ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጥቅምት 1998 ጀርመን ላይ የተጠየቁት ጥያቄ ‹‹ፓሪስም፣ ቦነስ አይረስም የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሰው የገደሉት ግን ኢትዮጵያ ብቻ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ አቶ መለስም የምርጫው ውጤት ግጭት በማስከተሉ፣ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ ማዘናቸውን ገልጸው፣ የፀጥታ ኃይሎች ሰው የገደሉት ግን ቦምብ ስለተወረወረባቸው ጠበንጃቸውን ሊቀሙ/ይቀሙ ስለነበር ነው ብለው፣

‹‹አንድ የመጨረሻ ነጥብ፣ ፈረንሳዮች ተቃዋሚውን ሰልፈኛ አልገደሉም፡፡ ይህ ለእነሱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኛም ልንኮርጀው የምንመኘው ነገር ነው፡፡ እኛ መማር የሞከርነው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን፣ ተቃውሞን የመከላከልና የመመከት ብቃት ያለው ፖሊስ አልነበረንም፡፡ ችግሩ መፈጠር ሲጀምር ግን ገንዘብ አወጣን፡፡ ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል አሠለጠንን፡፡ በቂ መሳሪያ አመጣን፡፡ ይኸውም በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ያንድ ወር ጊዜ ብቻ ስለነበር ነው፤›› አሉን፡፡

አቶ መለስ በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ፊት የሰጡት መልስ ምናልባትም ‹‹የተከሳሽነት›› መልስ ግራ ቀኙን አከራክሮና ሰምቶ ውሳኔ ከሰጠው ከአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት መደምደሚያ ጋር በጭራሽ አብሮ አይሄድም፡፡ በፀጥታ አስከባሪ ኃይል የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ነው አይደለም? የሚለው ጥያቄ ከእያንዳንዱ ሟች ወይም የተገደለ ሰው በሕይወት የመኖር መብት፣ ይህ ሰው ሊያደርሰው ይችል ከነበረው ሕገወጥ ጥቃት አንፃር፣ ለዚያውም ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ሌላ መንገድ አለመኖሩ ተመርምሮና ተረጋግጦ የሚሰጥ መልስ መሆኑ ቀርቶ ነገሩ ሁሉ የጥፋትና የልማት ኃይሎች፣ የከፋና የተሻለ ሥርዓት፣ ማለቂያ የሌለው የብጥብጥና የሰላም ምርጫ ሆኖ ቀረበ፡፡ የተከሰተውን ሁከት ለመግታት የተወሰደው ዕርምጃ አዲሱን ሥርዓት መንግሥት ለመከላከልና አገሪቷ ወደ ባሰ ምናልባትም ማለቂያ ወደሌለው ብጥብጥ እንዳትገባ የተወሰደ ሕጋዊና አስፈላጊ ዕርምጃ ነው ተባለና አረፈው፡፡

ከምርጫ 97 የአጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት አሥር ዓመት በኋላ ሌላ አገር ያወቀው የመላው ዓለም ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የግንባርና ርዕሰ ዜና የሆነ ኦሮሚያ ውስጥ ግጭትና ሁከት ተከሰተ፡፡ ይህን ጉዳይ ማጣራትም ግድና አስፈላጊ ሆነ፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ግን ለጋምቤላው በአዋጅ ቁጥር 398/96 ለአዲስ አበባው በአዋጅ ቁጥር 478/97 እንደተቋቋመው ዓይነት ኮሚሽን አልተቋቋመም፡፡ የምርመራው ጉዳይ መደበኛው አሠራር ላቋቋማቸው የተቋቋመውን የአሠራር ሥነ ሥርዓት ተከትለው ለሚሠሩ የመርማሪ አካላት (ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ) አልተተወም፡፡ በዜና እንደተዘገበው ምርመራውን የኦሮሚያውን በራሱ አነሳሽነትና የቅማንቱን ጉዳይ ደግሞ በአቤቱታ የወሰደው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው፡፡

ዜና ሆኖ በቀረበው በኮሚሽኑ ሪፖርት መሠረት በቅማንት ሕዝብ ጥያቄ ጉዳይ በአጠቃላይ በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በተነሳው ግጭት 97 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በቦታው የተሰማራው ልዩ የፖሊስ ኃይል ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ ተጠቅሟል፡፡ ‹‹በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በድምሩ የፀጥታ አስከባሪው የወሰደው ዕርምጃ የዜጎችን ሕይወት፣ የአካል ደኅንነት፣ በአጠቃላይ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅና ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በክልሎችና በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች በመዳረስ እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ የተወሰደ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ነው፤›› ብሏል፡፡

በዚህም ሪፖርት የተመጣጣኝ ኃይል አጠቃቀም ትርጉም አልተፈታልንም፡፡ በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ የሞቱት ሰዎች ተገደሉ እንኳን አልተባሉም፡፡ ተገደሉ ማለት ለሕይወታቸው መጥፋት ምክንያት የሆነውን የፀጥታ አስከባሪዎች ዕርምጃ የግድና ሁልጊዜም ወንጀል አያደርገውም፡፡

የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ነው ማለት ግን ዕርምጃውን የወሰደው ሰው (ወይም በተራ ቋንቋ ገዳዩ) የራሱን ወይም የሌላውን መብት/ሕይወት ሕገወጥ ከሆነ ጥቃት ወይም በቅርብ ከሚደርስ ሕገወጥ ጥቃት ለማዳን ሌላ አማራጭና የተሻለ መንገድ ሳይኖር ከሁኔታው መጠን ሳያልፍ የፈጸመው ድርጊት ነው ማለት ነው፡፡ በዚህና በእያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታ ከሕግ ወሰን ሳይተላለፍ የተፈጸመ ሕጋዊ ተግባር ነው ማለት ነው፡፡ እውነት ነወይ? እውነትና ትክክል ቢሆን እንኳን ሪፖርቶቹ በቀረቡበት መልክና ይዘት ይህንን እውነትና ሐቅ እንኳንስ ጉዳቱ ለደረሰባቸው ሰዎች ቤተዘመዶችና ወገኖች ለተራውና ለባዳው፣ ስሜቱ ሳይነዝረው ደሙ ሳይፈላ ራቅ ፈቀቅ ብሎ ለሚሰማው ገለልተኛ ሰውስ ይገባል ወይ? ያሳምናል ወይ? የመንግሥትን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማወራረድ ቀርቶ፣ የሕዝብን ልብ መርታት ይቅርና በመርማሪዎችና በሪፖርት አቅራቢዎች በኩል ዕውን የማያዳግም፣ በአረም የማይመለሱበት የጠራ የተዋጣለት ሥራ ነወይ? በዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ መድረክ በአደባባይ ሳያፍሩና ሳይፈሩ ተሟግተው የሚረቱበት መርህና አቋም ነወይ? ሪፖርቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት የሚያስጨብጠው ትምህርትስ የአገርና የሰብዓዊ መብቶች መኩሪያና መታፈሪያ የሆነ የማንም የቡድን ጥቅም ተቀጢላ ያልሆነ የሕግና የፀጥታ ኃይል መኮትኮትና ማፍራት የሚያስችል ነወይ? ሳንፈራና ሳንቸር መነጋገር አለብን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...