Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመለያየት ፍቺ የሚሆነው መቼ ነው?

መለያየት ፍቺ የሚሆነው መቼ ነው?

ቀን:

መለያየት ፍቺ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ምን ያህሉ ተጋቢዎች ያውቃሉ? በተግባር የተፋቱ የሚመስላቸው ግን በሕግ ያልተፋቱ መሆናቸውንስ የሚያውቁ አሉ? እስከ ቅርብ ዓመታት ባልና ሚስት በፍርድ ቤት ካልተፋቱ በተግባር ተለያይተው የራሳቸውን ሌላ ሕይወት ቢጀምሩ እንኳን እንዳልተፋቱ ይቆጠራል፡፡ ቢያንስ በሕግ ባለሙያዎች መካከል ይህ መረዳት ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተለያዩ ተጋቢዎች እንደተፋቱ የሚቆጠሩበት የሕግ መርህ በሰበር ችሎት ተሠርቷል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሕግ ባለሙያዎች ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› የሚል ስያሜ ይሰጡታል፡፡ የሰበር ችሎቱ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የራሱ መርህና ልዩ ሁኔታ ያለው ሲሆን፣ ፍርዶቹ ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት የሰጡ አይመስልም፡፡ ጭብጡ የተለያዩ አቋሞች ስለሚያዝበትና መርሆቹ በዝርዝር ስላልተሠሩ አከራካሪነቱ የቀጠለ ይመስላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሰበር ችሎቱ የወሰናቸውን ፍርዶች መነሻ በማድረግ የተወሰነ ምልከታ እናደርግበታለን፡፡

 ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› የሚለው ኃይለ ቃል የውሰት ቃል በመሆኑ ትርጉሙን ከአመንጪው እንስጥ፡፡ አቶ ፊሊጶስ አይናለም የተባሉ የቀድሞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በሚዛን የሕግ መጽሔት ለቃሉ ትርጉም ሰጥተዋል፡፡ በእርሳቸው ትርጉም ‹‹በተግባር/በእውነታው የተፋቱ በሕጉ ድንጋጌ መሠረት ግን ያልተፋቱት›› ተጋቢዎች ሁኔታን ያመለክታል፡፡ ጸሐፊው በጽሑፋቸው ይዘት ሐሳቡን ሲያብራሩ ባልና ሚስት ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለዓመታት ተለያይተው የግል ሕይወታቸውን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በፍርድ ቤት የፍቺ ውሳኔ ወይም አንደኛው ተጋቢ ሲሞት ሚስትነት (ባልነት) እንዲረጋገጥላቸው የሚጠይቁትን እንደሚመለከት ይገልጻሉ፡፡ የአሁኑ ጸሐፊም ሊያነሳው የሚፈልገው ሐሳብ ከዚሁ የዘለለ ባለመሆኑ ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› (Defacto divorce) የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፡፡

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በአብዛኛው ባልና ሚስት ተፋታን ብለው የሚያስቡት በራሳቸው፣ በቤተ ዘመድ፣ በሽማግሌዎች ወዘተ. የማይስማሙበትን ሐሳብ መክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር የፈጸሙትን መለያየት ነው፡፡ አልፎ አልፎም በተጋቢዎቹ መካከል አለመስማማት ባይኖርም ተለያይተው ለዓመታት ሊቆዩ፣ የየራሳቸው የግል ሕይወትም ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ተቀባይነት ያለው ፍቺና ለዘመናት የኖረ ሃቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በማንኛውም ዓይነት ሥርዓት የተፈጸሙ ጋብቻዎችን ፍቺ የሚገዛው የቤተሰብ ሕግ፤ ተርጓሚዎችም የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሕጉና የሕጉ ጥሬ ንባብና የባለሙያዎቹ የኖረ (የቆየ) አስተሳሰብ ደግሞ ፍቺ በፍርድ ቤት ካልተፈጸመ በሕግ ፊት ፍቺ እንደሌለ እንደሚቆጠር ነው፡፡ ያም ሆኖ ዳኞች ከዚህ አቋም የተለየ አስተሳሰብ በማራመድ ወደ ኅብረተሰቡ አስተሳሰብ ከፍ/ዝቅ ያሉበት አጋጣሚም አለ፡፡ ይህን የምንለው አስገዳጅ ፍርድ ባልተጀመረበት የሕግ ሥርዓታችን ጭምር ነው፡፡ ከሰኔ 1997 ዓ.ም. በኋላ ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጅ ቁጥር 454/97 መሠረት ከአምስት ባላነሱ ዳኞች የሚሰጣቸው ፍርዶች አስገዳጅ ትርጓሜ ስለሆኑ በሥር ፍርድ ቤቶች ሳይቀር የሕግ ውጤት ያላቸው ሆነዋል፡፡ የአዋጁ ዓላማ በየአውዱ እንደተገለጸው ውሳኔዎችን ወጥ ለማድረግ፣ ልዩነትን ለማጥበብና የተከራካሪዎችን ወጪ ለመቆጠብ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ችሎቱ የሰጣቸው ፍርዶች በ18 መዛግብት የታተሙ ሲሆን፣ ይዞታቸውን የመረመረ ባለሙያ የሕጉንና የአተገባበሩን ልዩነት በመዳኘት ረገድ ሁለት አቋሞች ሲንፀባረቁ ያስተውላል፡፡ የመጀመሪያው የችሎቱ ለጥሬው የሕግ ንባብ ያለው ወገንተናዊነት ነው፡፡ አንዳንዶች ይህንን የችሎቱ አቋም ለሕግ አውጭው ንባብ ያደላ (Positivist thought) ስለመሆኑ ትችት ያቀርቡበታል፡፡ ኋላ በተሰጡ ፍርዶች የተሻሻለ ቢሆንም የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ምዝገባን በተመለከተ በችሎቱ የተሰጡ ፍርዶች ይህንኑ ዓላማ ያሳብቃሉ፡፡ አንዳንዴም ለመንግሥት ፖሊሲዎችና ተቋማት ያዘነብላሉ የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡ ሁለተኛው የዳኝነት ንቁ ጣልቃ ገብነት (Judicial activism) የሚንፀባረቅበት ከሕጉ ይልቅ ኅብረተሰቡ ተማምኖ ለሚተገብረው ሃቅ የመወገን አቋም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አቅም ችሎቱ ማኅበረሰባዊ (Sociological)፣ ተግባራዊ (Realism) አስተሳሰብ በሚለው የሥነ ሕግ ምድብ እንዲፈረጅ ሊያደርገው እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ ከዚህ አቋም አንፃር ሳይፋቱ ፍቺን የተመለከቱ ፍርዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ችሎቱ ወደ የትኛው ክንፍ (ጥግ) ያደላል የሚለው አጥኚዎች የሚያረጋግጡት ይሆናል፡፡

ሳይፋቱ ፍቺን በተመለከተ የተሰጡትን የሰበር ፍርዶች ያስተዋለ ሰበር ችሎቱ ለኅብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ ዋጋ የሰጠበት መሆኑ አያከራክርም፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተፋቱን ተጋቢዎች ስለተለያያችሁ፣ አብራችሁ ስለማትኖሩ፣ መፋታታችሁን በፈቃዳችሁ በመቀበላችሁ ጋብቻው ስላለመፈታቱ የምታቀርቡት ክርክር ቅቡል አይደለም ሲል ችሎቱ ወደ ተጨባጭ እውነታው ቀርቧል፡፡ ሕግን በኮንቲኔንታል /Continental/ ሥርዓት ለተማረ ባለሙያ ይህን መቀበል ከመክበድ ባለፈ የማይታሰብ ነው፡፡ የዛሬው ጽሑፍም ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑት ነጥቦች ላይ ምልከታ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፍቺ በማንና በምን ምክንያት ይፈጸማል? የሰበር ችሎቱ የተለያዩ አቋሞች ምን ይመስላሉ? የችሎቱ ፍርዶች ምን ክፍተት አለባቸውና እንዴት ሊጠገኑ ይችላሉ የሚሉትን ነጥቦች ተራ በተራ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የሕጉ ይዘት

በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ያሉ የቤተሰብ ሕግጋት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ይዘት ስላላቸው በ1992 ዓ.ም. የወጣውን የፌዴራሉን የቤተሰብ ሕግ መሠረት ያደረገ ገላጭና ተንታኝ ሐሳብ ማቅረብ ጊዜ ቆጣቢ ነው፡፡ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 76 መሠረት ጋብቻ በፍቺ እንዲፈርስ ሊወሰን የሚችለው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑ ወይም ከተጋቢዎች አንዱ ወይም ሁለቱም በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡ የሕጉ አንቀጽ 76 ና 117 የጣምራ ንባብ በሁለቱም ጊዜ ፍቺን የሚያፀድቀው ወይም የሚወስነው ፍርድ ቤት ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት ፍቺንና የፍቺን ውጤቶች የመወሰን ሥልጣን ሕጉ የሰጠው ለፍርድ ቤቶች በመሆኑ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ፍቺ አይኖርም፡፡ የሕግ አውጭው ዓላማ ግልጽና ሁሉንም የማያስማማ ነው፡፡ የተጋቢ ግለሰቦችን የጥቅም ልዩነት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የማስታረቅ፣ የሕግ አውጭውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ የሕጉን ይዘት ማስፈጸም የሚችለው ዳኛው ነው፡፡ ዳኛው የሚይዘው አቋም በፍትሕ ሥርዓቱ ወጥነትንም የሚያሰፍን በመሆኑ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ያም ሆኖ የሕግ ብዙኅነት ባለበት ሁኔታ የሕጉ ይዘት የተወሰኑ ክፍተቶች እንዳሉበት በምሁራን የቀረቡ ትችቶችን በጽሑፍ ቀጣይ ክፍሎች ስንመለከት የምናየው ይሆናል፡፡

የችሎቱ የቀደመ አቋም         

የሰበር ችሎቱን የቀደመ አቋም አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በጥሩ መልኩ ያጠኑት በመሆኑ ጽሑፋቸውን መሠረት አድርገን አቋሙን እናስቀምጥ፡፡ ሰበር ችሎቱ አስገዳጅ ፍርድ ለመስጠት ሥልጣን ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ ከብዙኃኑ የቀድሞ አስተሳሰብ የተለየ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ፍርዶቹ በሰበር መዝገብ ቁጥር 14290፣ በመዝገብ ቁጥር 20938 እንዲሁም በሰበር መዝገብ ቁጥር 31891 የተሰጡ ናቸው፡፡ በእነዚህ ፍርዶች የቀረቡት ክርክሮች ባልና ሚስት በአንዱ ጉዳይ ለ13 ዓመታት፣ በሁለተኛው ጉዳይ ከ20 ዓመት በላይ፣ በሦስተኛው ደግሞ ለ12 ዓመታት ተለያይተው በቆዩበት ሁኔታ የቀደሙ ሚስቶች የቀደሙ ባሎቻቸው ሲሞቱ ፍቻቸው በፍርድ ቤት ውሳኔ አልተደረገምና ንብረት እንካፈል ሲሉ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በክርክሩ እንደተገለጸው ባልና ሚስቱ በተለያዩበት ዘመናት የራሳቸውን ሕይወት የጀመሩ ሲሆን፣ እንዲያውም በአንዱ መዝገብ ሚስት ነኝ ብላ የቀረበችው ከሌላ ትዳር የ11 ዓመት ልጅ ያላት መሆኑን ነው፡፡ በእነዚህ መዛግብት ሰበር ችሎቱ በሰጠው ተመሳሳይ ፍርድ ተጋቢዎቹ ከአቅም በላይ ባልሆነ ምክንያት ለረጅም ዓመታት ተለያይተው መኖራቸው ግንኙነታቸው እንደቀጠለ ነበር ለማለት ስለማያስደፍር፣ ግንኙነቱ ማንም ሌላ ማስረጃ ሊያስረዳ ከሚችለው በላይ በመካከላቸው የነበረው የጋብቻ ግንኙነት መፍረሱ ሁለቱም ሌላ ሕይወት በመጀመራቸው ጭምር መገለጹ በፍርድ ቤት የተፈጸመ ፍቺ ባይኖርም ከእውነታው ተፋትተዋል በማለት የቀደሙ ሚስቶችን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

ይህ የሰበር አቋም ቀድሞ በብዙኃኑ ከሚንፀባረቀው ሐሳብ ባዕድ በመሆኑ የሕግ ሥርዓቱን ምልከታ የለወጠ ነው፡፡ ፍቺ በፍርድ ቤት ካልተፈጸመ ተቀባይነት አይኖረውም የሚለውን አስተሳሰብ የቀየረ ነው፡፡ ችሎቱ ፍቺ በፍርድ ቤት ውሳኔ ባይደረግም ተጋቢዎች ለረጅም ዓመታት ተለያይተው የየራሳቸውን ሕይወት ከጀመሩ ፍቺ እንደተፈጸመ ይቆጠራል የሚል አቋም ወስዷል፡፡ አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም የእነዚህን ፍርዶች አመክንዮ ‹‹ሕጉ በጠባብ ንባቡ ብቻ መተርጎም እንደሌለበትና የሕጉን ዓላማና መንፈስ እንዲሁም ማኅበራዊ እውነታን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግ ነው፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ጸሐፊው ረዥም ጊዜ መለያየት እንደፍቺ ማስረጃ የመቆጠሩን ፍትሐዊነት ወደኋላ ይሞግታል፡፡

የችሎቱ የቅርብ ጊዜ አቋም

ከላይ የተገለጹት የሰበር ችሎቱ ፍርዶች ከተወሰኑ በኋላ ችሎቱ የተወሰኑ የአቋም ለውጦች አሳይቷል፡፡ ችሎቱ በቅርቡ በሰጠው ፍርድ ባልና ሚስቶች ረጅም ጊዜያት ተለያይተው ቢኖሩም፣ በመካከላቸው ያለው ማኅበራዊ ትስስር የጋብቻ ግንኙነቱ አለማቋረጡን ካስረዳ «ሳይፋቱ ፍቺ» እንደማይኖር ወስኗል፡፡ ይህ ጉዳይ የታየው በሰበር መዝገብ ቁጥር 67924 ሲሆን፣ ፍርዱ የተሰጠው መጋቢት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ የሰበር አመልካች 18 ዓመታት የተለዩዋቸው ባላቸው ሲሞቱ ሚስትነታቸውን በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በውሳኔ አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ የሟች ልጅ በመቃወም ሚስትነታቸው እንዲሻር ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ታቀርባለች፡፡ የተቃዋሚዋ ጥያቄ አመልካች ሟች አባቴ ጋር በሕግ በታወቀ ሥርዓት ግንኙነት አልመሠረተም፤ ጋብቻ አለ እንኳ ቢባል አመልካቿ ከአሥር ዓመታት በላይ ኑሯቸውን ውጭ አድርገው ተለያይተው የኖሩ በመሆኑ፣ ጋብቻው ፈራሽ ነው በማለት የሚስትነት ማረጋገጫው ውሳኔ እንዲዘረዝራቸው ጠይቀዋል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ በአመልካችና በሟች መካከል የጋብቻ ግንኙነት ስለመኖሩ በሁኔታ ተረጋግጧል፣ አመልካችና ሟች ጋብቻቸው ባለበት ጊዜ በተለያየ አገር ተለያይተው መኖራቸው ቢታወቅም ጋብቻውን ቀሪ አያደርገውም፤ ምክንያቱም በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 55 እንደተመለከተው ተጋቢዎች በስምምነት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው መኖር መብታቸው በመሆኑ፣ በማለት ለአመልካች ፈርዷል፡፡ የአዲስ አበባ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሟች ልጅ ይግባኝን ተቀብሎ ካከራከረ በኋላ አመልካች ከሟች ጋር የነበራቸውን የጋብቻ ግንኙነት ተቀብሎ ነገር ግን ሁለቱም ለ18 ዓመታት ያህል ተለያይተው በመኖራቸው ምክንያት የቀጠለ ትዳር ግንኙነት አለመኖሩን ያሳያል በማለት የፌዴራል ሰበር ችሎት ቀደም ሲል በ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› ላይ የሰጣቸውን ፍርዶች መሠረት አድርጎ የአመልካችን ሚስትነት ሰርዟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎትም የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግ ስህተት አልተፈጸመበትም በሚል አመልካች ያቀረቡትን ማመልከቻ ዘግቶታል፡፡

ጉዳዩ በመጨረሻ ለፌዴራሉ ሰበር ችሎት የቀረበ ሲሆን፣ ችሎቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የባልና የሚስትን ግንኙነት ቀጣይነት እንደሚያሳይ አትቷል፡፡ ባልና ሚስቱ በአካባቢው ዕድርና በቤት ሥራ ማኅበር በባልና ሚስትነት እንደሚታወቁ፤ ሟች ሥራ ስላልነበራቸው ተጠሪዋ የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥ ከባለቤታቸው ጋር ባደረጉት ስምምነት ወደ ውጭ አገር ሄደው ሥራ በመሥራት በሚልኩት ገንዘብ ቤት መሥራታቸውን፣ ሟችም ሲታመም ገንዘብ በመላክ አስታምመው እንደነበር መረጋገጡ እስከ ዕለተ ሞት በትዳር ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ማሳያ ነው በማለት የአመልካችን ሚስትነት ያረጋገጠውን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ ይህ ገዥ ፍርድ ቀደም ብለን ለተመለከትናቸው ፍርዶች ልዩ ሁኔታ (Exception) ነው፡፡ ባልና ሚስት ለረጅም ዓመታት ተለያይተው ቢኖሩም በመካከላቸው ያላቸው ግንኙነት አለመቋረጡን በማኅበራዊ ትስስር ካረጋገጡ መለያየታቸው ለፍቺ ማስረጃ እንደማይሆን ነው፡፡ ቀጥለን ችሎቱ በተለያዩ ጊዜያት በያዛቸው አቋሞች ላይ ምልከታ ለማድረግ እንሞክር፡፡

በፍርዶቹ ላይ የቀረበ ምልከታ

ሰበር ችሎቱ የሰጣቸው ፍርዶች በዋናነት ሳይፋቱ ፍቺን ለአገራችን የሕግ ሥርዓት ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ ተጋቢዎች ለተወሰኑ ዓመታት ተለያይተው መኖራቸውና የየራሳቸውን ሕይወት መጀመራቸው ለመፋታታቸው በቂ ማስረጃ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ ያም ሆኖ መለያየታቸው ማኅበራዊ ትስስራቸውን ያላቋረጠው መሆኑ ከተረጋገጠ ፍቺ መኖሩን ግምት መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ችሎቱ ሌላ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የችሎቱ አቋም ሕጉን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑና አካሄዱ በተግባር የሚኖሩበትን ክፍተቶች ቀጥለን እንመልከት፡፡

ሕጉና ሳይፋቱ ፍቺ

የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 76 እና 117 ጣምራ ንባብ ፍቺ የሚፈጸመው በፍርድ ቤት ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ የቤተሰብ ሕጉ ማሻሻያ አንዱ አስኳል ነው፡፡ የቤተሰብ ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት የነበረው አሠራር የቤተ ዘመድ ጉባዔ ፍቺን እንዲወስን ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ ብዙ ችግሮች በጥናት ተረጋግጠውበታል፡፡ በዚህ መነሻነት ፍቺና የፍቺን ውጤቶች የመወሰን ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች ብቻ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ የሕጉ መግቢያ ይህን ዓላማ ሲገልጽ ‹‹በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱ ክርክሮችን ፍትሐዊ በሆነና በተቀላጠፈ ሁኔታ ብቃት ባለው አካል እንዲዳኙ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ›› ሕጉ ስለመሻሻሉ ይገልጻል፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ቅኝት (Perspective) አንፃር የሰበር ችሎቱን አቋም ከተመለከትን ውሳኔዎቹ ፍቺ ከፍርድ ቤት ውጭ እንዲከናወን የሚፈቅዱ ናቸው፡፡ ሕጉ ያለፍርድ ቤት ፍቺ አይኖርም እያለ ሰበር ችሎቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ባትፋቱም ተለያይታችሁ ስለቆያችሁ ተፋታችኋል በማለት አቋም መያዙ ከሕጉ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ሳይፋቱ ፍቺን የሕግ መሠረት መስጠት የሚቻለው ሕጉን በማሻሻል እንጂ ሕጉን ከደረቅ (ነጠላ) ግልጽ ንባቡ እንዲያፈነግጥ በማድረግ አይደለም፡፡

በእርግጥ ተጋቢዎች ለረዥም ዓመታት ተለያይተው፣ ግላዊና ንብረት ነክ ግንኙነታቸው ተቋርጦ፣ ኅብረተሰቡ መፋታታቸውን መስክሮላቸው አልተፋታችሁም ማለቱ ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡ ሆኖም የሕግ ሙያው ደግሞ የዳኝነት አካሉ ሕጉ ተግባራዊ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጉ ዘንድ ሕግ እንዲያወጡ መፍቀድ አይኖርበትም፡፡ በልማድ እንደሚባለው «ዳኞች ሕግ ነጋሪዎች እንጂ ሠሪዎች አይደሉም» The role of the judge is to declare what the law is, not to make it እንዲል፡፡ ዳኞች ሕግ የሚሠሩ ከሆነ የሕጉን ይዘት ወሰኑና ገደቡን መተንበይ ካልሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ በሕግ አውጭውና በሕግ ተርጓሚው መካከልም ያለውን የሥልጣን ክፍፍል ያፋልሳል፡፡ አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸውም የሕጉ አቋም ፍትሐዊነት የሚጎድለው መሆኑን በመግለጽ የሕግ ማሻሻያ መፍትሔ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ እንደእርሳቸው አመለካከት ሕጉ ጋብቻ ለሚፈጸምበት ሥርዓት ሦስት ዓይነት አማራጭ ዕድሎች ሰጥቶ ለፍቺ ሥርዓት አንድ ዓይነት መንገድ (ፍርድ ቤት) መሥራቱ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ጸሐፊው ፍርድ ቤት ብቸኛ አማራጭ መሆኑ አብዛኛው የገጠር ኅብረተሰብ ከሚኖርበት እውነታ ጋር የማይጣጣም ከመሆኑም በላይ ተደራሽነቱንና ተግባራዊ አፈጻጸሙን አከራካሪ ያደርገዋል ሲሉም አሳማኝ ሙግት ያቀርባሉ፡፡ ያም ሆኖ ሕጉ ያለበት ክፍተት በማሻሻያ ካልሆነ በዳኝነት ትርጉም የሚሞላ አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል ሕግ አውጭው ሕግን ሲቀርጽ የራሱ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ ፍቺና ውጤቱን ለፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሲተው በመግቢያው ላይ ከተገለጸው የፍርድ ቤቶች ቅልጥፍናና ብቃት ሌላም ኅብረተሰቡን ወደ ዘመናዊ አኗኗር ለመምራት በማሰብ ነው፡፡ ሕግ ኅብረተሰብን የሚለውጥ አንድ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡ ጋብቻና ፍቺውን እንዲያስመዘግብ፣ ፍቺውንም በፍርድ ቤት እንዲያደርግ ያበረታታል፡፡ ሳይፋቱ ፍቺ የተወሰነባቸውን ጉዳዮች በጥሞና ለተመለከተ ሰው አብዛኛዎቹ የተከሰቱት ከ30 ወይም 40 ዓመታት በፊት በተፈጸሙ ጋብቻዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የነበረው የአገራችን ሁኔታ ከመደበኛው ሕግና ሥርዓቱ ይልቅ ልማዳዊ አስተሳሰብና አሠራር የገነኑበት ነው፡፡ ዘመናዊ ሕግጋት ቢኖሩም ልማድ የሸፈናቸውና የአፈጻጸም ክፍተት እንቅፋት የሆናቸው ነበሩ፡፡ የአሁኖቹ ፍርድ ቤቶቹ ፍርድ ሲሰጡ ያለፈውን ትውልድ ቅርስ ለማስቀጠል ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን ተተኪ አስተሳሰብ ለመወሰን (ድርጊቱን ለመግራት) ሊሆን ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከድሮው በተለየ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ (ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት) ለመመዝገብ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የተቀረጸበት ዘመን በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ተስፋ እንዳላቸው አስቦ ኅብረተሰቡ ፍቺን በፍርድ ቤት እንዲፈጽም ማበረታታት ተገቢ ይሆናል፡፡

የሰበር ችሎቱ ደረቁን ሕግ ገለል በማድረግ ወደ ኅብረተሰቡ ሃቅ መሄዱ በሳይፋቱ ፍቺ ብቻ ሳይሆን የፍቺ ውጤቶችንም በመወሰን ይንፀባረቃል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ችሎቱ በሰበር መዝገብ ቁጥር 43988 መስከረም 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የሰጠው አስገዳጅ ትርጉም ነው፡፡ ይህ ፍርድ የተሰጠው ሁለት ሚስቶች ያሉት ወንድ የንብረት ክፍፍል በሚወሰንበት አግባብ ነው፡፡ ችሎቱ በሰጠው ፍርድ ‹‹ጋብቻው በተገቢው መንገድ ሳይፈርስ ጋብቻውን ትቶ የሄደ ተጋቢ ጋብቻውን ትቶ በሄደበት ወቅት ሌላው ተጋቢ ያፈራውን ንብረት የጋብቻ ውጤት ነው በማለት እንዲካፈል መፍቀድ ተገቢ አይደለም፤›› ብሏል፡፡ ይህ የችሎቱ አቋም ከሕጉ ጥሬ ንባብ ያፈነገጠ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕጉ ጋብቻ በንብረት በኩል የሚኖረውን ውጤት ለመወሰን የተጠቀመበት መሥፈርት በዋናነት ንብረቱ የተፈራው በጋብቻ ውስጥ ነው ወይስ ከዚያ በፊት የሚለውን ነጥብ መሠረት በማድረግ መሆኑን ከቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 57 መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ በማይጣጣም መልኩ ንብረቱ በጋብቻ ሲፈራ ሌላኛው ተጋቢ በአካል ስለመገኘቱና አለመገኘቱ ወይም በንብረቱ መፈራት ያለው አስተዋፅኦን ማጣራት ሕጉ ለዳኞች ከፈቀደው ሥልጣን መውጣት ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋም ከችሎቱ በዘለለ በአንዳንድ የሕግ ምሁራንም እንደሚታመንበት አቶ ፊሊጶስ በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ምሁራን ባልና ሚስት በተለያዩበት ዘመን በግላቸው ያፈሩት ገቢ ወይም ሀብት ፍቺ ባለመፈጸሙ ብቻ የጋራ ይሆናል ማለት አይደለም ይላሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት አቋም ከሕጉ ይዘት መዝለልን ያስከትላል፡፡ ፍቺ በፍርድ ቤት እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ተጋቢዎች በጋብቻ ውስጥ ያፈሩት ንብረት የጋራ መሆኑ በግልጽ በሕጉ ተቀምጧል፡፡

ይህንን ነጥብ ለማጠቃለል ያህል ሕጉ ፍቺንና ውጤቱን የመወሰን ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች የሰጠ በመሆኑ፣ ሕጉ ባልተሻሻለበት ሁኔታ ተጋቢዎች ለዓመታት መለያየታቸውን ለፍቺ ማስረጃ ማድረግ አሳማኝ አይሆንም፡፡ ሕጉ ባለበት አኳኋን ኅብረተሰቡ ሕጉ ባስቀመጠው ሥርዓት ጋብቻውን ለማፍረስ ከፈለገ ፍርድ ቤቶችን እንዲጠቀም ማበረታታት፣ ማገዝ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ በአደባባይ የሚፈጸም ጋብቻ በየቤቱና በየመንገዱ እንዲፈታ መፍቀድ ነው፡፡

የችሎቱ አቋም ክፍተቶች

ከሰበር ችሎት ፍርዶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው የተለያየ ሁሉ ተፋትቷል ወደሚል መደምደሚያ አያደርሰንም፡፡ ችሎቱ ልዩ ሁኔታዎችን በግልጽም በተዘዋዋሪ መንገድም አስቀምጧል፡፡ ቀዳሚው ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 14290 በተዘዋዋሪ (Indirectly) ያስቀመጠው ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ ተጋቢዎች ለዓመታት ተለያይተው እየኖሩ ያሉት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሆነ ሳይፋቱ ፍቺ አይኖርም፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት የሚለው ትርጉም አከራካሪ ቢሆንም የተለያዩት አብሮ መኖራቸውን ባቋረጠ ከሁለቱም አቅም በላይ የሆነ ምክንያት ከሆነ ጋብቻው እንደልተቋረጠ ግንዛቤ ይወስዳል፡፡ ለአብነት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አዲስ አበባና አስመራ በመኖር ለ20 ዓመታት የተለያዩ ተጋቢዎች መለያየታቸው ለመፋታታቸው አስረጅ አይሆንም እንደማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ ሁኔታ በሰበር መዝገብ ቁጥር 67924 በተሰጠው ፍርድ መሠረት የተጋቢዎቹ ግንኙነት አለመቋረጥ ባላቸው ማኅበራዊ ትስስር ሲረጋገጥ ነው፡፡

እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ቀደም ሲል ከተሰጡት ፍርዶች አንፃር ፍትሐዊ ናቸው፡፡ ሰበር ችሎቱ ያለፍርድ ቤት ፈቃድ የተደረገ ፍቺን የመቀበሉ የሕግ አግባብነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉንም ጉዳዮች በተመሳሳይ መርህ አለመዳኘቱ ፍትሐዊ ነው፡፡ ባልና ሚስቶች ተለያይተው እየኖሩ ግን በዕድር፣ በማኅበር፣ በሐዘን፣ በደስታ በአንድም በሌላ በሚገናኙበት ጊዜ ግንኙነቱ እንዳልተቋረጠ ግንዛቤ መውሰድ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ችሎቱ በፍርዱ ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለመወሰን አስቸጋሪና ተጨማሪ ልዩ ሁኔታዎችን እንዳያሰፉ ሥጋት አለ፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑ መጠይቆችን በማንሳት የችግሩን አሳሳቢነት እናመልክት፡፡ ተጋቢዎች ምን ያህል ዓመት ከተለያዩ በኋላ የሚቀርብ ጥያቄ ነው በ‹‹ሳይፋቱ ፍቺ›› ሥር የሚወድቀው? ማኅበራዊ ትስስር ምን ምን ሁኔታዎች ያካትታል? ከደብዳቤ፣ ፎቶ፣ ዕድር፣ ማኅበር ሌላ ተለያይተው ለልጆቻቸው የማያደርጉት አስተዋጽኦስ ትስስሩን ያስረዳል? አንዳንዴ በእውነት (Defacto) የተለያዩ ባልና ሚስት ለልጆቻቸው አስተዳደግ እንዲመች በማለት ብቻ አብረው የሚውሉበት አልፎ አልፎም የሚያድሩባት ወዘተ. አጋጣሚ መኖሩ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሁለቱ ተጋቢዎች በየፊናቸው ሕይወት የመጀመራቸው ነገር ልዩ ሁኔታ አይኖረውምን? ለምሳሌ ባል በተለያዩበት ዓመታት ሌላ ትዳር ቢመሠርት ግን ከቀድሞዋ ጋር አልፎ አልፎ ቢገናኝ፣ የአስቤዛ ወጪ ቢሰጥ፣ በዕድር በማኅበር ተመዝግቦ ቢገኝ ማኅበራዊ ትስስሩን በተሻለ አያስረዳምን?

የሰበርን አካሄድ መሠረት ካደረግን ብዙ ሁኔታዎች በልዩ ሁኔታው የሚሸፈንበት አጋጣሚ ይሰፋል፡፡ ይህም የሰበሩን መርህ ልዩ ሁኔታ፣ ልዩ ሁኔታውን መርህ የማድረግ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ፣ መያዣ፣ ስጦታ ወዘተ. የፎርማሊቲ መሥፈርት ጋር በተየያዘ ሰበር የሰጣቸው ፍርዶች ለዚህ መደምደሚያ ማጠናከሪያ ይሆናሉ፡፡ ችሎቱ በመጀመሪያ ፍርዶቹ ለሕጉ በመወገን ብዙ ውሎች እንዲፈርሱ አድርጎ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ልዩ ሁኔታዎቹ በመስፋታቸው መርሁ ልዩ ሁኔታ ሆነ፡፡ በማኅበራት ቤት፣ በስጦታ ውል፣ በተዋዋዮች መካከል ወዘተ. የፎርም መሥፈርት በልዩ ሁኔታ ታይቶ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ሁለተኛውንም ምልከታ ለማጠናቀቅ እንሞክር፡፡ ሰበር ችሎቱ በልዩ ሁኔታ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ተጋቢዎች ሲለያዩና ማኅበራዊ ትስስራቸው የፀና ከሆነ ግንኙነቱ ላለመቋረጡ አስረጅ መሆኑ ፍትሐዊ ነው፡፡ ሆኖም ልዩ ሁኔታው መኖሩን ማስረዳት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ልዩ ሁኔታውን ያሰፋዋል፡፡ የሕጉ መሻሻል ችሎቱን ካልጠራው አቋሙ ያወጣዋል፡፡ አቶ ፊሊጶስ እንደጠቆሙት ለባህልና ሃይማኖት ጉዳዮች ከፍርድ ቤት ውጭ ፍቺ የሚፈፀምበት ሁኔታ ቢደነግግ፣ ለረዥም ጊዜ የተለያዩ ባለትዳሮች ሁኔታ የሚታይበት የሕግ ግምት በሕጉ ቢካተት ችግሩን ሊቀርፈው ይችላል፡፡ ሕጉ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ሕጉ በኅብረተሰቡ የሚታወቅበትን ሁኔታ በማስፋት በማንኛውም ጊዜ ፍቺ በፍርድ ቤት ብቻ እንዲከናወን ወደሚደረግበት አሠራር ብንመለስ ብልህነት ነው፡፡ የትውልዱ መዘመን፣ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መምጣት ይህንን መንገድ ብሩህ ያደርገዋል፡፡  

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

       

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...