Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዚካና የሪዮ ኦሊምፒክ

ዚካና የሪዮ ኦሊምፒክ

ቀን:

በአሸናፊ ዋቅቶላ (ዶ/ር)

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በጁን 9 ቀን 2016  ባወጣው የዚካ ወቅታዊ ሁኔታ ዘገባ ውስጥ፣ እስከ ጁን 8 ቀን 2016 ድረስ 60 አገሮችና ግዛቶች (ቴሪቶሪስ) በቢንቢ የሚተላለፍ የዚካ በሽታ እንደተገኘባቸው አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ 46 አገሮች የመጀመርያው የዚካ ወረርሽኝ የተከሰተባቸው ከ2015 በኋላ ነበር። 14 አገሮች የዚካ ቫይረስ ወረርሽኝ ከ2007 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ የታየባቸው ሲሆን፣ አሁንም የዚካ ቫይረስ በቢንቢ አማካይነት እየተላለፈባቸው ነው። በተጨማሪም አራት አገሮችና ግዛቶች ከ2007 እስከ 2014 ድረስ የዚካ ቫይረስ ወረርሽኝን አሳይተው በአሁኑ ጊዜ ግን የዚካ ትልልፍ የማይታይባቸው ናቸው። እነኚህ ኩክ አይላንድስ፣ ፍሬንች ፖለኔዝያ፣ ኢስላ ደ ፓስኳ ቺሌና የማይክሮኔዥያ ፌደራላዊ አገዛዝ ያፕ ደሴቶች ናቸው። ሌሎች አሥር አገሮች ደግሞ ከሰው ወደ ሰው (ምናልባትም በግብረ ሥጋ ግንኙነት) የዚካ መተላለፍን አሳውቀዋል።

 የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) በድረ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው እስከ ጁን 15 ቀን 2016 ድረስ በስቴቶችና ዲሲ ውስጥ 756 ሰዎች የዚካ ቫይረስ እንደያዛቸው ሲዘገብ በሠፈራዊ (ሎካል) ቢንቢ ንክሻ የተላለፈው ቁጥር 0 (ዜሮ) ነው። ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ ዲሲ 6፣ ሜሪላንድ 25 እና ቨርጂኒያ 26 የዚካ ቫይረስ በሽታ ታማሚዎችን ዘግበዋል። ከ756ቱ 755 ሰዎች በሽታውን ያገኙት ከጉዞ ጋር ተያይዞ ሲሆን፣ አንድ ሰው በላቦራቶሪ ሥራ ምክንያት ተይዟል። ከ755ቱ ውስጥ 11 በግብረ ሥጋ ግንኙነት የተገኙ ናቸው። ሌሎቹ የዩኤስ ግዛቶች (ማለትም ከስቴቶችና ዲሲ ውጪ ያሉት) 1,440 የዚካ ሕመምተኞችን አስታውቀዋል። ከእነኚህ ውስጥ 1336 በሠፈራዊ ቢንቢ ንክሻ ሲተላለፉ አራት ሰዎች ደግሞ በሽታውን ያገኙት ከጉዞ ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ እስከ ጁን 9 ቀን 2016  ድረስ የዚካ ቫይረስ በላቦራቶሪ ምርመራ የታየባቸው እርጉዞች ቁጥር በዩኤስ ስቴቶችና ዲሲ 234 ሲሆኑ በዩኤስ ግዛቶች ደግሞ 189 ናቸው።

 የዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት ክልላዊ ድርጅት ፓሆ (ፓን አሜሪካን ኼልዝ ኦርጋናይዜሽን) የዚካን ወቅታዊ ሁኔታ በድረ ገጹ ላይ በጁን 9 ቀን 2016 ሲያቀርብ የገለጸው በማዕከላዊና በደቡባዊ አሜሪካ በቢንቢ ንክሻ የሚተላለፉ በሽታዎች የዓየር ፀባይ የሚወስናቸው በመሆኑ፣ የዚካ በሽታ የታየባቸው ሰዎች ቁጥርም እየቀነሰ መሆኑን ገልጿል። ከብራዚል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቀረበለትን ዘገባም በግራፍ አቅርቧል። በሌላ በኩል ደግሞ በካሪቢያን የሚገኙት አብዛኛዎቹ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ በዚካ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጠን እየጨመረ መሄዱን ገልጿል።

 ዚካ አፍሪካ በር ላይ

የአፍሪካ አኅጉር ክፍል በሆኑት የኬፕ ቨርዴ ደሴቶች ውስጥ የዚካ ቫይረስ በሽታ በቢንቢዎች አማካይነት እየተላለፈ መሆኑ ይታወቃል። በሜይ 20 ቀን 2016 በዓለም ጤና ድርጅት የተገለጸው ኬፕ ቨርዴ ውስጥ የሚተላለፈው የዚካ ቫይረስ የእስያ ዓይነት (አፍሪካ በቀል ሳይሆን) እንደሆነና ምናልባትም ከብራዚል የሄደ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው። እግረ መንገዱንም የቫይረሱ ወረርሽኝ አፍሪካ በር ላይ መድረሱን አስታውሶ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ መክሯል።

የዘገየ ግብረ ሥጋ ትልልፍ

ዋነኛው የዚካ ቫይረስ መተላለፊያ በኤዲስ ቢንቢ ንክሻ ቢሆንም፣ በሌሎችም መንገዶች እንደሚተላለፍ ተረጋግጧል። ከእነኚህ ውስጥ መከላከያ የሌለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት አንዱ ሲሆን፣ ቫይረሱ የወንድ ፍሬዘር (ሲመን) ውስጥ እስከ 62 ቀናት ውስጥ መቆየት ይችላል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተዘገበው ወንዱ ከዚካ ቫይረስ ሕመም ከ19 ቀናት በኋላ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ መቻሉን ነበር። አሁን ደግሞ ከ44 ቀናት በኋላ ቫይረሱ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አማካይነት መተላለፍ መቻሉ ተረጋግጧል። በዚህ ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅቶች ከዚካ ቫይረስ ሕመም በኋላ የሚያስፈልገውን መከላከያ የሌለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማስወገድ ወይም ከግብረ  ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ጥንቃቄ እስከ ሁለት ወራት እንዲራዘም መክሯል። እስካሁን ድረስ የዚካ ቫይረስ ከወንዶች ወደ ግብረ ሥጋ ጓደኞቻቸው መተላልፍ መቻሉ ቢረጋገጥም፣ ከሴት ወደ ወንድ መተላለፉ አይታወቅም።

ማይክሮኬፋሊና ሌሎች የነርቭ ሥርዓት መዋቅራዊ (ስትራክቸራል) መስተጓጉሎች

  ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን የተሰኘው የሕክምና መጽሔት በጁን 15 ቀን 2016 በኮሎምቢያ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው የዚካ ቫይረስ በሽታ ጊዜያዊ ዘገባ አቅርቧል። እዚህ ውስጥ ከተገለጹት ብዙ ነገሮች ዋነኛውና ትኩረትን የሳበው ጉዳይ በሽታው የተገኘው በሦስተኛው የእርግዝና ወቅት (ሰርድ ትራይሜስተር፣ የመጨረሻው ሦስት ወር) ውስጥ ከሆነ ማይክሮኬፋሊ (የጭንቅላት መጠን መቀነስ) እና ሌሎቹ የነርቭ ሥርዓት መስተጓጉሎች መጠን ምን ያህል ይሆናል? የሚለው ነው። 1,850 እርጉዞች የሚገኙበትና ከ90 በመቶ የሚሆኑት የዚካ ቫይረስ የያዛቸው የእርግዝና ሦስተኛው ሲሶ ወቅት የሆኑበት የጥናት ንዑስ ቡድን (ሰብግሩፕ) ውስጥ አንድም ማይክሮኬፋሊ ወይም ሌላ መዋቅራዊ የነርቭ ሥርዓት መስተጓጉሎች አልተገኘባቸውም። ይህ የሚያሳየው በዚካ ቫይረስ በሽታ ምክንያት የሚደርሱት የነርቭ ሥርዓት ጉድለቶች በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰቱት በበሽታው የሚያዙት በእርግዝና መጀመሪያዎቹ ወራት ሲሆን መሆኑን ነው።

የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ

የሪዮ ኦሊምፒክና ፓራሊምፒክ ውድድሮች ‹‹አዲስ ዓለም›› በሚል መሪ ቃል ከኦገስት 5 ቀን 2016 እስከ ኦገስት 21 ቀን 2016 እና ከሴፕቴምበር 7 ቀን 2016  እስከ ሴፕተምበር 18 ቀን 2016  ሪዮ ዲጀኔሮ ብራዚል ውስጥ ይደረጋሉ። ከ200 በላይ ከሚሆኑ አገሮች የሚመጡ 10,000 ግድም ተወዳዳሪዎች 500,000 የሚሆኑ ጎብኚዎች ይጠበቃሉ።

በታይም መጽሔት ድረ ገጽ ላይ በሜይ 10 ቀን 2016 እንደታተመው፣ የኦቶዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አሚር አታራን የዚካ ቫይረስ በሽታ ከሁሉ ይበልጥ ባጠቃት ብራዚል ውስጥ ሊፈጸም የታቀደው የኦሊምፒክ ዝግጅት ወደ ሌላ ጊዜ ይተላለፍ ወይም ጭራሹኑ ወደ ሌላ አገር ይዛወር የሚል ሐሳብ ማቅረባቸው ይታወቃል። ከዚህም ጋር ተያይዞ 150 የሚሆኑ ደጋፊ የጤና ባለሙያዎችና ሳይንቲስቶች የአታራንን ሐሳብ በመደገፍ ለዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል። በመቀጠልም የራሳቸውን ድረ ገጽ አቋቁመው ተጨማሪ ደጋፊዎች እያሰባሰቡ ናቸው።

    በዚህ ጉዳይ ላይ በእንዲህ እንዳለ ዋና ዋናዎቹ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶችና ምናልባትም የዚካ ወረርሽኝን በቅርብ የሚከታተሉ የኅብረተሰብ ጤና ምሁራንና ሳይንቲስቶች የሚያምኑት የብራዚል ኦሊምፒክ ውድድሮችን ለመሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ የኅብረተሰብ ጤና ምክንያት እንደሌለ ነው። ይህን ጉዳይ ለመረዳት ዋናው ጥያቄ ምን እንደሆነ በቅጡ ማጤን ያስፈጋል። የዚካ ቫይረስ በሽታ ከላይ እንደተገለጸው በብዙ አገሮች ውስጥ ተሰራጭቷል። የዓለም ሰፊና ፈጣን የጉዞ መገናኘቶች ከዚህ ይበልጥ እንዲስፋፋ እንደሚያደርገው የሚጠራጠሩ ካሉ ሲጽፉ ወይም ሲናገሩ አይሰሙም። ዋናው ጥያቄ በብራዚል ውስጥ የተዘጋጁት የኦሊምፒክና የፓራሊምፒክ ውድድሮች በተሳታፊና የኦሊምፒኩ ጎብኚዎች ላይ የሚያስከትሉት የዚካ ቫይረስ በሽታ መያዝ ሥጋትና ወደ አገሮቻቸው ሲመለሱ በከፍተኛ ደረጃ የማስተላለፋቸው አደጋ ምን ያህል ነው? የሚለው ነው።

እጅግ ከፍተኛው የዚካ ቫይረስ በሽታ መተላለፊያ መንገድ የኤዲስ ቢንቢ ንክሻ ነው። ይህ ቢንቢ ከዚካ ሌላ ደንጊ የተባለውን በሽታና ሌሎችን ያስተላልፋል። እ.ኤ.አ. በ2014 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በተደረገበት ጊዜ ከ600 ሺሕ በላይ ሰዎች ከዓለም ዙሪያ ወደ ብራዚል ሲጎርፉ ብዙዎች በደንጊ በሽታ ተይዘው ወደ አገሮቻቸው ያሰራጩታል የሚል ሥጋት በ2013 ተገልጾ ነበር። ይህንን ሥጋት አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት ያቀረቡት ባለሙያዎች የደመደሙት ከዓለም ዋንጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የደንጊ በሽታ መያዝ ከሦስት እስከ 59 ቢደርስ ነው ብለው ነበር። እንዳሉትም ውድድሩ ሲፈጸም በደንጊ መያዝ የተዘገበው ሦስት ሰዎች ላይ ነበር። ለዚህ ዋናው ምክንያት የዓለም ዋንጫ ወድድሮቹ የተካሄዱት በብራዚል ቀዝቃዛ ወቅት በመሆኑና ደንጊን የሚያስተላልፉት ቢንቢዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ስለሚሆን ነው። በተጨማሪም እነኚሁ አጥኚዎች በጁን 17 ቀን 2016  ዘላንሴት የሕክምና መጽሔት ላይ ያሰፈሩት በእነሱ ግምት የዚካ ቫይረስ በሽታ ሥጋት በ2016 ኦሊምፒክ ጊዜ ከደንጊ ቫይረስ በሽታ መያዝ ጋር ሲወዳደር በ15 ጊዜ እጥፍ የሚቀንስ መሆኑን ነው።

 የዓለም ጤና ድርጅት ሦስተኛው የአጣዳፊ ሁኔታ ኮሚቴ በጁን 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ላይ ከሪዮ ኦሊምፒክ ጋር ተያይዞ ሊመጣ ስለሚችለው የዚካ ቫይረስ በሽታ መያዝና መስፋፋት ላይ ከሌሎች ዚካ ነክ ጉዳዮች ጋር አንስቶ ነበር። በዚህ ላይም ጋዜጣዊ መግለጫና ከዓለም ዙሪያ በስልክና በኢሜይል በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ መልስ ተሰጥቷል፡፡ መደምደሚያው በኦሊምፒኩ ሳቢያ የሰዎች በዚካ ቫይረስ በሽታ መያዝና በዓለም ላይ ይበልጥ መሰራጨት አደጋ አነስተኛ እንደሆነ ነው።

ማጠቃለያ

ዚካ በብዙ የዓለም ክፍሎች ተሰራጭቷል። ቢያንስ ቢያንስ በሽታውን ሊያስተላልፉ የሚችሉት ቢንቢዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ይበልጥ የመስፋፋቱ ሥጋት ከፍተኛ ነው። ስለዚካ ቫይረስ በሽታ ብዙ ቢታወቅም አሁንም ገና ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። መድኃኒት የለውም። ክትባቶች ተጠንተው ለሕዝብ እስከሚቀርቡ ዓመታትን ይወስዳሉ። እስከካሁን ያለው መረጃ የሚያሳየው በሪዮ ኦሊምፒክ ምክንያት የዚካ ዓለም ላይ መሰራጨት አደጋ ዝቅተኛ መሆኑን ነው። የትኩረትን አቅጣጫ ቶሎ በማስተካከል የዚካ ቫይረስ በሽታ ዓለም ላይ ከፍተኛ አደጋን እንዳያስከትል አቅምን ማጠናከርና ለሕዝቡ ከፍተኛ ትምህርትን ማቅረብ ያስፈልጋል። የአዲስና የተመላሽ ተላላፊ በሽታዎች መከሰትና መሰራጨቶች እየከፉ እንጂ እየቀነሱ ስለማይሄዱ በዓለም አቀፍም ደረጃ ሆነ በየአገሩ ልዩና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...