Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢንዱስትሪዎች ተፅዕኖን በሚመለከት የሚሠሩ ጥናቶች ችግር አለባቸው ተባለ

የኢንዱስትሪዎች ተፅዕኖን በሚመለከት የሚሠሩ ጥናቶች ችግር አለባቸው ተባለ

ቀን:

በመላ አገሪቱ የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማና የማማከር ሥራ ከሚያካሂዱ 436 ድርጅቶችና ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ የአቅም ውስንነት፣ የሥነ ምግባርና በሌሎች ባለሙያዎች ቀደም ሲል ተሠርተው የተጠናቀቁ የግምገማ ውጤቶችን የራስ አስመስሎ (ኮፒ ፔስት) የማቅረብ ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ አስታወቀ፡፡

ይህም ሊታወቅ የቻለው ከክልል የአካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች፣ እውቅና ከተቸራቸው የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜአት በተደረጉ ውይይቶች እንዲሁም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችም በየክልሉ ተዘዋውረው ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት መሠረት መሆኑን አቶ ዮሐንስ አመሀ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአካባቢ ፈቃድ አሰጣጥ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የአቅም ውስንነት ከተንፀባረቀባቸው ሁኔታዎች መካከል በማዕድን ላይ ሊጠቀሙ የሚችሉትን የኬሚካሎች መጠን፣ አደገኛነትና ዝርዝራቸውን እንዲሁም በአካባቢና በሰው ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳቶች መጠቆም አለመቻላቸው ይጠቀሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለአንድ ፕሮጀክት ተግባራዊነት የተመረጠው ቦታ ለኢንዱስትሪ እንደማይሆን እያወቁ ይህን ችግር ሳይጠቅሱ የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ አጥንተው ማቅረባቸው አማካሪ ድርጅቶቹ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው ያሳያል ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመጥቀስ የቦታ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ማቅረብ ሲኖርባቸው በተቃራኒው ግን የተያዘው ቦታ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ተስማሚ ነው የሚል ሰነድ እንደሚያቀርቡ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

አማካሪ ድርጅቶቹም ሆነ ጥናት የሚሠሩት ግለሰቦች ማኅበር ስለሌላቸው ከጥናቶች ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውን ችግር መቅረፍ አለመቻሉ ተነግሯል፡፡ ፕሮጀክቱን የሚተገብረው አካል ምን ያህል ወጪ እንደሚያስወጣው የማወቅ መብት ቢኖረውም አጥኚዎቹ ይህንን እያሳወቁት እንዳልሆነና ይህም የፕሮጀክቱ እቅድ ለአግባቡ እንዳይተገበር መሰናክል እንደሆነ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ እንደተገለጸው ሕግ አክብረው የሚሠሩ አጥኚ ድርጅቶች ቢኖሩም በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ጉድለት የሚታይባቸው ነገር ግን በኃላፊነት ስሜት የሚሠሩ ብዙ ሲሆኑ በአፈጻጸም የጎላ ጉድለት የሚታይባቸውም አሉ፡፡

ወይዘሮ ሮማን ካሳሁን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተግባሪ አካላት ፕሮጀክት ክትትል፣ ግምገማና ፍቃድ መስጠት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አካባቢን በሚመለከት የወጡ የሕግ ማዕቀፎችን አስመልክተው ባደረጉት ገለጻ፣ አንድ የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ወደ ሥራ መግባት ይኖርበታል፡፡ ከሕዝቡ ጋር የሚደረግ ምክክርም ከአካባቢና ማኅበረስብ ተፅዕኖ ግምገማ ተግባር ተለይቶ ሊታይ አይችልም፡፡ ግምገማው ለውሳኔ ሰጪዎች ከመቅረቡ በፊት በገለልተኛ አካል መታየቱና የሕዝብ ተሳትፎና አስተያየት ማካተቱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡

በድርጅትና በግለሰብ ደረጃ የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ሥራ ለመሥራትና ለማማከር ፈቃድ ከወሰዱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሰብሰባ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ በግምገማውና በማማከሩ ሥራ ላይ የታዩት በርካታ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ተንፀባርቀዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊዎች ከተንፀባረቁት ተግዳሮቶች መካከል የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይካሄድባቸው ወደ ልማት እንዳይገቡ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በአብዛኛው የሚበረታው በግል ባለሀብቶች ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምንም ዓይነት ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ፕሮጀክቶቻቸውን ራሳቸው ግምገማው ራሳቸው እንደሚያፀድቁና እንደሚተገበሩ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡

አቶ ቃሬ ጫዊቻ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ለማድረግ ፍቃድ የመስጠት ኃላፊነቱ በአዋጅ የተሰጠው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶች ከሚኒስቴሩ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ተራ ወይም ወረፋ እንዳይጠብቁ ሲባል የተሟላ አደረጃጀትና ተቋማዊ አቅም ላለቸው ስድስት የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ፈቃድ እንዲሰጡ መወከላቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህ ሲባል ደግሞ ተጠያቂነት ከአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሂዷል ማለት እንዳልሆነ፣ በተረፈ ውክልና የወሰዱትም ሆነ ሎሎች ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የአካባቢና የማኅበረሰብ ተጽእኖ ግምገማ ለማካሄድ ሕጋዊ መሠረት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

የአካባቢና የማበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ መመሪያ ወቅታዊና ሊያሠሩ የሚችሉ በርካታ ሐሳቦች እንዳሉት ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው እነዚህን ሐሳቦችና ነጥቦች አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ከዓለምና አገር አቀፍ ሁኔታዎች አንፃር ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ‹‹የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማና ከዛም ቀጥሎ ያለው ሥራ እንደየትኛውም ቢዝነስ የሚታይ ሳይሆን ከሰው ልጅ ሕይወትና ከአካባቢ ሕልውና ጋር የተቆራኝ ወይም የተሳሰረ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የሚጠይቀው ትልቅ መስዋዕትነት አለ፤›› ብለዋል፡፡

ገንዘብ ለማግኝት ሲባል ብቻ የሚሠራ ከሆነ ከአካባቢና ከዚህም ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወንዞች፣ ሐይቆች፣ አፈር፣ ውኃና አየር ሁሉ ክፉኛ እንደሚበከሉና ብክለቶቹ አንዳንዶቹ ወዲያው የቀሩት ደግሞ ቆይተው እንደሚታዩ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልትን በመተግበር 283 ሚሊዮን ሜትራክ ቶን ይደርስ የነበረውን የአካባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ከ136 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ እንዳይሆን ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁለም የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች በእቅዳቸው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥልትን በማካተት መተግበር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...