Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​​​​​​​የደብረ ማርቆሱ ‹‹መቀነት››

​​​​​​​የደብረ ማርቆሱ ‹‹መቀነት››

ቀን:

የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሃዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ያዘጋጀውን ዓመታዊ ጉባዔ ለመታደም ወደ ከተማው ያመሩ ሰዎች በሆቴሉ ተሰብስበው ያወጋሉ፡፡ ደብረማርቆስ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ነው፡፡ ከጉባዔው ተሳታፊዎች አንዱ ዋሽንት ተጫዋቹ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ በብዛት ከእጁ የማይነጥላትን ዋሽንት ይዟል፡፡ በጨዋታ መሀል ስለ በላይ ዘለቀ ተነሳ፡፡ ጨዋታው የሳበው ዮሐንስ፣ ድንገት ጆሮ ሳቢ ዋሽንቱን እየነፋ ጨዋታውን ያጅብ ጀመር፡፡ የበላይ ጀግንነት ወሬ በሽለላ ሙዚቃ ማጀቢያነት ደራ፡፡

ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ድንገት አንድ ወጣት ተነስቶ ሁሉም ሊያዩት በሚችሉበት ቦታ ቆመ፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ፀጥ አለና በጌትነት እንየው ተውኔት ላይ ያለውን የበላይ ዘለቀ ሞኖሎግ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ትወናውን የጠበቀ ስላልነበረ ሁሉም ወጣቱን በመገረም ያዩታል፡፡ ጥቂት ሲቆይ የወጣቱ በስሜት የተሞላ ትወና አስደስቷቸው በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገለጹለት፡፡

ወጣቱ አቤል ብርሃኔ ይባላል፡፡ ጎጃም ካፈራቸው አማተር ተዋንያን አንዱ ነው፡፡ ከአካባቢው ከወጡ አንጋፎች መካከል የሚወደው ጌትነት እንየውና በጀግንነቱ የሚያከብረው በላይ ዘለቀን በአንድ ላይ የሚያወሳበት ሞኖሎግ ስሜቱን እንደሚነካው ይናገራል፡፡ ለመተወን በተዘጋጀባቸው መድረኮች ብቻ ሳይሆን ሆቴል ውስጥ እንደነበረው ዓይነት ድባቦች ላይ በድንገት መተወንም ያስደስተዋል፡፡

የ26 ዓመቱ አቤል ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ‹‹መቀነት›› የተሰኘ የቴአትርና ሥነ ጽሑፍ ክበብ ያቋቋመ ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉ የቴአትር ፍቅር ያላቸውን ወጣቶች አሰባስቧል፡፡ በተጨማሪም ደብረማርቆስ በሚገኙ አሥር ትምህርት ቤቶች አሥር የቴአትር ክበቦች እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ መደበኛ የቴአትር ትምህርት ባያገኝም፣ በአጫጭር ሥልጠናዎችና በንባብ የቴአትር ዕውቀቱን ለማዳበር ይሞክራል፡፡ ያገኘውን ዕውቀት ላሰባሰባቸው ወጣቶች ያካፍላል፡፡ እዛው ደብረ ማርቆስ ውስጥ ወይም በሌሎች ከተሞችም መድረክ እንዲያገኙ መሯሯጥ የዘወትር ተግባሩ ነው፡፡ መድረክ ሲያገኙ ደግሞ የቴአትር ጽሑፍ፣ ዝግጅት፣ አርትኦት፣ አልባሳት፣ ገፀ ቅብና የመድረክ ግብዓት ኃላፊነቶቹ ይሆናሉ፡፡

40 አባላት ያሉትን ‹‹መቀነት›› ለመመሥረት የወሰደበት ጊዜና ጉልበት ቀላል አልነበረም፡፡ በእርግጥ የጥበብ ፍቅር ያደረበት ቴአትር ምን እንደሆነ ከማወቁ በፊት ነበር፡፡ የተወለደው ጐዛምን ወረዳ ደለደል ማርያም የተባለ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ አርሶ አደሮች ሲሆኑ፣ ለቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ በልጅነቱ ከብት ሲጠብቅ ያንጎራጉራቸው ለነበሩ ዘፈኖች ልዩ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ የማኅበረሰቡ አኗኗርም ዛሬ ለሚሠራቸው ቴአትሮች ግብዓት ሆነውታል፡፡ ‹‹ሕዝቡ ሲያደርግ የማውቃቸውን ነገሮች ወደ መድረክ አምጥቼ መሥራት እፈልጋለሁ፤›› ይላል፡፡ ማንነቱን የሚገልጹ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ጥበባዊ ሥራዎች ይማርኩታል፡፡

ሁሌም ወደኋላ መለስ ብሎ ከሚያስታውሳቸው ነገሮች ከብቶች ሲጠፉበት ያደርግ የነበረው ይገኝበታል፡፡ ለምሳሌ የፍየል ግልገል ሲጠፋበት የእናት ፍየል ድምፅ አስመስሎ ይጮሃል፡፡ ከብት ሲጠብቅ ውሎ ሲያድር የነበረው የሌሊቱ ሁኔታም ትውስታው ነው፡፡ የዱር እንስሳት ሊመጡ ይችላሉ የሚለው ፍርሃት ቢኖርም፣ ከሌሎች እረኞች ጋር በመሆን ሲዘፍኑ ያድራሉ፡፡ ‹‹በአካባቢያችን ከብት ስንጠብቅ፣ ሰው ሲዳር፣ በዓላት ሲመጡና ሌሎችም ማኅበራዊ መስተጋብሮች ለሙዚቃ፣ ውዝዋዜና ሌሎችም ጥበባዊ ሥራዎች ያነሳሳሉ፤›› ይላል፡፡

ዘጠነኛ ክፍል ሲደርስ ለትምህርት ወደ ደብረ ማርቆስ ሄደ፡፡ የከተማ ኑሮ እንግዳ ስለሆነበት ከሰዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የከተሜነት ኑሮን ለመልመድ ጊዜ ወስዶበታል፡፡  ወቅቱ የቴአትር ዝንባሌው እያደገ የመጣበትም ነበር፡፡ አሥረኛ ክፍልን ሲጨርስ ኪያሜድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብቶ የሕክምና ትምህርት ተከታተለ፡፡

ሲማር ያሰላስል የነበረው ቴአትር የመሥራት ህልሙን የሚያሳካበትን መንገድ ብቻ ነበር፡፡ ዕድለኛ ሆኖ በአንድ አጋጣሚ ሕይወቱን እስከወዲያኛው ቀየረው፡፡ የደብረማርቆስ ቤተሰብ መምሪያ ውስጥ ቴአትር የሚሠራ ጓደኛው ልምምድ ወደሚያደርጉበት ቦታ ወሰደው፡፡ በቴአትሩ የመሪጌታ ገፀባህሪ የሚጫወተው ተዋናይ በዕውን የሚያውቃቸውን መሪጌታዎች አስመስሎ እንዳልተወነ ይታዘባል፡፡ በልምምዱ መጨረሻ አስተያየት ስጡ ሲባል፣ የቴአትር ዕውቀት ላላቸው ተዋንያን ሲፈራ ሲቸር አስተያየቱን ተናገረ፡፡ የቴአትሩ አዘጋጅ ተዋናዩ እንዴት መጫወት ነበረበት ብሎ ሲጠይቀው አቤል ተውኖ አሳየው፡፡ አዘጋጁ በችሎታው ተገርሞ በተዋናዩ ቦታ ተካውና ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ ፊት ቀረበ፡፡ ቴአትሩ በምሥራቅ ጎጃም የቴአትር ፌስቲቫል ላይ አንደኛ ሲወጣ በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ እንደሆነ እንዳመላከተው ይናገራል፡፡

ከተመረቀ በኋላ በአንድ ሆስፒታል በነርስነት ቢቀጠርም፣ ሥራውን አትኩሮ መሥራት አልቻለም፡፡ የቴአትር ፍቅሩ አሸንፎት ሥራውን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡ አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የሚያስተምሩበት ተቋም ትምህርት ጀምሮ ብዙም ሳይገፋበት ወደ ደብረማርቆስ ተመለሰ፡፡ በከተማው ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች የቴአትር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ የቴአትር ክበባት ቴአትር እያዘጋጁ በተገኘው አጋጣሚ ያሳያሉ፡፡ አቤል ይህንን ዕድል ያላገኙ ነገር ግን ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን ለማሰባሰብ የወሰነውም በዘርፉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ስላመነ ነበር፡፡

ክበቡን ሲጀምር ብዙም አልነበረውም፡፡ ራሱንም ክበቡንም ለመደገፍ ባጃጅ ገዝቶ መሥራት ጀመረ፡፡ ያሰባሰባቸው ወጣቶችም ለሙያው ካላቸው ፍቅር ውጪ ከየት መጀመር እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ምሩቅ ጋብዞ ለጥቂት ወራት ሥልጠና አሰጣቸው፡፡ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መለማመጃ አዳራሽ ሰጣቸው፡፡ ነገሮች ጥሩ መንገድ ቢይዙም፣ ለቴአትር የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች ለማሟላት አቅም አልነበራቸውም፡፡ አባላቱ በየቤታቸው ያሏቸውን ቁሳቁሶች እየተጠቀሙ መሥራት ጀመሩ፡፡

በደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ ውስጥ በሚዘጋጁ ወርሃዊ የኪነ ጥበብ ምሽቶች ስለሚሳተፉ በጥቂት ሰዎች ቢታወቁም፣ ‹‹መቀነት›› የሚለው ስም ገና በሕዝቡ ህሊና አልሰረፀም ነበር፡፡ አምና ራሳቸውን ለማስተዋውቅ ለወራት የተዘጋጁበትን ቴአትር ማስተዋወቅ ሲጀምሩ ቴአትሩ ምን እንደሚያመጣላቸው አላወቁም ነበር፡፡

ለቴአትራቸው መግቢያ ትኬት ለመሸጥ ደብረማርቆስ ውስጥ ሲዘዋወሩ ለፋሲካ በዓል ወደ ደብረማርቆስ ሄዶ የነበውን ጌትነት እንየው መንገድ ላይ አገኙት፡፡ እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው ጋበዙት፡፡ ጥሪያቸውን ተቀብሎም ቴአትራቸውን ታደመ፡፡ ‹‹ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቹ ተገኝተው ነበር፡፡ ቴአትራችንን አሳይተን ስንጨርስ አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ፡፡ ጌትነትም ስለ ሥራችን ቀና ምላሽ ሰጠን፤›› ይላል አቤል ወቅቱን ሲያስታውስ፡፡

ታዋቂነታቸው እየጨመረ ሄዶ በኢትዮ ታለንት ሾው በቴአትር ተወዳድረው ምርጥ አሥር ዙር ደርሰው ነበር፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ፌስቲቫል ላይ ‹‹ፋሬስ›› በሚል ቴአትር (የክበቡ 34 አባላት የተወኑበት) ከ18 ወረዳዎች ጋር ተወዳድረው ሦስተኛ ወጥተዋል፡፡ ዘንድሮ የሃዲስ ዓለማየሁን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልቦለድ 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በደብረማርቆስ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ሃዲስ የተወለዱበትን አካባቢና በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያት ታሪክ የሚያጠነጥንባቸው አካባቢዎችን ባህል የሚያሳይ ነበር፡፡ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ተዋናይ ሚካኤል ሚሊዮንና ሌሎችም በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙበት መድረክ ነበርና የ‹‹መቀነት›› ስም ወንዝ የተሻገረበት አጋጣሚ ሆነ፡፡

ለቴአትር ሥራ ግብዓት አለማግኘት፣ የሚደግፍ ተቋም ማጣት፣ መድረክ የማዘጋጀት ውጣ ውረድና ሌሎችም ችግሮችን የተጋፈጠው አቤል፣ ‹‹የክበቤ ልጆች እርስ በርስ እንዲሁም ለሙያው ፍቅር እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፡፡ ፍቅር ስላለንም ሁሉንም ነገር ማለፍ እንችላለን፤›› ይላል፡፡ ከአባላቱ ቤተሰቦች ጋር በመገናኘት ስለአዋዋላቸው ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ በትምህርታቸው እንዳይዳከሙ ይከታተላል፡፡ በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ለማስማማት ይጣጣራል፡፡ ችግሮቻቸው ከአቅም በላይ ሆነው በምሬት ያለቀሰባቸው ቀኖችንም አይዘነጋም፡፡ ቀን ቀን ባጃጁን ሲነዳ ይውልና ማታ ማታ አባላቱን ያሠለጥናል፡፡ ምንም እንኳን ከጀመሩበት ጊዜ አንፃር ለውጦች ቢኖሩም፣ አሁንም እንቅፋቶች አሉባቸው፡፡ በአሥሩ ትምህርት ቤቶች ያቋቋማቸው የቴአትር ክበቦች አባላት ቴአትር እንዲሠሩ፣ እንዲወዳደሩና በየወሩ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ላይ እንዲሳተፉም ያደርጋል፡፡ ወጣቶቹ የ‹‹መቀነት›› አባሎች ወደሌላ ደረጃ ሲሸጋገሩ እንደሚተኩ ያምናል፡፡

ባዶ ከሚባል ነገር ተነስተው በራሳቸው ጥረት የደረሱበትን ደረጃ ጠቅሶ፣ የሚደግፋቸው ተቋም ቢያገኙ አሁን ካሉበት የበለጠ እንደሚያድጉ ይናገራል፡፡ ዛሬም ባላቸው አቅም ቴአትር ከመሥራት ወደኋላ አላሉም፡፡ አንድ ቀን እንደ ሕይወቱ እስትንፋስ የሚያየውን ቴአትር፣ ልጆቼ የሚላቸው የክበቡ አባላት አሁን ካሉበት በሰፋ ሁኔታ እንደሚሠሩ ማሰቡ ብርታት ይሰጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...