Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቶችና የጃማ ኤደን ማንነት?

አትሌቶችና የጃማ ኤደን ማንነት?

ቀን:

በዓለም የስፖርት እንቅስቃሴ በተለይ በአትሌቲክሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ጉዳይ በዓለም መነጋገሪያ ከሆኑ ትልልቅ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይኽም በአሁኑ ወቅት የወራት ሳይሆን የቀናት ዕድሜ በቀረው የሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ላይ የራሱን ተፅዕኖ አሳድሯል፣ እያሳደረም ይገኛል፡፡ ችግሩ ካጠላባቸው ጥቂት የዓለም አገሮች ደግሞ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ከተረጋገጠ ሰነባብቷል፡፡ ጥቂት የማይባሉ አትሌቶቿ በዚሁ ሰው ሠራሽ በሆነው ወረርሽኝ ተጠርጥረው ለጊዜውም ቢሆን ከማናቸውም ውድድሮች ታግደው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑ ነገሩን እያከበደው ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲና ተባባሪ አካላቱ የወሰዱትን ዕርምጃ ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ጥቂት የአገሪቱ አትሌቶች በዚሁ ለአትሌቲክሱ ትልቅ ሥጋት እየሆነ በመጣው አበረታች ንጥረ ነገር ተጠርጥረው በምርመራ ሒደት ላይ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ አገር አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ቦርድና ጽሕፈት ቤት (ናዳ) በአዲስ መልክ በማደራጀት ለእንቅስቃሴው አስፈላጊ የሆኑትን ግብዓቶች በማሟላት ላለፉት አምስት ወራት ሰፊና ጠንካራ የመከላከል ሥራ እያካሄደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በዋናነትም የማስተማር፣ ግንዛቤ የማስጨበጥና የመፍጠር እንዲሁም በአትሌቶች ላይ የምርመራ ሥራዎችን በማድረግ በአገሪቱ ንፁህ አትሌቲክስና አትሌቶች እንዲኖሩ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጭምር መግለጫቸው ጠቁሟል፡፡ ይህንኑ የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) የሥራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች በቅርብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጉት የሥራ ግምገማ፣ አገሪቱ ችግሩን ለማስወገድ በማድረግ ላይ ላለችው ጥረት ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በመጪው የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ እንደሚኖራት ማረጋገጫ የተሰጠበት አጋጣሚም እንደነበር ይታወቃል፡፡

በመጨረሻም መግለጫው ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና ከተማ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬኖች ኤጀንሲ፤ በስፔን ፖሊስና በዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት (ኢንተር ፖል) አማካይነት በትውልድ ሶማሌያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ በሆነውና በአሁኑ ወቅት በመካከለኛ ርቀት በአሠልጣኝነት በመሥራት ላይ የሚገኘው ጃማ ኤደን ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር በተያያዘ በሆቴሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበርን በመጥቀስ ይፋ አድርጓል፡፡

ግለሰቡ የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አሠልጣኝ ሆኖ የሚሠራ መሆኑ ቢታወቅም በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል ግን ምንም ዓይነት የአሠልጣኝነት ዕውቅና ያልተሰጠውና የሥራ ግንኙነትም የሌለው መሆኑን፣ በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር ተያይዞ ስሙ መነሳቱ ፌዴሬሽኑን በእጅጉ እንዳሳዘነው፣ እንደዚህም ሆኖ የአበረታች ንጥረ ነገሮችን ለመከላከልና ለመዋጋት የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት የአገሪቱ መንግሥት ብሔራዊ የአበረታች ንጥረ ነገሮች ቦርድና ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ ችግሩን ለማስወገድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቅንጅትና በጥምረት እየሠራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ድርጊቱን እንደሚያወግዝ በመግለጫው አካቷል፡፡

በአትሌቶች፣ በማናጀሮች፣ በአሠልጣኞችና በሌሎች አካላት የሚደረገው የመከላከልና የቁጥጥር ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲና ሌሎች ተቋማት ለሚያከናውኑት ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራ የበኩሉን ድጋፍና ትብብር ከማድረግ ባሻገር ጥፋተኛ ሆነው በሚገኙ ግለሰቦችና አትሌቶች አግባብ ባለው ሕግ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ አበክሮ እንደሚሠራ፣ በዚህ አጋጣሚ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ከዚህ መሰል ድርጊት ራሳቸውን ነፃ እንዲያደርጉና ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ሁሉም ወገኖች የድርጊቱ ተሳታፊዎችን እንዲከታተሉና የሚደርስባቸውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በመስጠት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርበት ጭምር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በአትሌቲክሱ ላይ ያጠላውን ይህን የአበረታች ንጥረ ነገሮች ጉዳይ ከኢትዮጵያ ለማራቅ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ መንግሥት የሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር መጠናከሩ ቢገለጽም፣ አሁንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከችግሩ ጋር በማገናኘት የሚወጡ መረጃዎች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ በዚህም በአገሪቱ ከሁሉም አቅጣጫዎች የሚደመጡ አስተያየቶችና ጥቆማዎች ከጥርጣሬ ይልቅ እምነትን የሚያረጋግጡ መምሰል ጀምረዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና የማናጀር ተወካዮች፣ የቀድሞና የአሁኑ አትሌቶች ለችግሩ መንስዔ የሚሉዋቸውን ያስቀድማሉ፡፡

አትሌቲክሱ በተለይም ከአቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሔራዊ ማንነት መገለጫ ከመሆኑ ባሻገር፣ ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህም በአገሪቱ በተለይም በአትሌቲክሱ ያለውን ሀብትና አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡና የገቡበትን ዓላማ ያለገደብ እንዲጠቀሙ አጋጣሚው እንደፈቀደላቸው ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በአሠልጣኝ ወይም በማናጀር ስም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የውጭ ዜጎችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህ በዋናነት ተጠያቂ የሚያደርጉት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን የሚከታተለውን ተቋም ነው፡፡

ከሰሞኑ በስፔን ባርሴሎና ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር በተያያዘ በዋዳና በስፔን የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ ትብብር በቁጥጥር ሥር የዋለው እንግሊዛዊው ጃማ ኤደን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ከማንም በተሻለ እንደሚያውቃቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ግለሰቡ ለምን ወደ ኢትዮጵያ መጣ የሚል አቋም እንደሌላቸው፣ ነገር ግን የሚመጣበት ምክንያትና የሥራ ድርሻው በሚገባ ተጣርቶና ተለይቶ ሊሆን እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ ይህንኑ አትሌቲክሱን በበላይነት የሚመራው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአትሌቲክሱና አትሌቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ ዜጎችን በሚመለከት ተቋሙን እንደማይመለከት፣ የውጭ ዜጎችን የመግባትና የመውጣት ጉዳይ በሚመለከት ኃላፊነቱ የሌላ መንግሥታዊ ተቋም መሆኑን በግልጽ ሲተች የተደመጠበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሕክምና ክፍል ውስጥ በመሥራት ለዓመታት የሚታወቁት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መርፌ የሚወጉ የውጭ አገር ዜጎች በየሠፈሩ እንደ አሸን የበዙበት ሁኔታ መኖሩን በመድረክ ላይ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትና የሚወጡበትን ሁኔታ አስመልክቶ ከሚስተዋለው ክፍተት ጎን ለጎን አትሌቶች ከጊዜውና ከወቅቱ ጋር መሄድ የሚችል የተሻለ ሥልጠናና የውድድር ዕድል በመሻት የችግሩ ተጠቂ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ የሚናገሩ አሉ፡፡

የተሻለ ሥልጠናና የውድድር ዕድል በሚለው ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡ ሙያተኞች ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ኢትዮጵያዊው የማናጀር ተወካይና አሠልጣኝ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ማናጀር ተወካዩ ገለጻ፣ በተለይ አሁን በኢትዮጵያ ባለው የአትሌቲክስ ሥልጠና ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ሥልጠናዎች በቀድሞ አሠልጣኞች ጊዜ የነበሩና ሥልጠናው ከጊዜው ጋር ሊሄድ የማይችል በመሆኑ ምክንያት በአትሌቶች እንደማይፈለግ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በአትሌክሱ የተሻለ አቅምና ዕውቅና ያላቸው አትሌቶች እነሱ በሚፈልጉት መጠን ውጤታማ ሊያደርጋቸው የሚችለውን አማራጭ እንዲፈልጉ ያስገድዳቸዋል፣ እየሆነ ያለውም ይኼው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በዋስ መለቀቁ የተነገረለት ጃማ ኤደን ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች አትሌቶች እንዲያሠለጥናቸው ይመርጡታል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የማጀር ተወካዩና አሠልጣኙ፣ ‹‹ይኼ ጥሬ እውነት ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመናገር እንደሞከርኩት የአገራችን የሥልጠና አሰጣጥ ዘዴ ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ የአገራችን አትሌቶች ደግሞ ከተፎካካሪዎቻቸው ተሽለው ለመገኘት የተሻለውን ሥልጠናና ከሥልጠናው በኋላ የተሻለ የውድድር ዕድል የሚፈጥርላቸውን ሰው ይመርጣሉ፤›› ብለው ጃማ ኤደንን በተመለከተም ግለሰቡ ቀድሞ አትሌት የነበረና አሠልጣኝ ከሆነ በኋላም በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪውን ማግኘት የቻለ ሙያተኛ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር በተገናኘ ግለሰቡ በጥርጣሬ በቁጥጥር ሥር ውሎ የፍርድ ሒደቱን ውጭ ሆኖ እንዲከታተል በዋስ መለቀቁ ይታወሳል፡፡ ከዚሁ በመነሳት የማናጀር ተወካዩና አሠልጣኙ፤ ‹‹ጥርጣሬው ጉዳዩ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ጭምር መጥፎ ነው፡፡ ምክንያቱም ከችግሩ ጋር ተያይዞ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስማቸው ሳይቀር እየተጠቀሰ መነገሩ ጉዳዩን ከጥርጣሬም በላይ እውነታነት እንዲኖረው እያደረገ ነው፤›› ብለው ጉዳዩ መፍትሔ የሚያገኝበት አማራጭ ከወዲሁ ሊፈለግለት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

የሰሞኑን ክስተት ተከትሎ ብዙዎች በጉዳዩ ዙሪያ ለሚጠየቁት አስተያየት ማንነታቸውንና ስማቸውን መግለጽ አይፈልጉም፡፡ ከሥልጠናና ከዚሁ ከሰሞኑ ክስተት ጋር ተያይዞ ሪፖርተር ካነጋገራቸው አንዱ የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኝም ስማቸው እንዲገለጽ አልፈለጉም፡፡

አትሌቶች ከአገር ውስጥ አሠልጣኞች ይልቅ እንደነ ጃማ ኤደን የመሳሰሉትን የውጭ አሠልጣኞችን ለምን ይመርጣሉ? ለሚለው አሠልጣኙ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ምክንያቱ እንዲህና እንዲያ ሊሆን ይችላል ወደሚለው ዝርዝር መግባት ባይፈልጉም በሙያው ውስጥ የሚገኙ ሙያተኞች እሳቸውን ጨምሮ ፍፁም የተሟሉና ምንም  ክፍተት ሊኖርባቸው አይችልም ብለው እንደማይከራከሩ ይናገራሉ፡፡ አሠልጣኙ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች ከአገር ውስጥ አሠልጣኝ ይልቅ የግልና የውጭ አሠልጣኞችን የሚመርጡበት ምክንያት ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ምክንያቱም አሠልጣኙን በእነሱ ፍላጎትና ቅኝት ብቻ እንዲሄድ ከመፈለግ ይመነጫል፤›› ይላሉ፡፡

ጃማ ኤደን በብዙ አትሌቶች የሚመረጡበት ምክንያት፣ ‹‹አንዱና ዋናው ነገር ጃማ ኤደን ከአሠልጣኘነቱ ጎን ለጎን በግንኙነት ረገድ ከአገራችን ሙያተኞች የተሻለ ነው፡፡ ዓለም ላይ ወሳኝ የሚባሉ ቋንቋዎችን ሳይቀር ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይኼ ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ የውድድር አዘጋጅ ድርጅቶችንና ኩባንያዎች እንዲሁም ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት ጭምር እንዲያውቃቸው የተመቻቸ ሆኖለታል፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ ዓለም ላይ ያሉ ጠንካራ አትሌቶች እሱን እንዲመርጡ ምክንያት ሆኖታል፤›› በማለት የጃማ ኤደንን የተፈላጊነት ሚስጢር አሠልጣኙ ያስረዳሉ፡፡ ከፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ አሠልጣኙ የፍርዱን ሒደት የሚከታተለው አካል ጉዳዩን ‹‹እንዲህ ነው›› በማለት በይፋ እስካላሳወቀ ድረስ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ ጭምር ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...