ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር
ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ናቸው፡፡ ዋና ኮሚሽነር ከመሆናቸው በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ኮሚሽኑን ከተረከቡ በኋላ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ግጭቶችን አስመልክቶ መሥሪያ ቤታቸው ያደረገውን ምርመራ ያጠናቀረውን ሪፖርት ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከነአምን አሸናፊ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት በአገሪቷ ውስጥ እንዲሰፍን ዋና ሚና እንዲጫወት የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ተቋሙ የሰብዓዊ መብት በአገሪቷ ውስጥ እንዲዳብርና ዜጎች የሰብዓዊ መብታቸውን ተረድተው እንዲተገብሩት ከማድረግ አንፃር ምን እየሠራ ነው? ተጨባጭ ሁኔታው ምን ይመስላል?
ዶ/ር አዲሱ፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋመና ተጠሪነቱም ለሕዝብ ለተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋም ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሰፈሩ ሩብ የሚሆኑት አንቀጾች የሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ እንደመሆናቸው መጠን እነዚህ መብቶችን እንዲያስከብር የተቋቋመ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንደኛው ትልቁ ሥራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ማከናወን ነበር፡፡ የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራ አንደኛው በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ላይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ስለሰፈሩ ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ኅብረተሰቡ ምን ዓይነት ግንዛቤ ነው ያሉት? በመብቱ ዙሪያ ደግሞ አውቆ ተዋናይ እንዲሆን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ አንዱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በሰብዓዊ መብቶች አያያዝና አጠባበቅ ላይ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመጠቀም ይህንኑ መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች፣ በሕፃናትና በሴቶች መብቶች ዙሪያ የተፈረሙ ስምምነቶችን ተቀብላ አፅድቃለች፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በአገራችን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡ ስለዚህ የአገራችን ሕግ አካል እንደመሆናቸው መጠን በተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉመን የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራ እንሠራለን፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉመናቸዋል እነዚህ ሰነዶች ለሚመለከታቸው ክልሎች፣ ለወጣቶችና ለሴቶች አሰራጭተናል፡፡ ስለዚህ አንደኛው ትልቁ ሥራችን የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው ትልቁ ሥራችን በአዋጁ መሠረት ክትትል እናደርጋለን፡፡ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ምን ዓይነት ጥሰት ሊደርስባቸው እንደሚችሉ በመገንዘብ በንቃት ክትትል እናደርጋለን፡፡ አንዱ ለምሳሌ የፖሊስ ጣቢያዎች አያያዝ ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች እንዴት ነው እስረኞችን የሚይዙት የሚለውን እንከታተላለን፡፡ ሕገ መንግሥታችን እያንዳንዱ እስረኛ ሲያዝ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ ሊያዝ ይገባል ይላል፡፡ ስለዚህ መብቱ መከበር አለመከበሩን ታራሚዎችን በማነጋገር በየማረሚያ ቤቱ እየሄድን ክትትል እናደርጋለን፡፡ የጎደሉት እንዲስተካከሉ ምክረ ሐሳብ እንሰጣለን፡፡ ከእነሱ አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ ለመንግሥትም ምክር እንሰጣለን፡፡ ሦስተኛው የምርመራ ሥራችን ነው፡፡ ምርመራ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ከተጣሱ በግጭትም ይሁን በአንዳንድ ግጭት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዴት እንደተያዙ ከሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ አኳያ ያሉትን መሬት ላይ ያሉትን እውነታዎችን የግድ መመርመር ስለሚያስፈልግ እንመረምራለን፡፡ ስለዚህ በዚህ የምርመራ ሥራ ዜጎች የደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ በአራተኛ ደረጃ ለሚመለከተው አካል ምክር እንሰጣለን፡፡ ምክሩ ምንድን ነው? መንግሥት እንዲያሻሽል የሚገባው ነገር ካለ ሊወሰዱ የሚገባቸው የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ካሉ መንግሥትን እናማክራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራታችሁን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ የሚደመጡ ምሬቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰብዓዊ መብት በአገሪቱ እንዲሰፍን በተጨባጭ ምን ለውጥ አምጥቷል?
ዶ/ር አዲሱ፡- ክሶችና አቤቱታዎች ይመጣሉ፡፡ የመጀመርያው ሥራችን አቤቱታዎች ሲመጡ በአዋጁ መሠረት እኛ ጋር የሚወድቅ መሆኑን መመልከት አለብን፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡ ፍርድ ቤት እያየው የሚገኘውን ጉዳይ ማንም ሰው ጣልቃ ገብቶ ማየት አይችልም፡፡ ስለዚህ የሚመጡልንን አቤቱታዎች በአዋጁ ሥር የሚወድቁ መሆናቸውን ማጣራት የመጀመርያው ሥራ ነው፡፡ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ምንድነው በግልጽ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሆነ ወደ እንባ ጠባቂ ተቋም እናመላክታለን፡፡ ምክንያቱም እኛ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ ያሉትን ነገሮች ነው የምናየው፡፡ የአስተዳደር ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ ወደሚመለከተው አካል እናመላክታለን፡፡ ጉዳዩ በእኛ ሥር የሚወድቅ ከሆነ ግን እንመረምረዋለን፡፡ መርምረን ምላሽ የሰጠናቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች መርምረን አንደኛ ከሚመለከተው አካል ጋር ጉዳዩ ስለሚፈታበት ሁኔታ ምክክር እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ እየተፈቱ ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሒደት ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመገምገም በየሦስት ወሩ ከሕዝብ ጋር የምንገናኝበት መድረክ አለ፡፡ በአብዛኛው ሕዝብን የማያገለግሉ አስተዳዳሪዎች እዚህም እዚያም ይገጥማሉ፡፡ ሕዝብን ማገልገል እንዳለባቸው ያለመረዳት ነው፡፡ የተቀመጡበትን ወንበርና ኃላፊነት መገልገያ አድርገው የሚቀመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ አብዝተን በተለያዩ ደረጃዎች ካሉ አስተዳደር ጋር መሥራት እንዳለብን ተረድተን እየሠራን ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አንዳንዴ ሄዶ ሄዶ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ሊደርስ ስለሚችል ከወዲሁ ለመከላከል ከአስተዳደሩ ጋር ሰብዓዊ መብት ከማክበር ረገድ የአስተዳደሩ ሚና ምንድነው? በሚለው እየሠራን ነው፡፡ ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር ነው የምንሠራው፡፡ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ጋር የምንሠራበት ዋነኛው ነገር ከጀርባ የያዛቸው ብዙ ማኅበራትም ዜጎችም ስላሉ ነው፡፡ እኛ በአንድ ጊዜ ሁሉንም መድረስ ላንችል እንችላለን፡፡ በእነሱ ግን የአሠልጣኞች ሥልጠና በመስጠትና በተለያዩ ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንዳለብን ግን እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ መሬት ላይ ያለው የእኛ አካሄድ እነዚህን ነው የሚመስሉት፡፡ የተፈቱ ችግሮች አሉ፤ በሒደት ላይ ያሉና እየተፈቱ ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ የእኛ የምርመራ ክፍል የያዛቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአሁን ወቅት ብዙ መርማሪዎቻችን የመስክ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነው ያሉት፡፡ ከመስተዳድሩ ጋር በየደረጃው ካሉ የአስተዳደር አካላት ጋር እየተነጋገሩ ችግሮች እየተፈቱ እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ነው መሥራት የምንችለው፡፡ ያን እያደረግን ነው ያለነው፡፡ እንግዲህ እስካሁን ጥሩ ውጤት አለ፡፡ ግን እዚህ ውጤት ላይ መተኛት አንፈልግም፡፡ የተሻለ ለመሥራት የተሻለ ነገር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብን ካላገለገልን ተልዕኳችንን ስተናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ደግሞ ያን ተልዕኮ እንዳንስት እየሠራን ነው፡፡ ዋናው መረሳት የሌለብን ቁም ነገር ሕዝብን አገልጋይ የሆነ አመራር ነው እንጂ መኖር ያለበት ተገልጋይ አይደለም፡፡ ስርፀት እስኪመጣ ድረስ በጣም በርካታ ሥራዎች መሥራት እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አንዱ ዓላማ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከልና መቆጣጠር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች ተከስተው ስለ ሁኔታው ሪፖርት ከማውጣት ይልቅ ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች ከመነሻው እንዳይፈጠሩ ከማድረግ አኳያ ምን እየሠራችሁ ነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- ይህ ነጥብ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዳችንን ስንቀርጽ በሥነ ሥርዓት ያየነው ነው፡፡ የመከላከል ሥራ አስቀድሞ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እሳት ከማጥፋት ይልቅ የመከላከል ሥራ መሥራት ተገቢ እንደሆነ ተገንዝበን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንደኛ መሥራት የምንችለው ግንዛቤን ማስረጽ ነው፡፡ ተገልጋይ ኅብረተሰብ አለ፤ አገልጋይ አካል አለ፡፡ በእነዚህ መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት መሀል ላይ ያለው የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ነው፡፡ ያንን አክብረው ሁለቱም አካላት መንቀሳቀስ እንዲችሉ በተለይ ደግሞ ሊያገለግል በተለያየ ደረጃ የተሰየመው አካል ግንዛቤ ከማስፋት አኳያ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለብን ስለገባን፣ በተገልጋይ በኩል ደግሞ መብቱ ምንድነው ግዴታውስ ምንድነው? የሚለውን በማስረጽ እየሠራን ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መብት ስናይ ግዴታም እንዳለ መታወቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ የሕገ መንግሥቱን መርሆዎችን ከማስረጽ አኳያ አሁንም ለወደፊቱም ሰፋፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራ በሚገባ ካልተሠራ የመከላከል ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ መከላከል የሚባለው ሊመጣ የሚችለው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ስንሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሊያገለግል የተሰየመው አካል በአጠቃላይ የማገለግለው ኅብረተሰብ ምንድነው? ለምንድነው የማገለግለው? ይህን በማድረጌ በኅብረተሰብ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ምንድነው ብሎ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ ግንዛቤ የሚባለው ነገር መሀል ላይ ያለ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ግንዛቤ ያለው ዕውቀት ያለው መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ግንዛቤና ዕውቀት ካለ የሚጠፋ ነገር አይኖርም፡፡ ግንዛቤ ያለመኖር ነው አንዱ ትልቁ ነገር፡፡ ወደ ግጭትም ሆነ ወደ ብጥብጥም የሚያስኬዱ መንገዶች ስናያቸው ሁሉም ይኼ ነው ብዬ ነው ላስብ የምችለው፡፡ ሁለተኛው ሰላማዊ የዜጎችን ጥያቄ በሆነውና ባልሆነው ሊነጠቅ አይችልም፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ሲኖር አንዱ አካል መብቱን ያውቃል፡፡ የሚጠይቀውን ጥያቄ ያውቃል ሌላኛው ደግሞ የሚያገለግለውን ኅብረተሰብ ያውቃል፡፡ መሀል ላይ ከሁለቱም ያልሆኑ ፀረ ሰላም የሆኑ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም የነበረውን የኅብረተሰብ ድርሻ ለመንጠቅ የሚሯሯጡ ኃይሎች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ እነሱ ቦታ እንዳይኖራቸው ከማድረግ አኳያ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የእኛ ድርሻ ምንድነው የመከላከል ሥራ መሥራት የሚቻለው በዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀትን ከማስፋፋት ግንዛቤን ከማስፋፋትና አኳያ እርሱ ነው በስትራቴጂክ ዕቅዳችን እየሠራን ያለነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልልም እየሠራን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በአገሪቱ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ያለውን ግምገማ የሚያሳይ ሪፖርት እያዘጋጀ እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅዱ ጋር ተናቦ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆንም ተገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን የወጣ ሪፖርት የለም፡፡ ሪፖርቱ ከምን ደርሷል?
ዶ/ር አዲሱ፡- እስከገባኝ ድረስ በመጨረሻ ሩብ ዓመቱ 2007 ላይ ለፓርላማው የቀረበ ሪፖርት አለ፡፡ እዛ ላይ ተጠቃለው ቀርበዋል፡፡ በማረሚያ ቤቶች አያያዝ ላይ፣ በፖሊስ ጣቢያ ያሉ ተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ እነዚህ በምክር ቤቱ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ተጠቃለው ቀርበዋል፡፡ ከዛ በኋላ ያሉ ሪፖርትና ጥናቶች አሉ፡፡ እነዚህ ጥናቶች ደግሞ የአርትኦት ሥራ ያስፈልጋቸው ስለነበር እርሱን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ በሴቶች ዙሪያ ላይ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የተካሄዱ ጥናቶች አሉ፡፡ በደቡብ ክልል በመንጃ ማኅበረሰብ ላይ የተሠራ ጥናት አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሞላ ጎደል ጥናቶቹ ተጠናቀዋል፡፡ ጥናቶቹ አልቀው ወደ ሕትመት እየገቡ ነው፡፡ እነርሱ ይፋ ሲሆኑ የምናውቀው ነገር ይሆናል፡፡ እነዚህ ተጠንተው መኖራቸውን ግን አውቃለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደረጃን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሚሰጣቸው ውጤቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ተቋማችሁ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ምንስ ላይ ለመድረስ ያቅዳል?
ዶ/ር አዲሱ፡- ከተመድ በፊት ሕዝቡ እንዲፈርደን ያስፈልጋል የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ሕዝባችንን ምን ያህል አርክተናል በሚል ነው፡፡ እኛ ራሳችንን በቅጡ መጠየቅ የሚገባን ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ላይ ነው ፍርድ ሊሰጡን የሚገባው፡፡ ደረጃም ካወጣን አያያዙንም አጠባበቁንም የሕገ መንግሥቱ መርሆዎችንም አፈጻጸም ያንን መሠረት አድርገን ሥራችንን እንሠራለን፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፣ በየሦስት ወሩ ያለንበትን ደረጃ እንዲነግሩን የሚዘጋጅ መድረክ አለ፡፡ ይህንን ጥሩ አድርጋችሁታል፣ ይኼ ይቀራችኋል እያለ ኅብረተሰቡ እንዲገመግመን እንፈልጋለን፡፡ ለዛ ደግሞ መድረክ የማዘጋጀታችን አንደኛው ትልቁ ነጥብም ይኼ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ ላይ የደረጃ አወጣጥ ላይ የራሱ ብዙ አካሄዶች ያሉት ነው፡፡ በባለፈው ጄኔቭ ላይ በነበረው ስብሰባችን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ዘርፍ የሚከታተሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደገለጹልን ከሆነ ሪፖርቶችን በየጊዜው የማሳወቅ ነገር ከእኛ ይጠብቃሉ፡፡ በተረፈ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በዚህ ዘርፍ ላይ ያለን ግንኙነት በጣም መልካም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አብዛኛው የኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያተኩረው ከመሬት፣ ከምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የወጡት የሚዲያ፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ ሕግና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጆች ዋነኛዎ ቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሚያ መሳሪያ ሆነዋል የሚል ትችት ይደመጣል፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ እነዚህ ሕጎች ከሰብዓዊ መብት ደረጃዎች አኳያ በማየት እንዲሻሻሉ ወይም ከማጥናት አንፃር ምን እየሠራ ነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለተቋቋመለት ዓላማ መሥራት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ሕጎችን ከሰብዓዊ መብት አኳያ ሊኖራቸው የሚችል አንድምታ ምን እንደሆነ ቀድሞ ለእኛ ረቂቅ ይላክልናል፡፡ በተለይ አዋጆች ሲወጡ ከሰብዓዊ መብት አከባበር አኳያ ሊተላለፉ የሚችሉ አንቀጾች እንዳይኖሩ ግልፅነት ከመፍጠር አኳያ እኛም የራሳችን ድርሻ ይኖረናል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ የወጡትን የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉንና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጆች ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተያያዥነት አላቸው ብለው የሚፈርጁትን አካላት እንግዲህ መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንመልከት፡፡ ይህን ሕግ ኢትዮጵያ ብቻ ነች ወይ ያፀደቀችው? ሰብዓዊ መብት እናከብራለን የሚሉና በአንደኛ ደረጃ ሰብዓዊ መብት አክባሪ የሚባሉ አገሮች ይህ ሕግ አላቸው፡፡ ግን ይህንን ሕግ መሬት ላይ አውርዶ ሰብዓዊ መብት ጥሷል ወይስ አልጣሰም? ነው ጥያቄ መሆን ያለበት እንጂ ሕጉ መውጣቱ ተነጥሎ መታየት የለበትም፡፡ በሽብር ተግባር ላይ ሳይሰማራ በሽብር ሕጉ የተከሰሰ አካል ካለ እርሱን ነው ማየት ያለብን፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ የመጣልን ማመልከቻም ቅሬታም የለም፡፡ እርግጥ ከዓለም አቀፍ ማኅበራት አንዳንዶቹ በደፈናውና በደምሳሳው በዚህ አዋጅ የተወሰኑ ሰዎች ተከሰው፣ የተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት መከሰሳቸውን በዚህ አዋጅ መግባታቸውን ይቃወማሉ፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት የወሰነውን ጉዳይ ከሽብር ጋር ተያያዥነት የሌለው ሥራ ነው የሠሩት ብለው ይከራከራሉ፡፡ ፍርድ ቤት ደግሞ ከሽብር ተግባር ጋር ከነማስረጃው ያቀረበው ጉዳይ አለ፡፡ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ተጥሎ የክስ ለዚያውም ማስረጃ የሌለው እውነታ የሌለው ነገር ገዝፎ መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ገዝፎ መታየት ያለበት ጉዳይ እያንዳንዱ ዜጋ በሕግ ፊት እኩል ነው፤ ጉዳዩም ሲቀርብ ከሕጉ አኳያ የተጣሰ መብት ካለ እርሱን ማየት ይቻላል፡፡ የተጣሰ መብት ከሌለ ግን አዋጁ እንደ አዋጅ መቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን አዋጅ መቃወም ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሉዓላዊ አገር ናት፡፡ የትኛውን ሕግ እንደምታወጣ የትኛውን ሕግ እንደምትተገብር ኢትዮጵያ ታውቃለች፡፡ እየቀረበ ያለው ግን ይህን ሕግ ማውጣት የለባችሁም፡፡ ይህን ሕግ አውጡት፡፡ ይህንን ሕግ ቀይሩት፡፡ ይህንን ሕግ በዚህ ተኩት የሚባል ነገር ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባውም፡፡ መሠረቱ ትክክል ስላልሆነ፡፡ ወደ ተቋማችን ስንመጣ ከመብት አኳያ በየጊዜው ክትትል እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ለመቀልበስ አይደለም የምንሄደው፡፡ በተረፈ ግን ከሚወጡት ሕጎች ጋር ያለው ተቃርኖ ከሕግ መርሆዎ ጋር የተገናኘ ሳይሆን በአብዛኛው ከተቃዋሚዎቹ የራሳቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ጋር የተያያዘ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕግን መውጣት ተከትሎ አብዛኞቹ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዘግተዋል፡፡ አንዱ የእናንተ ሥራ ደግሞ ቀደም ሲል እንደገለጹት ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማትም ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃር ሲሠሩ የነበሩት ሥራ ነበርና ይህ የሰብዓዊ መብት ሁኔታውን አይጎዳውም?
ዶ/ር አዲሱ፡- ቅድም እንዳልኩት ከብዙ የማኅበረሰብ አካላት ጋር እንሠራለን፡፡ ከሴቶች ማኅበራት፣ ከወጣቶች፣ ከሕፃናት ጋር እንሠራለን፡፡ ከእነዚህ ማኅበራት ጋር የምንሠራው ዋናው ነገር የግንዛቤ ማስፋፋቱ ሥራ ተደራሽነቱ እንዲረጋገጥና ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ስናየው እኛ የተጎዳብን ነገር የለም፡፡ ማኅበራቱ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በየሦስት ወሩ ደግሞ ከሕዝብ ክንፍ ጋር እንገናኛለን፡፡ በዛ ውስጥ የምናያቸው ብዙ ማኅበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ የማኅበረሰብ አካላት ጋር እየሠራን ስለሆነ እኛ ያጣነው የቀነሰብን ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ጥያቄው ግን እናንተን ይጎዳችኋል ወይም ያጣችሁት ነገር አለ ለማለት ሳይሆን የተቋማቱ መዘጋት አጠቃላይ የሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ የሚሠሩ ሥራዎችን አይጎዳም ወይ ነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- የሲቪክ ማኅበራት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝብን ወክለው ያወጡት ሕግ ግን መከበር አለበት፡፡ ከሕጉ ጀርባ ደግሞ አሳማኝ የሆኑ ነጥቦችም አሉ፡፡ እነዚህን እኛም እንደ ተቋም አክብረን ነው መገኘት ያለብን፡፡ ተደራሽ ከመሆን አኳያ መንግሥት የራሱ የሆነ አንድ ኃላፊነት አለበት፡፡ ምክር ቤቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የፍትሕ አካላትም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነቱ የመንግሥትና የተለያዩ አካላት ነው፡፡ እነዚህ የድርሻቸውን ከተወጡ ብዙ ችግር ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ለፓርላማ አቅርበውት ወደነበረው ሪፖርት ልመልስዎትና፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት አስመልክቶ የተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ ሰብዓዊ መብት ጉባዔም (ሰመጉ) ያወጣው ሪፖርት ነበር፡፡ ከዚህ እንነሳና በእናንተና በጉባዔው ሪፖርት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የሰመጉ ተጠሪነት ለማን እንደሆነ በግልጽ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ሪፖርታችንን በተመለከተ ምርመራ አካሂደናል፡፡ ከምርመራ አኳያ የተከተልናቸው ዘዴዎች አሉ፡፡ አንድ መርማሪ ሊኖረው የሚገባ የምርመራ ስልት ግልጽና ገለልተኛ በሆነ መልኩ መሥራት እንዳለበት ያስቀመጥነውና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ ያደረግነው ስልት አለ፡፡ ስለዚህ የእነርሱን ሪፖርት የራሳቸው ስለሆነ እነርሱ ራሳቸው ነው አስተያየት ሊሰጡት የሚገባው፡፡ ጊዜ የፈጀ አድካሚ የሆነ ግልጽ የሆነ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ አድርገናል፡፡ ስለዚህ የሪፖርታችን መነሻና መድረሻ ሕገ መንግሥቱን ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ለማጣራት ባደረጋችሁት ጥረት የምርመራ ሒደቱ ምን ይመስል ነበር? የተጠቀማችሁት ቴክኒክ ምን ነበር? የሚገኙ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በምንድነው ስታጣሩ የነበረው?
ዶ/ር አዲሱ፡- መጀመሪያ መርማሪ ቡድን እናሰማራለን፡፡ ከመርማሪ ቡድን መሰማራት በፊት ግን ሊከተሉት የሚገባ ሥነ ምግባር፣ ሊከተሉት የሚገባ የምርመራ ዘዴ፣ ሊያከብሩት የሚገባ ሕግ፣ በአጠቃላይ መጠይቆችና የት የት ቦታ ግጭቶች እንደተፈጠሩ ይህን ሁሉ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ አስቀድሞ ለሚላኩ መርማሪ ቡድኖች ግንዛቤ እንዲኖራቸው በብጥብጡና በግጭቱ የደረሰው ጉዳትና ማስረጃ ያለው ምርመራ ከማድረግም አኳያ ጥልቅ የሆነ ሳይንሳዊ የሆነ ዝግጅትም ተደርጎ ነው ወደ ኦሮሚያም ሆነ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ጎንደርም የተሰማራው፡፡ ስለዚህ ምርመራው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ነው፡፡ በብጥብጡና ሁከቱ ውስጥ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብለው የሚታወቁ አካላት አሉ፡፡ መንግሥት አንዱ ነው፣ ተጎጂ ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰብ እንደማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የፀጥታ ኃይላት፡፡ እነዚህ ሁሉ በብጥብጡና በሁከቱ ድርሻ የነበራቸው ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳ ያሉ ቀበሌዎች ስንት ናቸው፡፡ ምን ያህሉ ቀበሌ ውስጥ ግጭት ነበር፡፡ ምን ያህል ንብረት ወደመ? የማን ንብረት ነው የወደመው? ግድያው እንዴት ተፈጸመ ማን ፈጸመው? የሚለው ዝርዝር የተቀናጀ አካሄድ ነው የሄድንበት፡፡ አንድ መረጃ የሰጠህ አካል አለ፡፡ እሱን መረጃ ደግሞ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የምትሄድበት ተጨማሪ መንገዶችን ለመሄድ እስከ ሕክምና ማስረጃ ጭምር መርምረናል፡፡ በዚህም መሠረት በእያንዳንዱ ወረዳ ምን ያህል ሰው ሞተ፣ ምን ያህል ንብረት ወደመ ማን ነው ይህን ያደረሰው የሚለውን ዝርዝር ነገሮች ስንሠራ ነው ይህን ያህል ጊዜ የፈጀው፡፡ ምክንያቱም እውነትን ማጣራት ቀላል አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ጭብጥ ላይ ኮሚሽኑ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ሆኗል ሲል ማስረጃ አለህ ወይ ነው? ከዛ አኳያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው የምርመራ ሪፖርት በመጀመሪያ ኅብረተሰቡ በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን መብት ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ችግሩን ከመለየትም አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለበትን አካል ደግሞ በሚገባ ለይቶ በምክር ቤቱ ከማቅረብ አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ለወደፊቱም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጠር ከማድረግም አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለፓርላማው ሪፖርትዎን በሚያቀርቡበት ወቅት በኦሮሚያ የተፈጠረው አለመረጋጋት በኦነግ መጠለፉን ገልጸዋል፡፡ ይህን በምን ዓይነት ማስረጃ ነው ሊያረጋግጡ የሚችሉት? ኦነግ የተፈጠረውን አለመረጋጋት መጥለፉን አስመልክቶ ያላችሁ ተጨባጭ ማስረጃ ምንድነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- የዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ዜጎች ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግና ፀረ ሰላም ኃይሎች የሕዝቡን ሰላማዊ ሠልፍ ነጥቀው ነው ወደ ብጥብጥና ወደ ሁከት እንዲያመራ የተደረገው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃው ሕዝቡ የጠየቀው ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝቡ የጠየቀው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አለኝ ብሎ ነው፡፡ የግልጽነትን ጥያቄ ነው የጠየቀው፡፡ ለምሳሌ የግልጽነትን ጥያቄ በተመለከተ ከኦሮሚያና የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ጋር ተያይዞ ግልጽ ሊሆንልኝ ይገባል ብሎ የጠየቀው ጥያቄ አለ፡፡ ይህ ጥያቄ ሊከበር ይገባል የሚል እምነት እንደ ተቋም አለን፡፡ አንደኛው የዜጎች የመብት ጥያቄ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መብታቸው ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ መልስ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ይህ አልተደረገም ነው ኮሚሽኑ እያለ ያለው፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በጊዜ ተቀብሎ በጊዜ መፍትሔ አልሰጠም፡፡ ይህንን ጥያቄ ግን ተገን በማድረግ የሕዝቡን ጥያቄ ወስደው ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያመራ ያደረጉት ግን ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው፡፡ የኦነግ አርማ የተሰቀለባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ በአገር ሽማግሌዎች ጥረትና በሕዝቡ ጥያቄ እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ የኦነግ አርማ ይዘው በየመንገድ ሲሄዱ የነበሩ ማሳያዎች ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማስረጃዎቹ አሉ፡፡ መርማሪዎቻችንም ሒደው ያገኙት ይህንን ነው፡፡ ይበተን የነበረ ወረቀት አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች መሬት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ የእኛ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው የነበረው፣ ነገር ግን ጥያቄያችን ነጥቀው በግድ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንድንገባ አደረጉን በማለት ነው ሕዝቡ የነገረን፡፡ አንገባም ስንል ቤታችንንና የእህል ክምሮቻችንን ተቃጠሉብን፤ ይህንን ኅብረተሰቡ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያ ላይ የመልካም አስተዳደር እጦት ነበር፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ አልተመለሰም ነበር፡፡ ይህንን በጊዜ አልተስተናገደም፡፡ ባለመስተናገዱም ኅብረተሰቡ ጥያቄ ጠይቋል፡፡ ጥያቄው ግን ተነጥቋል፡፡ መጨረሻው ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ወደ ሕይወት መጥፋትና የሚያሳዝን ጉዳይ ደርሷል፡፡ እጅግ አሳዛኝ በአገራችን ልናየው የማንፈልገው ነገር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሪፖርቱ ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር አካባቢ ለደረሰው ጉዳት የልዩ ፖሊስ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሟል፤ ለዚህም ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድበት አሳስበዋል፡፡ ነገር ግን በግልጽ የክልሉ አስተዳደር ለደረሰው ጉዳት ምንም ዓይነት ኃላፊነት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡ የክልሉ አስተዳደር የሚያዘው ልዩ ፖሊስ ተጠያቂ ይሁን እያሉ አስተዳደሩ ነፃ ነው ማለት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- ተጠያቂ መሆን ያለበት እዛ የተሰማራው ልዩ ፖሊስ ነው ብለን አስምረናል፡፡ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሟል የተባለው በጎንደር ዙሪያ ማውራና አይከል ላይ የተሰማራው ልዩ ፖሊስ ነው፡፡ መሬት ላይ ያሉ ማስረጃዎችን ያንን ስለሚሉ ነው፡፡ ይህንን ከክልሉ አስተዳደር ጋር ተያያዥነት እንዳለውና እንደሌለው ስንመረምር ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ብናገኝ ወደኋላ የምንለው ነገር የለም፡፡ ግን ማስረጃ ከሌለ በእያንዳንዷ ምክረ ሐሳብና ጭብጥ ላይ ክስ አይደለም የምታቀርበው፡፡ ስለዚህ የፖሊሱን ኃይል ሚና አይተናል፡፡ ለምሳሌ ማውራ ከተማ ላይ የፖሊስ ኃይሉ በአገር ሽማግሌዎች ለሦስት ቀናት ሲለመን የነበረ እንደሆነና አለመመለሱን አይተናል፡፡ ይህ ማስረጃ ነው፡፡ ይህንን የመንግሥት ወይም የካቢኔ እጅ እንዳለበት ስንመረምር እጁ እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘንም፡፡ ከዚህ አኳያ ማስረጃ ከሌለ የምንለው ነገር አይኖርም፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን ኢ ምክንያታዊ ምላሽ አይመስልዎትም? ምክንያቱም የክልሉ መስተዳድር የክልሉን የፀጥታ ጉዳይ በተመለከተ እያንዳንዱን ሥራ እንደሚያከናውን ይታወቃል፡፡ በስፍራው የነበረው ፖሊስ በራሱ ዕርምጃ ወስዷል ብላችሁ በማመናችሁ ወይም ምንም ዓይነት ሁለቱን የሚያናኝ ማስረጃ ባለማግኘታችሁ ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ እንዴት ይቻላል?
ዶ/ር አዲሱ፡- ኢ ምክንያታዊ የሚሆነው ማስረጃ ሳናገኝ የምንከሰው አካል ሲኖር ነው፡፡ ያጣራነው ጉዳይ ላይ እነዚህን ማስረጃዎች ደምረን ደማምረን ይህንን ጭብጥ አግኝተናል፡፡ ይህ ጭብጥ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ከዋና አካሉ ጋር ሊገናኝ ይገባል፡፡ ለየብቻ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ይህንን በምናጣራበት ሁኔታ ላይ የክልሉን መንግሥት ሚና እጁ እንዳለበት የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘንም ማለት አላገኘንም ማለት ነው፡፡ ካልተገኘ አልተገኘም፡፡ ልዩ ፖሊስ ኃይል በተሰማራበት በማውራና በአይከል ግን የተጠቀመው ኃይል ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው መደምደሚያ ላይ የደረስነው ማስረጃ ስለተገኘበት ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት እጁ እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ ቢገኝ የክልሉ መንግሥት እጁ አለበትና ተጠያቂ መሆን አለበት ለማለት ወደኋላ አንልም፡፡ ምርመራ በመሠረቱ በስሜት የሚሠራ ነገር አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ማውራና አይከል ላይ የነበረውን ችግር ሲያባብስ የነበረው የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ነው ወደሚል መደምደሚያ ልንደርስ እንችላለን?
ዶ/ር አዲሱ፡- የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይልን ተጠያቂ አላደረግንም፡፡ ነገር ግን በቦታው የተሰማራው ልዩ ፖሊስ ኃይል ማውራና አይከል ላይ የተሰማራው ልዩ ፖሊስ ኃይል ነው፡፡ ለምንድነው ያገኘነው ማስረጃ እነዛ ቦታዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ልዩ ፖሊስ በሕዝብ ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀማቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሪፖርቱ ለፓርላማ ከመቅረቡ በፊት የሚመለከታቸው የክልል ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበት ተደርጎ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለፓርላማው ሆኖ ሳለ ለፓርላማው ሪፖርቱ ሳይቀርብ ለሌሎች አካላት እንዲቀርብ መደረጉ የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ አይከተውም?
ዶ/ር አዲሱ፡- ለሚመለከተው አካል መሠረታዊ ግኝቶች ላይ ግብረ መልስ መስጠት አይደለም አንድን ተቋም ገለልተኛ ነው አይደለም ብሎ ሊያስብል የሚያስችለው፡፡ ግብረ መልስ ምንድነው የሰበሰብነው አጠቃላይ መረጃ አለ፡፡ መርማሪዎች ሲሰማሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሰበሰቡት መረጃ አለ፡፡ ይህንን መረጃ አግኝተናል ብሎ ግብረ መልስ በመስጠት የሚቀየር ነገር አይኖርም፡፡ ግብረ መልሱ ማለት ምንድነው በክልሉ ገብተን ያገኘናቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ግብረ መልስ መስጠት ማለት ነው፡፡ ይህንኑ ግኝታችንን እንዲያውቁት የማድረግ ሥራ ክፋት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ግብረ መልስ ሳይንሳዊ ነው፡፡ አሠራሩም ይፈቅዳል፡፡ የአንድ ተቋም ገለልተኝነት የሚለካው ግን በተግባር ነው፡፡ መሬት ላይ ወርደን ገለልተኛ ሳንሆን የሠራነው ሥራ እንዳለ እርሱ ሊነገረን ይገባል፡፡ ገለልተኛ በመሆናችን አጥርተን ምን ያህል ሰው እንደሞተ፣ ምን ያህል ንብረት እንደወደመ፣ የት የት እንደሆነና ማንስ ተጠያቂ እንደሆነ ግልጽ በሆነ ጉዳይ ላይ ጽፈን ለምክር ቤቱ አቅርበናል፡፡