ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር ባለመክፈል ከተጠረጠረው ሪል የማዕድን እሽግ ውኃ አምራች ድርጅት ጋር በተገናኘ ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ታስረው ያደሩት፣ የአክሰስ ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የቦርድ አባል አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ ተለቀቁ፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መርማሪ ፖሊስ፣ አቶ ኤርሚያስን ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ስለ ሪል የታሸገ የማዕድን ውኃ አምራች ድርጅት ቅድመ ታሪክና አጠቃላይ አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ቃላቸውን እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ፣ ማረፊያ ቤት ቆይተው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተነግሯቸው ማቆያ ጣቢያ ማደራቸው ታውቋል፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎትም ቀርበዋል፡፡
የባለሥልጣኑ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ሪል የታሸገ የማዕድን ውኃ አምራች ድርጅት መክፈል የነበረበትን ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር አልከፈለም፡፡ ከአሥር በላይ ተሽከርካሪዎችም የት እንዳደረሳቸው እንደማይታወቅና ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ካሽ ሪጅስተር ማሽኖች መጥፋታቸውንም አስረድቷል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ድርጅቱን ከሸጡ ከዓመት በላይ እንደሆናቸውና ገቢዎችና ጉምሩክም ምርመራ አድርጐ መጨረሱን አስረድተዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ሪል የታሸገ የማዕድን ውኃ አምራች ድርጅትን መጀመሪያ የገዙት ከአቶ ታደለ ጋልቻ መሆኑን፣ ቀጥሎም አብዲና ቤተሰቡ የሚባል ድርጅት 80 በመቶ፣ አክሰስ ካፒታል 12 በመቶና አቶ ታደለ ስምንት በመቶ በሆነ ድርሻ እንደገዙት ገልጸዋል፡፡ 80 በመቶ ድርሻ ያለው አብዲና ቤተሰቡ ከአገር በመውጣቱ ባለሥልጣኑ በድርጅቱ ላይ ቁጥጥር እያደረገ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹና መርማሪ ፖሊስ ረዘም ያለ ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና እንደማያስከለክል የተረዳው ፍርድ ቤቱ፣ አቶ ኤርሚያስና አቶ ታደለ እያንዳንዳቸው በአሥር ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ በመስጠቱ፣ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡