Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የገጠማቸውን ችግር ለፓርላማ ይፋ አደረጉ

የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የገጠማቸውን ችግር ለፓርላማ ይፋ አደረጉ

ቀን:

  • የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዝናብና በውኃ ችግር ተመቷል
  • አይካ አዲስ ኪሳራ አንጃቦበታል

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እንዲሁም በቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በየዘርፋቸው የገጠማቸውን ከፍተኛ ችግር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አደረጉ፡፡

ኮሚቴው ከኩባንያዎቹ የሰበሰበውን ቅሬታና መልካም አጋጣሚዎች በማጠናከር ሰኔ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፋብሪካዎቹ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡

በቦሌ ለሚ አንድ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች በሙሉ እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የቱርኩ አይካ አዲስ፣ ኤምኤንኤስ፣ ካሮያ አፍሪካ፣ ከቆዳ ዘርፍ ደግሞ ጆርጅ ሹ፣ ኃጂዬን የተባሉት ጫማ ፋብሪካዎችና የኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካ፣ ሼባ ቆዳ፣ አዩ ከለር ፋብሪካ ናቸው፡፡ በመሆኑም 11 ድርጅቶችና አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቅሬታ ተሰብስቧል፡፡

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኙ ሼዶች ላይ በኮንስትራክሽን ሒደት የተጓደሉ ነገሮች በመኖራቸውና ባለመጠናቀቃቸው ምርት ተቀባይ ደንበኞች ትዕዛዝ ለመስጠትና እምነት ለመፍጠር የሚያስችሉ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በሁሉም ሼዶች የእሳት አደጋ መስመር የውኃ አቅርቦት አለመኖር፣ የእሳት አደጋ መስመሮች የሚያፈሱ መሆናቸው፣ የሽንት ቤት መስመሮች መዘጋትና የውኃ አለመኖር፣ የመብራት ችግር፣ መጥፎ የሥራ አካባቢን እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡

ለምሳሌ ሸንቲስ የተባለው የቻይና ኩባንያ በቦሌ ለሚ በያዘው ሼድ ውስጥ የውኃ መስመሩ ፈንድቶ ሲፈስ የቆየ በመሆኑ፣ ያልተጠቀሙበትን 992 ሺሕ ብር እንዲከፍል መጠየቁ በተጠናቀረው ሪፖርት ተገልጿል፡፡

መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማለትም የጉምሩክ፣ የባንክ፣ የጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የቆዳ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመሳሰሉት ተቀናጅተው እንዲያገለግሉ ቢያቅድም፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግን የሚገኘው ጉምሩክ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህም በሚገባ የሰው ኃይል ባለመደራጀቱ የተነሳ ኩባንያዎች አገልግሎት ፍለጋ ወደ ቃሊቲ ጉምሩክ ለመሄድ እየተገደዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውጭ ያሉ ኩባንያዎች መካከል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሰበታ አካባቢ የሚገኘው አይካ አዲስ እየደረሰበት ያለው ጉዳት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ችግር ያሳያል፡፡

አይካ አዲስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑት ልብስ አምራቾች የጀርመኑ ቼቦ እና ኤች ኤንድ ኤም ለመሳሰሉት የሚቀርብና ለአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ሞዴል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡

አይካ አዲስ ያቀረበው ቅሬታ በአገር ውስጥ የሚመረተው ጥጥ ጥራቱ የጎደለ፣ መገለጫዎቹም ጥጡ በሚሰበሰብበት ወቅት ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ በመሆኑ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀሉበት እንደሆነ፣ በእርጥበት የተበላሸ በአጠቃላይ የሚቀርብለት ጥጥ ከዋጋ አንፃር ሲታይም ውድ በመሆኑ፣ በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ዶላር እያጣ መሆኑን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሊኪውድ ፔትሮሊየም ጋዝ (LPG) በእጅጉ ውድ በመሆኑ ለአብነትም ከተወዳዳሪ አገሮች ማለትም የባንግልዴሽና የቱርክ ብቻ ተወስዶ የኢትዮጵያ ዋጋ በሦስት ዕጥፍ የሚንር በመሆኑ፣ በየዓመቱ ባልተመጣጠነ ዋጋ ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚያጣ ገልጿል፡፡

የድንጋይ ከሰል በመጠንም ሆነ በጥራት የማይገኝ በመሆኑ ኩባንያውን በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር እያሳጣው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብር ምንዛሪ መጠን አነስተኛ መሆንም ገበያውን እየጎዳው መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ በሎጂስቲክስ ዘርፍ አይካ አዲስ ያነሳው ከፍተኛ የዋጋ ንረትም በሌሎች ፋብሪካዎች በድጋሚ ተነስቷል፡፡

ኤምኤንኤስ የተባለው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያቀረበው ቅሬታ እንደሚያመለክተው ከፍተኛ የሠራተኞች ክህሎት አለመኖር ኩባንያውን 53 በመቶ ለሚደርስ የምርት ብክነት እየዳረገው መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከሎጂስቲክስ ረገድ አንድ ኮንቴይነር ዕቃዎችን ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት 1,110 ዶላር የሚከፍል መሆኑን፣ ምርቶቹን ኤክስፖርት ለማድረግ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ወደብ በኮንቴይነር 650 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ገልጾ ዋጋው ከመርከብ የትራንስፖርት ዋጋ በላይ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

ካኖሪያ የተባለው ኩባንያ የጥጥ አቅርቦት ከጥራት ጉድለቱ ውጪ አሥር በመቶ ከዓለም ገበያው የናረ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልጿል፡፡

ሁሉም ኩባንያዎች በዋናነት ያነሱት ትልቅ ችግር የሠራተኞች ዲስፕሊንና በጣም አስቸጋሪ የሥራ ባህልን ነው፡፡

ሠራተኞች የመፀዳጃ ቦታዎች አጠቃቀም ሥርዓት የጎደለው በመሆኑ መፀዳጃዎች መዘጋታቸው፣ ሠራተኞች ከሥራ ይልቅ እረፍት ማብዛት በከፍተኛ ችግርነት ተጠቅሷል፡፡

ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው አኳያ የሥራ ባህሉ ዝቅተኛ መሆኑን፣ የበዓላት ቀን በጣም የሚበዙ መሆናቸው፣ በሥራ ቀን ቢሆንም ባልታወቁ ምክንያት ከሥራ መቅረት ተጠቅሰዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት መልስ እንዲሰጡ መድረኩን የከፈቱ ሲሆን፣ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማናጀር የሆኑት አቶ መንግሥቱ ረጋሳ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተነሱትን ችግሮች አምነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪ ፓርኩን የገነቡ ኮንትራክተሮች ስህተቶችን እንዲያርሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስትቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ያሬድ መስፍን በበኩላቸው፣ አይካ አዲስ ላይ ያለው ችግር የገበያ መሆኑን ይኼንን ችግር ከአውሮፓ ገበያ በመውጣት ካልፈታ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የአይካ አዲስ የፕሮዳክሽን ማናጀር በበኩላቸው የገበያ ችግር እንደሌለባቸው ችግሩ በኢትዮጵያ ያለው የምርት ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለትና የሎጂስትቲክስ ዋጋ ምርታቸውን በማናሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ በበኩላቸው ‹‹ከችግሮቹ ጋር ተለማምደን እየኖርን ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከወሬ ባለፈ ወደ ዕርምጃ መግባት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የሠራተኛ ዲስፕሊንን በተመለከተ የሠራተኛ ሕጉ ኢንዱስትሪውን በሚጠቅም መልክ እየተሻሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...