Saturday, June 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢኮኖሚው ጣጣ ሌላ ቀውስ እንዳያመጣ!

ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ ያጋጠማት የፖለቲካ ቀውስ በዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ በበርካቶች ላይም የሥነ ልቦና ችግር  አስከትሏል፡፡ የፖለቲካ ቀውሱ የፈጠራቸው ተጓዳኝ ችግሮች በኢኮኖሚው ላይ በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡ በበርካታ ሥፍራዎች መረጋጋት በመጥፋቱ በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮች መቀዛቀዝ ታይቷል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍም የችግሩ ግዝፈት በሚገባ ተስተውሏል፡፡ ቱሪስቶች ሰላምና መረጋጋት የሌለባቸው ሥራዎች መሄድ ስለማይፈልጉ፣ በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ችግር ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ በቅርቡ የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ መዳከሙ በዜጎች ላይ ካስከተለው የዋጋ ግሽበት በተጨማሪ፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ትርምስ ፈጥሯል፡፡ ምርት መደበቅ፣ ከመጠን በላይ ዋጋ መጨመርና ገበያው ውስጥ የተጋነኑ ግምቶች መፈጠር ራሱን የቻለ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱና የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሽመደምዱ ችግሮችን በቅጡ አውቆ ለመፍትሔ መነሳት የወቅቱ አንዱ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ጣጣው የበለጠ ቀውስ ይፈጥራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገሪቷን እጅና እግሯን ጠፍሮ የያዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብዙዎችን እንደ መርግ ከብዶአቸዋል፡፡ በአብዛኛው ከግብርና ምርቶች፣ እንዲሁም በአነስተኛ ደረጃ ከማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ወጪ ንግድ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚገኘው ገቢም እንደ በፊቱ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ገቢ ንግድ ከመጠን በላይ በመሆኑ የንግድ ሚዛኑ የተዛባ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማንቀሳቀስ ባለሀብቶችን መጎትጎት ብቻ ሳይሆን መሬት፣ ብድርና ተዛማጅ ማበረታቻዎችን በአግባቡ ማቅረብ አለመቻል ትልቁ የዘርፉ ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩል የብርን የምንዛሪ አቅም በመቀነስ የኤክስፖርት ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር ውሳኔ ላይ ሲደረስ፣ ይህ ውሳኔ ብቻውን ምንም ውጤት እንደማያመጣ ማሰብ ያስፈልግ ነበር፡፡ ኢንቨስተሮችን የሚያበረታቱና ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ጫናዎች እንዳይፈጠሩ የሚረዱ የፖሊሲ ውሳኔዎች መዘንጋት አልነበረባቸውም፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ኢኮኖሚው በጠራራ ፀሐይ ፍሪጅ ውስጥ ያለ ይመስል እየተኮማተረ ነው፡፡ ሌላ ዙር የብር ምንዛሪ አቅም ቅነሳ ዕርምጃ ይወሰዳል የሚል ያልተረጋገጠ መረጃ ውስጥ ለውስጥ እየተሠራጨ የበለጠ መኮማተር እየፈጠረ ነው፡፡ የሚመለከተው አካል ወጣ ብሎ ማረጋጋት ሲገባው፣ በዝምታው ምክንያት ከተሽከርካሪ ግብይት እስከ ዕለታዊ ፍጆታ ምርቶች ድረስ የተጋነኑ ዋጋዎች ይጠራሉ፡፡ የተጋነኑ የዋጋ ግምቶች እየተሰጡ ምርቶች ይደበቃሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢኮኖሚው እንደ በረዶ እየቀለጠ እንዳይሄድ ያሠጋል፡፡

መንግሥት ለዓመታት ሲኩራራበት የነበረው ባለ ሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት እየተንሸራተተ ወደ አንድ አኃዝ ሲሸጋገር፣ በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበት ከአንድ ወደ ሁለት አኃዝ እየተምዘገዘገ ነው፡፡ ወትሮም በመላምት የሚመራው የግብይት ሥርዓት የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት አልበቃ ብሎ፣ በየቦታው የሚከሰቱ ሁከቶችና ትርምሶች ብዙዎችን ሥራ እያስፈቱ ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ከምንም ነገር በላይ ሰላምና መረጋጋት ይፈልጋሉ፡፡ ኢንቨስተሮች በራሳቸውና አገር በሚያስተዳደረው መንግሥት መተማመን ሲያቅታቸው እንቅስቃሴያቸውን ይገታሉ፡፡ በቁርጠኝነት ተነስተው መሥራት ሲያቅታቸው ይዳከማሉ፡፡ ሠራተኞችን ያሰናብታሉ፡፡ ከሥራ የተሰናበቱ ወገኖች የሚበሉትና የሚጠጡት ሲያጡ ወደ አመፅ ይገባሉ፡፡ የኢኮኖሚውን መቀዛቀዝ በቶሎ በማስቆም ወደነበረበት ደረጃ መመለስ ካልተቻለ፣ ጣጣው እንዲህ በቀላሉ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ ባንኮች ከሕዝብ የሰበሰቡትን ገንዘብ አበድረው ካልተሠራበት ኪሳራ ይከተልባቸዋል፡፡ ለንግድና ለኢንቨስትመንት የተበደሩ ሰዎች በአግባቡ ብድራቸውን ካልመሰሉ ወይም ይዘው ከጠፉ አደጋ ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት የምትፍጨረጨር አገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ ቀርቶ፣ ባለችበት ለመርገጥ እንኳን ፈጽሞ አይቻላትም፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ በእርሻ፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች እንቅስቃሴያቸው ሲስተጓጎል የአገር ኢኮኖሚ ለቀውስ ይዳረጋል፡፡ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለተለያዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎችና ለመሳሰሉት የሚሰበሰብ ቀረጥና ግብር መጠኑ ይቀንሳል፡፡ ወይም የማይሰበሰብበት ደረጃ ላይ ይደረሳል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ ሥራዎች ሲደናቀፉ ቀውሱ የበለጠ አድማሱን እያሰፋ አገር ያዳርሳል፡፡ ለሥራ ፈጠራ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ሀብታቸውን ኢንቨስት አድርገው የበለጠ ሀብት ማፍራት የሚፈልጉና በዚያው ልክ ሥራ የሚፈጥሩ ዜጎች ይታቀባሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ፀረ ንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ትኩረት ካልተሰጣቸው የበለጠ አደገኛ ይሆናሉ፡፡ እርግጥ ነው ዜጎች ተቀጥረው ሲሠሩ ተመጣጣኝ ክፍያና የሥራ ላይ ደኅንነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን አገር ኢኮኖሚን የሚያዳክሙና ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች ደግሞ ሕገወጥ መሆናቸውን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ታች እየተንሸራተተ ሥራ ማከናወን የማይቻልበት ደረጃ ላይ እስኪደረስ ቆሞ መመልከት፣ አገሪቷን የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ነው የሚከታት፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው የሕዝብ መጠን 24 በመቶ እንደሚገመት ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ አኃዝ የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸውን ወገኖች የሚወክል ነው፡፡ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ እጅግ በጣም በርካታ ከመሆኑ የተነሳ ድህነት አሁንም የአገሪቱ ትልቁ ራስ ምታት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መካከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ ከወር ወር ለመድረስ አሳራቸውን ያያሉ፡፡ ይህንን የመሰለ ፅኑ ችግር ባለበት አገር ውስጥ የፖለቲካ ቀውሱን በፍጥነት በመፍታት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት አለመቻል፣ ለበለጠና ከገቡበት ለማይወጡበት የባሰ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሲዳከም እንዳለዩ ሆኖ ከማለፍ ይልቅ፣ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሚመጥን ደረጃ በባለሙያዎች የተዘጋጀ ጥናት ቀርቦ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ሰጪ የነበረው ኢኮኖሚ ተንገጫግጮ እንዳይቆምና በተሻለ ፍጥነት እንዲንቀሳቀስ፣ አዳዲስና አዋጭ የፖሊሲ ውሳኔዎች መተላለፍ አለባቸው፡፡ በግትርነት ውጤት አይገኝም፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ ቀልጣፋና ውጤታማ አሠራሮችን በፍጥነት ማስፈን ይገባል፡፡ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ጠንቅ የሆኑ የማያሠሩ መመርያዎችና ደንቦችን አሽቀንጥሮ በመጣል፣ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረቱ ዘመናዊ አሠራሮችን በባለሙያዎች በመታገዝ ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ የአሳሪ ሕጎችና የብቃት የለሽ አመራሮች ጉዳይም መታሰብ አለበት፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳከም፣ የቱሪዝም መቀዛቀዝ፣ የጎንዮሽ ችግሮችን ያላገናዘበ የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ፣ በሥጋት ላይ የተመሠረተ የዋጋ ግመታ፣ ልቅና ሥርዓተ አልባ የግብይት ሥርዓት፣ የዜጎችን ጀርባ የሚያጎብጥ የዋጋ ግሽበትና የመሳሰሉት ችግሮች ከፖለቲካ ቀውሱ ጋር እየተመጋገቡ አገርና ሕዝብን እንዳያጠፉ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ በተለይ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እጃቸውን አስረዝመው ያስገቡ ሕገወጥ ተዋንያንና ግብረ አበሮቻቸው አደብ እንዲገዙ ካልተደረገ ቀውሱ ይባባሳል፡፡ በፖለቲካው መስክ ለተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች የማያዳግም ምላሽ በመስጠት አገሪቱን ወደ ትክክለኛው ጎዳና መመለስ የግድ ነው፡፡ በፖሊሲ ውሳኔዎች የሚስተካከሉትን በመለየት በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት ይገባል፡፡ ቀውሱ እየተባባሰ በሄደ ቁጥር የሚጎዱት አገርና ሕዝብ ናቸው፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ ያለባት አገር የአካባቢው ትልቅ ገበያ እንደ መሆኗ መጠን፣ በተፈጥሮ ሀብቶችና በቱሪዝም መዳረሻነቷ ተስፋ ያላት መሆኗ ከግንዛቤ ተይዞ፣ እንኳን ለራሷ ለአካባቢው አገሮች የሚተርፉ በርካታ ፀጋዎችና በረከቶች እንዳሏት ታስቦ፣ ወዘተ. ከቀውሱ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ብርቱ ጥረት ይደረግ፡፡ ይህ ጥረት የአገሪቱን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለማንቀሳቀስ ይረዳ ዘንድ ደግሞ ለብሔራዊ መግባባት ትልቅ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲነሱ ምኅዳሩ ይመቻች፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የአገሪቱ መላ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት መልካም አጋጣሚ ይፈጠር፡፡ ካልሆነ ግን የኢኮኖሚው ጣጣ ሌላ ቀውስ ይዞ ይመጣል!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...