የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 16 ሺሕ ቤቶች መገንባት የሚያስችለውን ዕቅድ ለማሳካት የአፈር ምርመራ፣ የዲዛይን ክለሳና አዳዲስ ዲዛይኖች ከሚሠሩለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ፈጸመ፡፡
በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. እንደ አዲስ በድጋሚ የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ከ26 ዓመታት በኋላ ቤቶች እንዲገነባ ተፈቅዶለታል፡፡
በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉት ይዞታዎቹ በማስተር ፕላኑ ዞን ሦስትና ዞን አራት ተብለው በተከፈሉ ቦታዎች፣ ከፍታቸው እስከ አሥር ፎቅ የሆኑ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ አውጥቷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በያዘው የሦስት ዓመታት ዕቅድ መሠረት እስከ አራት መኝታ ክፍል ያላቸውን ቤቶች ገንብቶ፣ በኪራይ ለመንግሥት ተሿሚዎች፣ ለሠራተኞችና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡
ዓርብ ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቀደም ብሎ በከተማ ልማትና ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሠራውን ዲዛይን ከልሰው፣ አዲስ ዲዛይን ከሚሠሩና የአፈር ምርመራ ከሚያካሂዱ ሁለት አማካሪ ድርጅቶች ጋር ተፈራርሟል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ብርሃኑ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ የዲዛይን ክለሳ አዳዲስ ዲዛይኖችና የአፈር ምርመራ ለማድረግ የተመረጡት ኩባንያዎች ያሚ እና ጂአ ውል በገቡት መሠረት በሁለት ወራት ውስጥ ሥራቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡
በደርግ መንግሥት በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን እንዲያስተዳድርና አዳዲስ ቤቶችን እንዲገነባ የተቋቋመው የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት፣ በተለያዩ መዋቅሮች አልፎ በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተብሎ ተቋቁሟል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ አዳዲስ ቤቶች እንዳይገነባ፣ ይልቁኑም ያሉትን ቤቶች ብቻ እንዲያስተዳድር ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ለመንግሥት ተሿሚዎች መኖርያ ቤት ማቅረብ ባለመቻሉና ይህም ትልቅ ቅሬታ በመፍጠሩ፣ ከዓመታት የባለሙያዎች ጉትጎታ በኋላ ወደ ግንባታ እንዲገባ ተፈቅዶለታል፡፡
የሚገነባቸውን ቤቶች ለተሿሚዎችና ለመንግሥት ሠራተኞች በዝቅተኛ ኪራይ፣ ለኅብረተሰቡ ደግሞ በገበያ ዋጋ የሚከራዩ ቤቶችን ለመገንባት ሥራውን መጀመሩን አቶ ግሩም ገልጸዋል፡፡