ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሲገነባው የነበረው የሽሮሜዳ–ኪዳነ ምሕረት መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቀቁ፣ ከታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
መንገዱ በማስተር ፕላኑ መሠረት በአጠቃላይ 2.1 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር ስፋት ኖሮት እየተገነባ እንደነበር የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ ፕሮጀክቱን ከየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ተረክቦ ግንባታውን በራሱ ለማጠናቀቅ መጀመሩን ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡
ባለሥልጣኑ በሥራ ተቋራጮች ከሚያሠራቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሽሮሜዳ–ኪዳነ ምሕረት የመንገድ ፕሮጀክት፣ ግንባታው በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ተጀምሮ በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡
ተቋራጩ ፕሮጀክቱን ከተረከበ በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግንባታ ለማከናወን ሥራዎችን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በተዋዋለበት ቀነ ገደብ መሠረት ያለውን አቅም በመጠቀም ሥራውን በአግባቡ እየሠራ አለመሆኑ የግንባታ ሒደቱን እንዲከታተልና እንዲቆጣጠር ከተቀጠረው ከቤስት አማካሪ ድርጅት ተደጋጋሚ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያዎች ሲደርሰው መቆየቱን ባለሥልጣኑ አብራርቷል፡፡
ነገር ግን ሥራ ተቋራጩ በተለያዩ ጊዜያት በተሰጡት ማሳሰቢያዎች መሠረት የግንባታ አፈጻጸሙን ማሻሻል ባለመቻሉና ያለውን አቅም ተጠቅሞ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለማጠናቀቁ ምክንያት፣ ውሉ ሊቋረጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡ በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ የተረከበውን ፕሮጀክት ማከናወን የቻለው 25 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሆን የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የወሰን ማስከበር ሥራው በወቅቱ በክፍለ ከተማውና በመሠረተ ልማት ተቋማት በኩል ባለመከናወኑ በተያዘለት ቀነ ገደብ እንዳልተጀመረ ለባለሥልጣኑ ሥራ ተቋራጩ ማመልከቱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ይኼንን ችግር ታሳቢ በማድረግ ሥራውን በአግባቡና በሚፈለገው መጠን ከወሰን ማስከበር ነፃ በሆኑ የፕሮጀክቱ ክፍል ውስጥ እንዲሠራ በከተማው ከፍተኛ አመራር፣ በባለሥልጣኑና ከአማካሪ ድርጅቱ በቂ ክትትልና ድጋፍ ቢደረግም፣ በአፈጻጸም ግን የሚጠበቀውን ያህል ሊያከናውን አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
ኮንትራክተሩ ያለበትን ክፍተት እንዲያስተካክልና አፈጻጸሙን በማሳደግ በቀነ ገደቡ መሠረት ግንባታውን እንዲያስረክብ የቃልም ሆነ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያዎች እንዲደርሰው መደረጉን ነው ባለሥልጣኑ ያስረዳው፡፡
‹‹ሥራ ተቋራጩ ባጋጠመው የውስጥ ችግርና በአቅም ማነሳ ምክንያት ግንባታው በሚፈለገው መጠን ለማከናወን እንቅፋት እንደገጠመው ለባለሥልጣኑ በደብዳቤ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ሥራ ተቋራጩ ያጋጠመው ችግር ግንባታውን በአግባቡ ለማከናወን ከገባው ውል ጋር የገጠመው እንቅፋት ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለውና ሥራውን በአፋጣኝ እንዲጀምር ባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ አስታውቋል፤›› በማለት ገልጿል፡፡
የሽሮሜዳ–ኪዳነ ምሕረት መንገድ ኅብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባለት ሲጠይቅ ነበረ፡፡ ለኅብረተሰቡ የመንገድ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ባለሥልጣኑ ዲዛይን አስጠንቶና የሥራ ተቋራጭ አወዳድሮ ወደ ሥራ ቢገባም፣ በግንባታ ሒደትም አጥጋቢ አፈጻጸም ሊመዘገብ ባለመቻሉ በኅብረተሰቡ ላይ ቅሬታዎችን ፈጥሯል፤›› ብሏል፡፡
ይኼ የመንገድ ፕሮጀክት የኅብረተሰብ ቅሬታ የፈጠረና የመልካም አስተዳደር ችግር እያስከተለ በመሆኑና ተቋራጩ ጥሩ አፈጻጸም ባለማሳየቱ፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉ ተገልጿል፡፡ የመጨረሻ አማራጭ የሆነው የውል ማቋረጥ ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ሥራ ተቋራጩ በተደጋጋሚ ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ እንደተደረገለት ተጠቁሟል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ የተሰጠውን ድጋፍ ባለመጠቀም ሥራው ተነጥቆ ባለሥልጣኑ በራስ ኃይል ለመገንባት ተገዷል፤›› ሲልም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ግርማ (ኢንጂነር)፣ ድርጅቱ ሲገነባው የነበረው መንገድ በባለሥልጣኑ መቋረጡን አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ለግንባታው መዘግየትና መቋረጥ እንደተባለው የአቅም ማነስ ሳይሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የድርጅቱ ባለቤት በመከሰሳቸው ምክንያት የድርጅቱን ንብረቶች ጨምሮ የባንክ ሒሳቡ በፍርድ ቤት በመታገዱ በገጠመው ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሥራ ተቋራጩ ባለቤት አቶ የማነ ግርማይ ባለፈው ዓመት በፀረ ሙስና ተከሰው በእስር ላይ ከሚገኙ ባለሀብቶችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው፡፡
በፍርድ ቤት እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ የተጣለበት የሥራ ተቋራጩ ንብረት የተለቀቀው በቅርቡ እንደነበር ለሪፖርተር ያስረዱት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ እንዳያጠናቅቅ የፍርድ ቤት ሒደቱን በመጥቀስ ባለሥልጣኑን የጊዜ ማራዘሚያ ቢጠይቁም፣ በውል ስምምነቱ ያልተካተተና ባለሥልጣኑን የማይመለከት ችግር ነው የሚል ምላሽ ስለተሰጣቸው ግንባታውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በተጠቀሰው ምክንያት እንጂ ድርጅታችን የአቅም ችግር የለበትም፡፡ ከዚህ በፊትም ስናከናውናቸው በነበሩ ግንባታዎች ችግር አጋጥሞ አያውቅም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
አሁን እንዲቋረጥ ውሳኔ የተላለፈበትን ፕሮጀክት አቶ የማነ ከሁለት ዓመት በፊት ቀድሞ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት አቶ ፍቃዱ ኃይሌ (ኢንጂነር) ጋር ነበር የተፈራረሙት፡፡ እንደ አቶ የማነ ሁሉ አቶ ፍቃዱም በአምናው የፀረ ሙስና ዘመቻ በተመሳሳይ ክስ ተመሥርቶባቸው በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡