Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ለቀረቡ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች የኢሕአዴግ ምላሽ እየተጠበቀ ነው

በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ለቀረቡ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች የኢሕአዴግ ምላሽ እየተጠበቀ ነው

ቀን:

አሥራ አምስት አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አራተኛ የመደራደሪያ አጀንዳ በሆነው የፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001 ላይ ተከታታይ ድርድር ሲያደርጉ፣ ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ እንዲሰረዙ፣ እንዲሻሻሉና እንዲጨመሩ ብለው ላነሷቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች የኢሕአዴግ ምላሽ እየተጠበቀ ነው፡፡

አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ለሦስት ጊዜያት ከኢሕአዴግ ጋር ባደረጉት ድርድር ስድስት አንቀጾች እንዲሰረዙ፣ አራት እንዲሻሻሉና አምስት እንዲጨመሩ ኢሕአዴግን የጠየቁ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ለረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ፓርቲዎቹ ሐሙስ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከኢሕአዴግ ጋር ባደረጉት ድርድር፣ የፀረ ሽብር አዋጁ ሕገ መንግሥቱን የጣሰና የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ያጠበበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ ቁጥራቸው አሥራ ስድስት ሲሆን፣ በአንድ ዓመት የድርድር ቆይታቸው በሦስት አዋጆች ላይ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተው የፀረ ሽብር ሕጉን ደግሞ አራተኛ አጀንዳቸው አድርገው እየተደራደሩ ነው፡፡ አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፀረ ሽብር አዋጅ ማሻሻያን በተመለከተ ለሦስተኛ ጊዜ ድርድር አድርገዋል፡፡

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር ባደረጉት ድርድር የፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ያጠበበና የዘጋ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከፀረ ሽብር አዋጅ ውስጥ ስድስት አንቀጾች እንዲሰረዙ፣ አራቱ እንዲሻሻሉና አምስት ቢጨመሩ ያሏቸውን ዘርዝረዋል፡፡

ለአብነት ያህል የቴሌኮሙዩኒኬሽን አጠቃቀም አዋጅ አንቀጽ 19 ከፀረ ሽብር ሕጉ ጋር እንዲዛመድ በመደረጉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቁጥጥር አዋጅ አንቀጽ 19(5) ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ መረጃን የማግኘትና የመስጠት መብትን እንደሚገድብ ገልጸው፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ከቁጥር 1 እስከ 4 ድረስ ከተገለጹት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጋር ተጣጥሞ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

አዋጁ የፕሬስ ነፃነትን፣ ጋዜጠኞችና ዓምደኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን የሚከታተልና መረጃ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እንደሚያዳክም የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበርና የአሥራ አንዱ አገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካይ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ድንጋጌዎችን በአንቀጽ 13 የሕግ አካል መደረጉን የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ልዩነት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱትን የሰብዓዊና የነፃነት መብቶች እንዲያከብር በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ እንደሆነ ፓርቲዎቹ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋም መቋቋማቸውን፣ እነዚህ ተቋማት እ.ኤ.አ. የ1993 የፓሪስ የሰብዓዊ መብት ዲክላሬሽን በአግባቡ መተግበር እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ተፈጻሚ እንዳላደረገውና የፍትሕ አካላትም በየጊዜው ሲጥሱት ማየት የተለመደ እንደሆነ ፓርቲዎቹ አስረድተዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ቢስተካከሉ ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ የመተባበር ግዴታ፣ ዛቻ የሚለው ቃል፣ ሽብር የሚለው ቃል ትርጉም፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ የስልክ ጠለፋና የናሙና አሰጣጥ (ተመጣጣኝ ዕርምጃዎች)፣ የስሚ ስሚ፣ በማሰብ፣ ሰላም መባባል፣ አብሮ መቀመጥና መጋበዝ፣ ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

እንዲሻሻሉ የተፈለገበት ምክንያት ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም፣ አዋጁ ሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚቃረን በመሆኑ፣ ወደ ተግባር ከተሸጋገረ በኋላ አሻሚ ትርጉም የያዘ ከመሆኑ በላይ የሽብርተኝነት ድርጊቶችን ያልለየና ንፁኃንን ያካተተ በመሆኑ፣ የሚዲያ ሰዎችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኢንተርኔት ዓምደኞችን፣ የሰብዓዊ መብት አንቀጾችን የሚፃረርና በነፃነት የማሰብ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ የስልክ ንግግሮችንና የሕዝብ መገናኛዎችን የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የሚቃረንና ሌሎች መብቶችን የሚጥስ በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈታሉ ስለተባሉ ግለሰቦች ጉዳይ ለምን እንደ ዘገየ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ኢሕአዴግ በፀረ ሽብር ሕጉ መሰረዝ፣ መሻሻልና መካተት አለባቸው በሚላቸው አንቀጾች፣ እንዲሁም እፈታቸዋለሁ ስላላቸው እስረኞች ዝርዝር ምላሽ እንዲሰጥ ለረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም.  ቀነ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...