የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ቀጣይ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በጠየቀው የግልጸኝነትና የአካሄድ ሥርዓት በተነሳ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ መከናወን ሳይችል ቀርቶ እንዲራዘም ተደርጎ ነበር፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ በፊፋ የምርጫ ሥርዓት ‹‹ገለልተኛና ብቃት›› ከሚለው በተቃራኒ ‹‹ውክልናን›› መነሻ ያደረገ የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ መደረጉ አይዘነጋም፡፡
ለምርጫው መራዘም ምክንያት በሆነው የፊፋ የግልጸኝነትና የሥርዓት ጥያቄን መሠረት በማድረግ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ፣ የምርጫ ሒደቱን በታቀደለት መልኩ ዕውን ማድረግ ይቻል ዘንድ በተለይ የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ግለ ታሪክና ለምርጫ የሚያስፈልጉ መሰናዶዎችን አጠናቆ ዓርብ ታኅሣሥ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ከአስመራጭ ኮሚቴው አሰያየም ጀምሮ አንዳንዶቹ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ የቀረቡበት ሥርዓት ክፍተት የነበረበት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ያለውን ነገር በማቻቻል ለምርጫ የሚቀርቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎችንም ሆነ ምርጫውን ማከናወን በሚያስችል መልኩ የተጣለበትን ኃላፊነት ማጠናቀቁን የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኰንን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ከታኅሣሥ 16 ወደ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም የተደረገው ምርጫም በተያዘለት ቦታ፣ ቀንና ሰዓት እንደሚከናወን በዕለቱ ተናግረዋል፡፡
ጥር 5 ቀን በአፋር ሰመራ ሊከናወን ቀንና ሰዓት ተቆርጦለት የሰነበተው ምርጫ ‹‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይስቅም›› እንዲሉ፣ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ይህኛውን ከወትሮው ለየት የሚያደርገው ለጠቅላላ ጉባዔ አባላት ጥሪ ተደርጎ፣ የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪዎች ተፈጽመው እንዲያውም የአንዳንድ ክልሎች የጉባዔ አባላት ምርጫው ወደ ሚደረግበት ክልልና ከተማ ጉዞ በጀመሩበት ሁኔታ ላይ መሆኑ ግርምትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
ምክንያት ተብሎ እየቀረበ ያለው ደግሞ፣ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኰንን ታኅሣሥ 6 ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በዋናነት ከስፖርት መገናኛ ብዙኃኑ የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የጥር 5 ምርጫ ከመደረጉ በፊት ከአስመራጭ ኮሚቴው አንዳንዶቹ ‹‹የተገቢነት ጉዳይና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ፤›› በሚል ለፊፋ በጻፉት ደብዳቤ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሥጋትና የፊፋ የ‹‹ይራዘም›› ውሳኔ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደረሰው ማክሰኞ ጥር 1 ቀን ከሰዓት በኋላ ሲሆን፣ ይፋ የሆነው ደግሞ ረቡዕ ጥር 2 ቀን ነው፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹አገር መቀጣት የለበትም›› ለሚለው ሰሞነኛ ቀልድ ይኼ ጥሩ ማሳያ ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴውን ሰብሳቢ ጨምሮ ኅዳር 14 ቀን በተጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ጥንቅር፣ የፊፋ የምርጫ ሥነ ምግባር ኮድ እንደሚለው ‹‹ገለልተኛና ብቃት›› ከሚለው በተቃራኒ ውክልናን መነሻ በማድረግ የተከናወነ ስለነበረ ነው፡፡ ይህም ለእግር ኳሱ ትልቁ የሥልጣን አካል ተደርጎ በሚወሰደው ጠቅላላ ጉባዔ ሲወሰን፣ ከሰሞኑ እንደተደመጠው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተመሳሳይ ዓይነት የአካሄድ ስህተት ስለመሆኑ ከአቶ ዘሪሁንም ሆነ ከሌሎች አካላት ቅሬታ ሲቀርብ ለምን እንዳልተደመጠ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
አቶ ዘሪሁን ለፊፋ የጻፉትን ደብዳቤ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአስመራጭ ኮሚቴው ብዙዎቹ አባላት ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ ሰብሳቢው ለዚህ ውሳኔያቸው ከነማን ጋር ተነጋግረው ደብዳቤውን ሊጽፉ እንደቻሉ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ጭምር ነው የሚያስረዱ፡፡
በሰብሳቢው ውሳኔ ቅሬታ እንደገባቸው የሚናገሩት የኮሚቴው አባላት፣ ምርጫው ለሁለት ወር ያህል እንዲራዘምና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕጋዊ ባልሆነ አካል እንዲቀጥል የሆነበትን አሠራር ጭምር ይተቻሉ፡፡ እንደ ብዙዎቹ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት እምነት፣ ምርጫውን ተከትሎ እየተደመጠና እየተስተዋለ ለሚገኘው አለመግባባትና ትርምስ በዋናነት ሰብሳቢው ለፊፋ ይፋ እንዳደረጉት ‹‹የመንግሥት ጣልቃ ገብነት›› ሳይሆን የግል ፍላጎትና ቡድንተኝነት ምክንያት የመጣ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ኮሚቴው አካላት፣ ‹‹ሰብሳቢው በዋናነት የመሪነት ሚና ቢኖራቸውም፣ እኛም በጉባዔው ሙሉ እምነት ተጥሎብን እስከተመረጥን ድረስ፣ በእያንዳንዱ ውሳኔና አካሄድ ላይ የሚኖረን አስተያየት ሊደመጥ ይገባል፤›› በማለት የአቶ ዘሪሁንን ውሳኔ እንደማይቀበሉት ያስረዳሉ፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኰንን በበኩላቸው፣ ከጋዜጣዊ መግለጫ ዕለት ጀምሮ በአስመራጭ ኮሚቴው በተለይም በአንዳንዶቹ አካሄድና ውሳኔ ድምፀ ተአቅቦ እንደነበራቸው፣ ይህን ኃላፊነት ሲቀበሉ ሕግን ለማስከበር እስከሆነ ድረስ በውሳኔያቸው እንደማይፀፀቱ ነው የሚናገሩት፡፡
ታኅሣሥ 6 ቀን በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ የምርጫውንና የአስመራጭ ኮሚቴው አጠቃላይ አካሄድን አስመልክቶ በተለይ ከመገናኛ ብዙኃን ቀርበው የነበሩ የአሠራርና የአካሄድ ክፍተቶች ላይ ይፋ ያላደረጓቸውን ጉዳዮች ከሰሞኑ እንደተሰማው ለፊፋ ግልጽ አድርገዋል ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹በግሌ ይህን ኃላፊነት ከተቀበልኩበት ዕለት ጀምሮ ፍላጎቴ ሕግ እንዲከበር ነው፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለትም ቢሆን፣ በብዙዎቹ ጉዳዮች በድምፅ ብልጫ ካልሆነ ውሳኔዎቹ ያመንኩባቸው እንዳልነበሩ ተናግሬያለሁ፡፡ ምክንያቱም በግልጽ በተቀመጠ ሕግ በእጅ ብልጫ በሚባለው ነገር አላምንም፡፡ ተገቢነት ያለው አሠራርም ነው ብዬ አልወስድም፡፡ አንዳንዶቹ ውሳኔዎች ላይ በድምፀ ተአቅቦ ስወጣ የነበረው ለዚህ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
ለዚህ ሁሉ ችግርና እሰጣ ገባ ዋናው ተጠያቂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መሆኑን የሚያክሉት አቶ ዘሪሁን፣ ከችግሮቹ አንዱና የመጀመርያው ‹‹ፌዴሬሽኑ ምንም ዓይነት የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ የለውም፡፡ ፊፋ አሁን የምንወዘጋገብበትን የምርጫ ደንብና ሥርዓት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያሳወቀው እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ ለዓመታት የቆየውን የምርጫ ደንብና መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ ለምን እንዳልተፈለገም ግልጽ አይደለም፤›› በማለት በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያለውን ግልጸኝነት የሌለውን የአሠራር ሥርዓት ይኮንናሉ፡፡
በሰብሳቢው እምነት የፊፋ የምርጫ ኮድ በተገቢው መንገድ ካልተፈጸመ በአገሪቱ ዕገዳ እንደሚጣል ነው፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እሳቸውን ጨምሮ ለአስመራጭ ኮሚቴነት የሰየማቸው አባላት፣ የክልል ውክልና ይዘው የመጡ መሆኑ ከፊፋ የአስመራጭ ኮሚቴ ሕግና ደንብ አንፃር እንዴት ይታያል? ለሚለው አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹ወደዚህ ኃላፊነት ምረጡን ብዬ አልመጣሁም፤›› ብለው ለዚህ ውሳኔያቸው መገናኛ ብዙኃኑ በየቀኑ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቧቸው የአካሄድ ስህተቶች መሆናቸውን ጭምር ተናግረዋል፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የሰብሳቢውን ውሳኔ እንደማይቀበሉ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹በሰብሳቢነቴ ያመንኩበትንና የነገውን የአገሪቱን እግር ኳስ ዕጣ ፈንታ ከመታደግ አኳያ የወሰንኩት ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም ምንም ዓይነት የበደለኝነት ስሜት አይሰማኝም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና ቀጣዩን የምርጫ ጊዜ በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ አላስደሰታቸውም፡፡ ምክንያቱም ምርጫው እስከ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ መራዘም አልነበረበትም ባይ ናቸው፡፡
የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ስለሚባለው አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ሲጀምር ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ አንዱና የመጀመርያው የፊፋ የምርጫ ኮድ ሲሆን፣ ሁለተኛው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በወጣቶችና ስፖርት ማኅበራት ስለሚደራጁበት የወጣው መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በተለይም ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አስመልክቶ፣ አስመራጭ ኮሚቴው ማብራሪያ ባልጠየቀበት ሁኔታ የተጻፈውን ደብዳቤ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ሌሎች የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ግን በኃላፊነት ቆይታቸው ሰብሳቢው እንደሚናገሩት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳልነበረ፣ ችግሩ ከራሱ ከአስመራጭ ኮሚቴውና ከፌዴሬሽኑ እንደሚመነጭ ነው የሚናገሩት፡፡
የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ባልሰጣቸው ሥልጣን ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እያስተዳደሩ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው ‹‹በምርጫው መራዘምም ሆነ አለመራዘም የእሳቸው ካቢኔ እንደማይመለከተው፣ ለጥር 5ቱ ምርጫ አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶ የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪዎች ተጠናቀው፣ በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ዝግጁ ሆኖ ሳለ ነው ፊፋ የአስመራጭ ኮሚቴውን ሰብሳቢ አቤቱታ መነሻ በማድረግ ምርጫው እንዲራዘም የጠየቀው፤›› ብለዋል፡፡
ፊፋ ምርጫው እንዲደረግ ባስቀመጠው ቀንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስቀመጠው ቀን መካከል ከሁለት ሳምንት ያላነሰ የቀን ልዩነት ከመኖሩ አኳያ አቶ ጁነዲን፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ ቀጣዩ ምርጫ ወደ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም ያደረገበት ዋናው ምክንያት፣ እ.ኤ.አ. ከየካቲት 4 (በኢትዮጵያ ጥር 27 ቀን 2010 ዓ.ም.) በኋላ ካልሆነ ለምርጫው ታዛቢ መላክ እንደማይችል በተገለጸልን መሠረት ያለውን የተጣበበ ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት ገፋ እንዲል ማድረጋችን ስህተት ሊባል አይችልም፡፡ ይልቁንም ውሳኔያችን ነገሮች ተረጋግተው አስመራጭ ኮሚቴውም አሉ የሚላቸውን ክፍተቶች በደንብ አጥርቶ እንዲቀርብ ከማሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአሁኑ ወቅት ምርጫውን ተከትሎ ለተፈጠረው አለመግባባትና ሽኩቻ በዋናነት ፌዴሬሽኑን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ለዚህም አቶ ጁነዲን ‹‹የፌዴሬሽኑ ችግር ተደርጎ በአስመራጭ ኮሚቴውም ሆነ በአንዳንድ ወገኖች እንደ ክፍተት እየተጠቀሰ ያለው፣ ከአሥር ዓመት በፊት ፊፋ ለፌዴሬሽኑ እንዳደረሰ የሚገነርለት የምርጫ ኮድ ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ስህተት የእናንተ አመራር ደግሞታል ከሆነ እቀበላለሁ፣ ከዚህ ባለፈ ግን ለአሁኑ ምርጫ እየተወዳደሩ ያሉ አንዳንድ አባላትም ጭምር ጉዳዩን የሚያውቁት በመሆኑ ስህተቱ የእነሱም ተደርጎ መታየት ይኖርበታል፤›› በማለት ነው ጥያቄውን በጥያቄ የመለሱት፡፡