Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተር‹‹ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቁልቁለት ጐዳና››

‹‹ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቁልቁለት ጐዳና››

ቀን:

መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በታተመው የአማርኛው ሪፓርተር ጋዜጣ ‹‹ዲላ ዩኒቨርሲቲ አልሞተም!›› በሚል ርዕስ (የጋዜጣው አዘጋጅ የሰጠው) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት የልቀት ማዕከል ሆኖ መመረጥ እንዴት ተሳነው በሚል ቁጭት አዘል ጥያቄ ዙርያ የምታጠነጥን መጣጥፍ ጽፌ፣ ታትማ ለንባብ መብቃቷም ይታወሳል፡፡

ይህች ጽሑፍ ከታተመች በኋላ በመደገፍም ሆነ በመቃወም ምላሽ የሚሰጥ ይኖራል ብዬ ብጠብቅም የጻፈ የለም:: በጽሑፍ ባይሆንም፣ ያነበቡና የሚያውቁኝ በቀጥታ አስተያየታቸውን የመስጠታቸውን ያህል በተዘዋዋሪ ‹‹በድሮ በሬ ለማረስ የማሰብ ያህል ነው›› በማለት ትችታቻውን የሰነዘሩም አጋጥመውኛል::

ይኼን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝም ‹‹በድሮ በሬ ማረስ …›› የሚለው ትችት ትክክል መሆኑን በማረጋገጤና ቀደም ብዬ በጻፍኩት ጽሑፍ ለደቡብ ክልልና በዙሪያው ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን ትምህርት የልቀት ማዕከል ሊኖር ይገባል ዓይነት ሐሳብ በጥያቄ መልክ ጠቆም ማድረጌ ተቀባይነት አግኝቶ መሰለኝ፣ ሰሞኑን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት የልቀት ማዕከል ሆኖ መመረጡን ለማወቅ ችያለሁ::

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ከዲላ የመምህራን ትምህርት በምን የተሻለ ሆኖ እንደተገኘ መረጃ ስለሌለኝ ተቋሙ ለዚህ መታጨቱ አይገባውም ወይም ልክ ነው፤ ተገቢ ነው ማለት አልችልም:: የጻፍኩትን ከጻፍኩ በኋላ ባገኘሁት መረጃ መሠረት ግን በእርግጠኝነት ማለት የምችለው፣ ቀደም ብለው በመምህራን ትምህርት በልቀት ማዕከልነት ከተመረጡት ሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሊሆን አለመቻሉ ትክክል መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት በጻፍኩት ጽሑፍ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ካደገ በኃላ የመምህራን ትምህርቱ ያለበትን ሁኔታ ባለማጤን በድሮ አፈጻጸሙ ላይ ብቻ በማተኮር የጅማና የመቐለ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን ትምህርት ረገድ ያሉበት ደረጃ፣ ያሳዩት መሻሻል፣ የሚገኙበት የዕድገት ሁኔታ፣ ያሳዩትን ለውጥ ካለማወቅ እንደሆነ አሁን ተረድቻለሁ:: የሰው ልጅ በቂ መረጃ ሳያገኝ በመሰለኝና በስሜት ሲወስን ወይም ስሜቱን ሲገልጽ እንደሚሳሳት ከዚህ በፊት የጻፍኩት ጽሑፍ ማሳያ ነው፡፡

ስህተቱ የሚከፋው ደግሞ በቂ መረጃ ካገኘና ዕውነቱን ከተረዳ በኃላ ከዚህ በፊቱ በተሳሳተው አቋሙ የፀና እንደሆነ ነው፡፡ የብዙዎች ችግርም ይኼው ነው፡፡ እኔ መሳሳቴን ሳውቅ ተሳስቻለሁ የማለት ልምድ አለኝ፡፡ ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ልምድ እንዲኖራቸው እመክራለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍም ይኼንኑ ነው ያደረግሁት፡፡

ወደ ጉዳዩ ስመለስ ምንም እንኳ ውልደት ቀዳሚ መሆን በሥራ አፈጻጸም ቀዳሚ መሆንን ባያመላክትምበመምህራን ትምህርት ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ፣ ከባህር ዳር፣ ከኮተቤና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ተከታይ ሆኖ እንደሚጠቀስ ይታወቃል:: ‹‹ምጥ ለእናቷ አስተማረች፤›› የሚለው ምፀታዊ አባባል እዚህ ላይ ተቀባይነት የለውምምክንያቱም ልጅቱ በአዋላጅ ነርስነት የሠለጠነች ከሆነች እናቷን ስለ ምጥና አወላለድ ልታስተምር ትችላለችና።

ይኼንን ጽሑፍ እንድጽፍ ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት የለውም፤›› የሚለው አሳማኝ ብሒል ነው። ምክንያቱም የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የመምህራን ትምህርት ተቋማት ከኋላው ተነስተው በልቀት ማዕከልነት መመረጥ ሲችሉ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ግን በድሮ ዝናው እየተኩራራ በቁልቁለት ጐዳና እንደሚንደረደር አውቆ ካላሳወቀ፣ ዕርዳታና ዕገዛ ካላገኘ፣ ጭራሹን በአፍ ጢሙ መደፋቱ ስለሚሆን፣ የሚመለከታቸው ሁሉ ተቋሙን ከሞት እንዲታደጉት በማሰብ ያስተዋልኳቸውን ዋና ዋና ችግሮች ለመጠቆም ነው።

ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከመሰየሙ በፊት፣ ዲላ የመምህራን ትምህርትና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እየተባለ ይጠራ በነበረበት ጊዜ፣ የትምህርት ጥራትን ጠብቆ ምርጥ መምራንን በማፍራት አገሪቱ የነበረባትን ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል ችግር በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ዕጥረት በመቅረፍ ረገድ  የታወቀና ስመ ጥር እንደነበር ይታወሳል። በነበር ብቻ ቀረ እንጂ!

በየትኞቹ መፈርቶች የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት እንዳገኘ እኔ አንዱ ግለሰብ ቀርቶ ተቋሙም ግብረ መልስ ስላልተሰጠው ድክመቱ የቱጋ እንደሆነ የሚያውቀው አይመስለኝም። ቀደም ብዬ በጻፍኩት ጽሑፍ እንደጠቀስኩትና እንደጠየቅሁት፣ የልቀት ማዕከል ለመሆን የሚያበቁትን መሥፈርቶች ዝርዝርና ግብረ መልስ ላልተመረጡትም ለተመረጡትም በግልጽና በይፋ ማሳወቁ ወደፊት ከፍተኛ ውጤት ያገኙባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዝቅተኛ ውጤት ያገኙባቸውንም ለማሻሻል ጥረት እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ማሳወቁ ተገቢ ነው

እንደምገምተው የልቀት ማዕከል መምረጫው መሥፈርት ብቃት ያላቸው መምህራንን፣ ርዕሰ መምህራንንና ሱፐርቫይዘሮችን ከማፍራት ጋር ተያያዥ የሆኑ ተጨማሪወሳኝ መሥፈርቶች እንዳሉ ነው። ለምሳሌ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ምንም እንኳ በየመቱ በትምህርት ዙያ ዓመታዊ የትምህርት ጉባየሚያካሂድ ቢሆንም አንድ ዓመት ዕድሜው እስካሁን የምርምር ሔት ወይም ጆርናል ማሳተም አለመጀመሩ አንዱ ድክመቱ ነው። የጊዜውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመማር ማስተማሩን ሥርዓት ማዘመኑ ላይም ዲላ ዩኒቨርሲቲ ውስንነት አለበት። ከድሮውና ከባህላዊው የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ያልወጣ መሆኑ ነጥብ ሊያስቀንስበት እንደሚችል ግልጽ ነው።

ስለዚህ ዋናው የዕርምትና የማስተካከያ ዕርምጃ የሚጠበቀው ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርትና ሥነ ባህሪይ ኢንስቲትዩት ስለሆነ፣ ተቋሙ ውስጡን ፈትሾ ያሉበትን ችግሮችና ድክመቶች አንጠርጥሮ በማውጣት ለማሻሻልና ለተወዳዳሪነት ተግቶ መሥራት የሚጠበቅበት ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት በዚህ ኢንስቲትዩት የሚስተዋለው ብዙዎች የሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩ መምህራን ኑሯቸውን ከዲላ ከተማ ውጭ ከዘጠና ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ከሚገኙ ከተሞች አድርገው ተመላላሽ መምህራን ስለሆኑ፣ የሚያስተምሩትን ኮርስ እንደነገሩ ለመጨረስ ከመሯሯጥ ባለፈ ተቋሙን ለማሳደግና ከእህት ተቋማት ጋር ተወዳዳሪና የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ፍላጐቱና ቁጭቱ ቢኖራቸው እንኳ የሚችሉት አይመስለኝም።

ዲላ ዩኒቨርሲቲ ችግሮች አንዱና ዋነኛው ልምድ ያላቸው መምህራንን ማቆየት አለመቻሉ ስለሆነ፣ ‹‹የድኅረ ምረቃ ትምህርታችሁን ከጀመራችሁበት እስካጠናቀቃችሁበት ጊዜ ድረስ የተከፈላችሁን ደመወዝ ከፍላችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ እስከከፈላችሁ ድረስ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፤›› እያለ ከመሸኘት ይልቅ የመምህራንን ፍልሰት ለመቀነስ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ሌላ መላ በማበጀት ዩኒቨርሲቲውን ከውድቀት መታደግ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን  ከመጀመርያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊሆን ቀርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎችም በታች እንዳይሆን ሥጋት አለኝ። ልምድ ያላቸውንና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩ መምህራንን እየሸኙ፣ በየዓመቱ አዳዲስና ጀማሪ መምህራንን መቅጠር፣ ዩኒቨርሲቲውን ከመዘጋት ይታደገው ይሆናል እንጂ ሊያሳድገው ስለማይችል ይታሰብበት!

(ተሰማ አያሌው፣ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...