Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አጥር አልባው ባቡር

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር ፕሮጀክት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በይፋ ጀምሯል፡፡ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማጓጓዝ ዕቅድ የተያዘለት ይህ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ዋነኛ ተግባሩ የአገሪቱን የወጪና ገቢ ምርቶች ማጓጓዝ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በዓመት ከሚያገኘው ገቢ ውስጥ 80 በመቶው ከዚሁ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያገኘው እንደሚሆን ስለ አገልግሎቱ የተሰጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባቡሩ በዓመት ከአራት ሚሊዮን ቶን በላይ የወጪና ገቢ ሸቀጦችን እንደሚያጓጉዝ ይጠበቃል፡፡

እንደተባለው ወይም በዕቅድ እንደተቀመጠው በኢትዮ ጂቡቲ የምድር የምድር ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት የዕቃ ማጓጓዝ ሥራው በአገሪቱ የትራንስፖርትና የሎጀስቲክ አገልግሎቱን አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ያደረገ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የማጓጓዣ ዋጋው በመቀነስ ጊዜንም በመቆጠብ ከፍተኛ ተጠቃሚነት የሚኖረውም መሆኑ ነው፡፡

የባቡሩ ሥራ መጀመር ከጂቡቲ ወደብ ወደ መሐል አገር ዕቃ በተሽከርካሪ ለማመላለስ ቀናት ይወስድን የነበረውን ጊዜ ወደ ሰዓታት ያሳጥረዋል፡፡ ማልዶ ከጂቡቲ ወደብ የተነሳ ባቡር ከቀትር በኋላ ሞጆ ደረቅ ወደብ መድረሱ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተግባር ይታይ ዘንድም በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በወጪና ገቢ ንግዱ ላይ እንዲህ ያለ ቀልጣፋና አዋጭ የትራንስፖርት አገልግሎት መምጣቱ፣ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፡፡ ከአገሪቱ፣ ከአስመጪው፣ ከነጋዴው በተጨማሪ ተጠቃሚው በዋጋ ተመጣጣኝ ምርቶች ማግኘት የሚችልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህም ሲባል ከውጭ የሚገባ ምርት በአንድ ቀን መግባቱ በተሽከርካሪ ለቀናት ተጓጉዞ ይገባ ለነበረው ምርት ማጓጓዣ ይወጣ የነበረውን ወጪ በእጅጉ ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡ የማጓጓዣና የሎጂስቲክስ ዋጋ ከቀነሰ፣ በተለይ በርካታ ጭነት የሚጓጓዝባቸው ምርቶችን የሚያስመጡ ነጋዴዎች ቀድሞ ከሚያወጡት ይልቅ በባቡሩ ምክንያት ቅናሽ ማውጣቸው ግልጽ ነው፡፡

የገቢ ምርቶች የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪ ከቀነሰ፣ ከቀድሞ ይልቅ በአነስተኛ ዋጋ ምርት ወደ ገበያ ሲገባ የዋጋ ለውጥ ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስካሁን ባለው ተሞክሮ እስከ 40 በመቶ የሸቀጦች ወጪ ለትራንስፖርትና ለሎጂስቲክስ የሚወጣ ነው፡፡ በመሆኑም የባቡሩ መምጣት ይህንን ወጪ ስለሚቀንሰው፣ በችርቻሮ የመሸጫ ዋጋዎች ላይ ቅናሽ ሊኖር እንደሚችል ያሳያል፡፡  አስመጪዎቻችንም ይህንን ታሳቢ እንደሚያድረጉና ዋጋ እንደሚቀንሱልን ይጠበቃል፡፡

በትራንስፖርት ማጓጓዣ ወጪ ጫና ምክንያት ይቀርቡ የነበሩ ሰበባ ሰበቦችም ይቀንሳሉ ማለት ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርቱ ትርጉም ያለው አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ አንዱ መለኪያም ይህ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ገበያው እንዲመራ ማድረግ ይገባል፡፡ አንድ ምርት ሸማቹ ድረስ ለማድረስ ይፈጅ የነበረው ወጪ ከቀነሰ በምርት መሸጫው ዋጋ ላይ ቅናሽ መደረግ ይጠበቅበታል፡፡

የአዲስ ጂቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት፣ ወደ አገር ውስጥ ጭኖ ሊያስገባው የሚችለው ሸቀጥ መጠን አሁን ባለው ስሌት አራት ሚሊዮን ቶን ከሆነ፣ ከአገሪቱ ገቢ ምርቶች ወደ አንድ አራተኛ የሚጠጋውን ድርሻ ሊይዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ በዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ምርቶቻቸውን የሚያስገቡ አካላት ምን ጥቅም አገኙ? ለገበያውስ ምን አተረፉለት ተብሎ መታየት አለበት፡፡

የአዲስ አበባ የጂቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ መጠቀስ ያለበት ሌላው ጉዳይ ከአደጋ ሥጋት ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ ከ650 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው የባቡር ሃዲድ ምንም ከለላ ወይም አጥር የሌለው በመሆኑ፣ በቀላሉ አደጋ የማድረስ ዕድል አለው፡፡ ይህንን ያህል ኪሎ ሜትር ሲያቆራርጥ፣ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ወደ ባቡር ሃዲዲ ገብተው አደጋ እንዳያደርስባቸው፣ ባቡሩ ያሳፈራቸው ሰዎችና ንብረቶችም ላይ አደጋ እንዳይከሰት በባቡሩ መስመር ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ከአደጋ የሚጠበቁበት አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህ ጉዳይ በቀላሉ ሊታይና ሊታለፍ አይገባውም፡፡ እንደሰማነውም አገር አቋራጩ ባቡር ከወዲሁ በርካታ ግመሎችን ገድሏል፡፡

ከባቡሩ ዘመናዊነትና ፍጥነት ጋር ተያይዞ ስለባቡሩ ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው ወገኖች እንዳይጎዱ፣ ባቡሩ በሚያልፍባቸው ቦታዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን የማስጠንቀቅና የማስተማር ኃላፊነት ቸል ሊባል አይገባውም፡፡ ይህንን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስተዳድረው አካል ዜጎች ከአደጋ የሚጠበቁባቸውን ሌሎች አሠራሮች በአስቸኳይ መግበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህም አደጋ ከደረሰ በኋላ ሳይሆን፣ ከወዲሁ ታስበት ታቅዶና ተጠንቶ ሊደረግ የሚገባው በመሆኑ መንግሥት እልባት ያበጅለት ዘንድ ይገባል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት