Tuesday, November 28, 2023

‹‹በታሪካችን በየትኛውም ጊዜ ዓይተነው የማናውቀው ተማሪ ሌላ ተማሪን የሚገድልበት ሁኔታ ተፈጥሯል››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ ከሃያ ስድስት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ፓርቲው አገሪቱን በመምራት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረበት ጊዜ ውስጥ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተከሰቱ ባሉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶች፣ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከመታወኩም በላይ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ለአሥር ወራት ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ተቋቁሞ የነበረው ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ‹‹በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ የሚቀሩ ትንንሽ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱን በመደበኛው የሕግ አግባብ መፍታት ይቻላል፤›› በማለት ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በሁለት ወራት ልዩነት ውስጥ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለበት ምክንያት፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት እጅ እንዳለበት በመሆኑ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል፡፡ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሳይበርድ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚማሩ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ብሔር ተኮር ግጭት የአራት ተማሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህን ግጭት ተከትሎ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ለቀው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ምክንያት እስካሁን ወደ ግቢያቸው ያልገቡ ተማሪዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡

መንግሥት መጠነ ሰፊ የሆነውን ቀውስ ለማስቆም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አቋቁሞት እንደነበረው ኮማንድ ፖስት ሁሉ፣ የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት በማቋቋም ወደ ሥራ ከገባ ከአንድ ወር በላይ አስቆጥሯል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ዓርብ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄዶት በነበረው ዝግ ስብሰባ፣ አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት ያመጣል ተብሎ የታመነበትን ዕቅድ አውጥቶ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

የጋራ የፀጥታ ምክር ቤቱ ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የዕቅዱን የአንድ ወር ተኩል ግምግማ ያካሄደ ሲሆን፣ ግምገማውን በተመለከተ የመከላከያ ሚኒስትርና የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ረቡዕ ጥር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በጦር ኃይሎች የመኮንኖች ክበብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንደተናገሩት፣ የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት ተቋቁሞና የጋራ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ምክንያት ባለፈው አንድ ወር ተኩል በአገሪቱ የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡

በወቅቱ ከነበሩ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የትም አካባቢ ሆነው ሀብት አፍርቶ የመኖር መብቶች ሲገደቡ እንደቆዩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሰበቦችን በመፈለግ ሕገወጥ ሠልፎችን ማካሄድ፣ ሕገወጥ መሣሪያዎች ማዘዋወር፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግጭቶች መቀስቀስ የተለመዱ ጉዳዮች ሆነው መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባለው ግጭት የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲጣስ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአወዳይ ወደ ጅግጅጋና ሌሎች አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን መስታወት ከመስበር ባሻገር፣ በሾፌሮችና በባለሀብቶች ላይ የአካል ጉዳትና የንብረት ዘረፋ ሲካሄድ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ሲራጅ፣ ‹‹በዋና ዋና አውራ መንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ተሽከርካሪዎችን ጭምር መስታወታቸውን የመሰባበር፣ የማስቆምና ዘርን እየለዩ የመተናኮል ችግሮች ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴዎችን የመገደብ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

አቶ ሲራጅ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ የፀጥታ ምክር ቤቱ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ የሠራቸውን ሥራዎች ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ችግር ያሉባቸውን ዋና ዋና መንገዶች የመለየት፣ በተለዩ አካባቢዎች ላይ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላትን በማሠማራት ሰላማቸው እንዲጠበቅ የማድረግ፣ በሕገወጥ ተግባር የሚሳተፉትን በቁጥጥር ሥር የማዋልና ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ዋና ዋና መንገዶች የተሻለ መረጋጋት እንደሚታይባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት እንዳልሆነና ኪስ አካባቢዎች አሁንም ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጠያቂ የምናደርግበትን የጋራ መግባባት ፈጥረናል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሠልፎች እየተካሄዱ ነበር፡፡ ሠልፎቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲካሄዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ሲካሄዱ የነበሩ ሠልፎችን በተመለከተ ሚኒስትሩ የጋራ የፀጥታ ምክር ቤቱ የገመገመውን ጉዳይ አውስተዋል፡፡

‹‹ሕገወጥ ሠልፎች ነበሩ፡፡ በዚች አገር ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ የፈለጉትን መቃወምና መደገፍ ይቻላል፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት አስተዋጽኦ አለው፡፡ አሁን ያሉት ሕገወጥ ሠልፎች ግን የሚመለከተውን ሕጋዊ አካል በማሳወቅ የሚካሄዱ አይደሉም፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር የሚካሄዱ ናቸው፡፡ የሠልፎቹ አዘጋጆች ወይም ባለቤቶች በቅጡ አይታወቁም፡፡ ማን እንደሚያደራጃቸው አይታወቅም፡፡ ሠልፎቹ ከተካሄዱ በኋላ ደግሞ የሕዝብን ሀብትና ንብረት የሚያወድሙ ናቸው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሠልፎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችን ዓርማ ይዘው የሚደረጉ መሆናቸውን አቶ ሲራጅ አክለው ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው ያለው የፀጥታ አካል በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በማረጋጋትና በማስተማር፣ እንዲሁም በነውጥ የሚመሩ አካላት ካሉ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በመሠራቱ የሚደረጉ ሠልፎችና ነውጦች በየጊዜው እየቀነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ቆመዋል ማለት አይደለም፡፡ አሁንም በትምህርት ቤቶችና አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሕገወጥ ሠልፎችን ለማስቀጠል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ተቀስቅሶ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት የመማር ማስተማሩ ከመስተጓጎሉ በላይ፣ በርካታ ተማሪዎች ግጭቱን በመፍራት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄዳቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ሲራጅ ተማሪ ሌላ ተማሪን የሚገድልበት ሁኔታ መፈጠሩን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

ይህ ዘግናኝና ሁል ጊዜም ሊያሳፍር የሚገባ፣ መቼውንም ቢሆን መሆን የሌለበት ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በታሪካችን በየትኛውም ጊዜ ዓይተነው የማናውቀው ተማሪ ሌላ ተማሪን የሚገድልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤›› ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች አጋጥሞ በነበረው ግጭት አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተሳታፊ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አቶ ሲራጅ ይህን በተመለከተ በግጭቱ ወቅት በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የማኔጅመንት አባላትም ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ግጭቶች የተነሱት በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች በሚገኙና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች እንደነበር አስረድተዋል፡፡  

የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ባደረጉት ጥረት መረጋጋት እንዲፈጠርና የማስተማር ሥራው እንዲጀመር መደረጉን አቶ ሲራጅ አውስተዋል፡፡ ግጭቱን በመፍራት ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው ያልመጡ ተማሪዎች እስካሁን ድረስ እንዳሉም አክለው ገልጸዋል፡፡

በዲሲፕሊንና በአካዳሚክ ውጤታቸው የተባረሩ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ሳይለቁ ውስጥ ሆነው ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችን ሲያባብሱ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ለማጥራት በተሠራው ሥራም በኦሮሚያ ብቻ 980 ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ መልክ ተባረው መውጣት የነበረባቸው ግን ቁጭ ብለው ሁከቱንና ብጥብጡን ሲያባብሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ብቻ 41 ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገኝተዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በቀሩት ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር ሥራውን ሊያውኩ የሚችሉ ተማሪዎች መኖርና አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራ መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የፀጥታ አካላት ቶሎ ደርሰው እንዳስቆሙትና ይህ ባይሆን ኑሮ ዘግናኝ የሆነ ዕልቂት ሊከሰት ይችል እንደነበር አቶ ሲራጅ ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ከግቢ ወጥተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ከፍተኛ ሥራ ባይሠሩ ኖሮ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ዕልቂት ሊከሰት ይችል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በተቋማቱ ያለው የፀጥታ ችግር መሻሻሉን የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፣ ‹‹ይህ ማለት ግን አሁንም ወደ ግጭትና ሁከት ሊቀየር የሚችል ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቱ በተፈጠረበት ወቅት የፌዴራል የፀጥታ አካላት ገብተው ግጭቱን እንዲያስቆሙ ሁለቱም ክልሎች መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ግጭቱ የሁለቱም ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት ነበር፡፡ የሁለቱም የፀጥታ አካላት ሳይወጡ በመሀል ያለው ቦታ ላይ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ አይቻልም የሚል ግምገማ ስለነበረን፣ የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ አካላት ከድንበር አካባቢ እንዲወጡ ነው መመርያ የተሰጠው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹በእርግጥ ሲወጡ መዘግየቶች ነበሩ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሶማሌ ክልል ከ33 ወረዳዎች ፖሊሲና ልዩ ኃይሎቻቸውን እንዲያስወጡ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ከ25 ወረዳዎች ሚሊሻ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይላቸውን እንዲያስወጡ ተደርጓል፡፡ መሀል አካባቢ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በፌዴራል የፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

በተከናወነው ሥራም ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን አሁንም የግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ የሉም ማለት እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ታኅሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢ ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት እንደጠፋ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ እየተከሰተ ላለው ቀውስና ችግር ዋነኛው ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሲራጅ፣ የፀጥታ አካላት እንዲሠማሩ የተደረገው የፖለቲካ አመራሩ ጊዜ አግኝቶ መፍትሔ እስኪሰጥ ድረስ፣ ጊዜያዊ የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡   

አገሪቱ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ሚዲያዎች የነበራቸውን ሚና በመግለጫቸው በማካተት ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ ሚዲያ በአግባቡ ከተሠራበት ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፣ የመንግሥትን ጨምሮ የግል ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ባለፉት ሁለት ወራት የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ የሚያባብሱ፣ የሚያቀጣጥሉ፣ ኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ሳይሆን በተቃራኒው ሲሠሩ እንደነበር በጋራ ምክር ቤቱ መገምገሙን አስረድተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉን ሚዲያ ያካትታል ማለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ወደፊት ይህ አቅጣጫ ይታረማል የሚል እምነት እንዳላቸውም ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

የተከሰተው ችግር ሊፈታ የሚችለው የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ጠቁመው፣ የዜጎች ነፃነት ጥያቄ በገባበት ወቅት የትኛውንም ነገር ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የጦር መሣሪያዎችን በማስገባት ሁከትና ብጥብጡ እንዲቀጥል የሚያደርጉ አካላትም እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ሲገባባቸው ከነበሩ ዋናዋና መስመሮች መካከል አሶሳ፣ መተማና ቶጎ ጫሌ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት በጋራ በሠሩት ሥራም ወደ መሀል አገር ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩ 270 ክላሽኒኮቭ መሣሪያዎች፣ 200 ሽጉጦች፣ 65 ሺሕ የክላሽ ጥይቶች፣ 1,000 የመትረየስ ጥይቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ሲባልም የመሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም አዋጅ በቅርቡ እንደሚወጣ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡    

ሚኒስትሩ በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኃላ ከጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል በፌዴራልና በክልሎች የፀጥታ አካላት መካከል አለመግባባቶች አሉ ይባላልና በዚህ ዙሪያ ምላሽ ቢሰጡን የሚለው የሚገኝበት ሲሆን በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር መግባባት የለም ተብሎ የተነሳው፣ መጀመርያውኑም ዕቅዱ የወጣው በጋራ ነው፡፡ ጥቃቅን ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በመሠረታዊነት ከሁሉም ክልሎች ጋር የጋራ መግባባት ይዘን ነው የምንሠራው፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በነበረው ግጭት የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ አካላት እጃቸው አለበት የሚል ውሳኔ ነበረ፡፡ እነሱ ወጥተው የፌዴራሉ የፀጥታ አካላት እንዲቆጣጠሩት የተደረገው ካለመተማመን ሳይሆን፣ መጀመርያ በተከሰተው ሒደት ውስጥ የእነሱ እጅ ስላለበት ገለልተኛ አካል ቢገባ የተሻለ ሰላም ሊያረጋግጥ ይችላል በሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል የፀጥታ አካላት ችግሩ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የማረጋጋት ሥራ ሲሠሩ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል የሚሉ ውንጀላዎች ሲደመጡ ቢሰማም ሚኒስትሩ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹የፀጥታ አካላት በተቀመጠው አሠራርና መመርያ መሠረት ነው የሚሠሩት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም ሙሉ በሙሉ እንዳልበረደና የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በግጭቱ የሞቱ ሰዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሲራጅ፣ ‹‹የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ይኖራሉ፡፡ የምናጣራው ጉዳይ አለ፡፡ ስለዚህ አጥርተን ስንጨርስ ይፋ የምናደርገው ይሆናል፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተጠረጠሩ ዜጎችን ወደ ሕግ ከማቅረብ አኳያ በሁለቱም ክልሎች አመራሮች ዘንድ ዳተኝነት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ኅብረ ብሔራዊነትን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሲራጅ ሲያብራሩ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎች የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች የሚመስል ሠራዊት መደራጀት አለበት በሚለው የአገሪቱ ሕግ መሠረት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ሠራዊት ከመመልመል አንፃር፣ በየአካባቢው ያሉ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ሠራዊት እንዲገነባ በማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤›› ብለዋል፡፡ እንደ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ኅብረ ብሔራዊነትን ያማከለ ሌላ መሥሪያ ቤት ማግኘት አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ፣ የአማራ፣ የትግራይና የኦሮሚያ ክልሎች ከሕዝባቸው ቁጥር ጋር ሊመጣጠን የሚችል የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱን አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡ የሶማሌ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላና የሐረሪ ክልሎች ከሕዝባቸው ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የመከላከያ ሠራዊት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህን ለማስተካከልም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡  

መከላከያ ሚኒስትሩ በወቅታዊ የግብፅ ጉዳይና በኢትዮጵያ ላይ ልታሳድረው ስለምትችለው ተፅዕኖ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ከግብፅና ከሱዳን ጋር ተያይዞ ተፅዕኖ ይኖረዋል፣ አይኖረውም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ እኛ ተፅዕኖ የለውም ብለን አልደመደምንም፡፡ የተፈጠረውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልነው ነው፡፡ ምንድነው? ወዴት ነው ሊሄድ የሚችለው? ምን ዓይነት ዕድገት ነው እያመጣ ያለው? የሚለውን በቅርበት እየተከታተልነው ነው፡፡ በቅርበት እያየነው ስለሆነ ወደፊት በጋራ የምናየው ይሆናል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በታኅሳስ ወር በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው ለአባላቱና ለግብፅ ሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን አልተሳካም፡፡ በተቃራኒው የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካይሮ አቅንተው ከግብፁ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች መሪዎች በዋናነት በጋራ የጦር ኃይላቸውን ስለሚያጠናክሩበትና በቀይ ባህር ስለሚኖራቸው ወታደራዊ ሚና መነጋገራቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት ነው፡፡   

      

    

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -