የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ከደቡብና ከፌዴራል መንግሥት ብቻ የ528 ሰዎች ክስ መቋረጡን አስታወቁ፡፡ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ይህን ያስታወቁት ዛሬ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን ተከትሎ የግንባሩ አራት አባል ድርጅት ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት›› ሲባል በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱና በክስ ሒደት ላይ ያሉትም ክሳቸው እንደሚቋረጥ ገልጸው ነበር፡፡
ይኼንንም ተከትሎ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ከደቡብ ክልል 413 ክሶች ከፌዴራል ደግሞ 115 ክሶች መቋረጣቸውን ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡
ከደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ዙሪያ ይርጋ ጨፌ፣ ኮቸሬና ጌዴቦ ግጭት ላይ የተሳተፉ 316 ሰዎችና በሰገን ሕዝቦች ኮንሶ ወረዳ በነበረ ግጭት የተሳተፉ 52 ሰዎች ናቸው እንዲፈቱ የተደረገው፡፡
እንደ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ገለጻ ክስ እንዲቋረጥ የተወሰነባቸው መስፈርቶቹ የሰው ሕይወት ያላጠፉ፣ ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሱ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ በደረሰ ውድመት ተሳትፎ የሌላቸው፣ ሕገ መንግሥቱንና የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ያልተሳተፉ የሚሉ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ክሳቸው የሚቋረጥ ተከሳሾችን ለመለየት ልዩ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የመለየት ሥራውን የሠራ ሲሆን፣ ዛሬና ነገ ተሃድሶ ተሰጥቷቸው ይፈታሉ ተብሏል፡፡
ግብረ ኃይሉ ለቀጣይ ሁለት ወራት በሚሠራቸው ማጣራቶችም የሚፈቱ ሰዎች ይኖራሉ ሲሉ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡