Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ 86 ሺሕ ዜጎች የመኖሪያ ቤቶች ሊሠሩ ነው

ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ 86 ሺሕ ዜጎች የመኖሪያ ቤቶች ሊሠሩ ነው

ቀን:

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት፣ የኦሮሚያ ክልል 86 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች መኖሪያ ቤቶች ሊሠራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ የኦሮሚያ ክልል በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለ86 ሺሕ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ለመሥራትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የፌዴራል መንግሥት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በመበጀት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ክልሎችና ባለሀብቶች ባደረጉት ድጋፍም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው፣ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ምግብ ነክ ለሆኑና ምግብ ነክ ላልሆኑ የፌዴራሉ መንግሥት ወጪ ማድረጉንና ይህ ጥረት ወደፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

ዜጎችን በማቋቋም ሒደትም የሶማሌ ክልል በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በተደረገው ጥናት መሠረት ከሁሉም ወገኖች የተፈናቀሉ አካላት ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ተመልሰው መሄድ የሚፈልጉና የማይፈልጉ እንዳሉ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስትሩ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረው ግጭት በቁጥጥር ሥር መዋሉን አክለው ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ‹‹ቄሮ›› ተብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ቄሮ እየተባሉ በሚጠሩት ወጣቶች ላይ ‹‹‹ሆን ብሎ አላስፈላጊ ትርጉም በመስጠት እንዲያውም አንዳንዶች ከሽብር ቡድን ጋር እያያያዙ የሚያናፍሱት ወሬ አላስፈላጊ አጀንዳ በመሆኑ ያንን መንግሥት የሚጋራው እንዳልሆነና አጥብቆ እንደሚቃወም ነው መግለጽ የምንፈልገው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ቄሮ›› እየተባለ የሚጠራው የወጣቶች ቡድን የፖለቲካ ድርጅት እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ ወጣቶች በመሪ ድርጅቱ ውስጥ በተለያየ መንገድ የሚሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ቄሮ የሚባሉት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ የሆነ የሥራ ፈት ቡድን አድርጎ መቅረፅ ትክክለኛ አጀንዳ እንዳልሆነ እንዲታወቅ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቄሮ›› እየተባሉ የሚጠሩ ወጣቶች አገር ችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት በግንባር ቀደምትነት የሚሳተፉ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ቄሮን በተመለከተ በፌዴራል ፖሊስ ያቀረበው ማብራሪያ ስህተት የለውም፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች አዛብተው እያቀረቡት ነው፡፡ ምርመራ የሚደረገው ቄሮዎች ላይ ሳይሆን ወንጀል የሠሩ አካላት ላይ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያም በሁለቱ ክልሎች የተጠረጠሩ ዜጎችን ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩና የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ በሁለቱ ክልሎች እጃቸው አለበት ተብለው ከተጠረጠሩና የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 55 ሰዎች መካከል እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት 15 ብቻ እንደሆኑ መግለጻቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ሁለቱ ክልሎች ሲነፃፀሩም በሶማሌ ክልል የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 29 ሰዎች መካከል 17 የሚሆኑት በክልሉ መንግሥት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ፣ በተመሳሳይ በኦሮሚያ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 26 ሰዎች መካከል በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሦስት ዜጎች ብቻ መሆናቸውን አቶ ሲራጅ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ እንዲሁም በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋል ያለባቸው አካላት ከዚህ በፊት በፌዴራል ደረጃ፣ በፖሊስና በእሳቸው መገለጹን አስታውሰው፣ ‹‹እስካሁን ድረስ በኦሮሚያ በኩል ከተለዩት ውስጥ መጀመርያ 98 የሚሆኑት በቁጥጥር ሲውሉ፣ በሶማሌ ክልል ደግሞ ከ39 ሰዎች መካከል 29 ተለይተዋል፡፡ ከ29 ሰዎች መካከል በቅርቡ እንደተገለጸው 12 በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አሁንም በሁለቱም ክልሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...