Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ባንክን የተበላሸ ብድር ለማስተካከል ግብረ ኃይል ተቋቋመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የተበላሸ ብድር መጠኑ ከ25 በመቶ በላይ ሆኖ ዘልቋል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ 25.3 በመቶ የሚሆነው የተበላሸ ብድር በመሆኑ፣ ይኼንን የተበላሸ ብድር ምጣኔ ወደ ገደቡ ለመመለስ በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና የሚመራ ግብረ ኃይል አቋቋመ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከአምስት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ገደብ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር መጠን 25.3 በመቶ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች፣ እንዲሁም የሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶች በብዛት የተበላሸ ብድር ውስጥ በመግባታቸው የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከፍ ብሏል፡፡

‹‹በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን የሚመራው ግብረ ኃይል የሚያገግሙትን ፕሮጀክቶች እንዲያገግሙ በማድረግ፣ በባንኩ መወረስ ያለባቸው ላይ ሐራጅ በማውጣትና  ሌሎችንም ዕርምጃዎች በመውሰድ የተበላሸ ብድር ምጣኔው እንዲቀንስ ለማድረግ ሥራ ተጀምሯል፤›› ሲሉ አቶ ተሾመ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአጠቃላይ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ 8.6 ቢሊዮን ብር የተበላሸ ብድር ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ 3.6 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶች ተሰጥቶ የመመለሱ ጉዳይ ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ የተበላሸ ብድር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ቀሪው ብዙ የተነገረለት የቱርክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አይካ አዲስና ሌሎችም የፋብሪካ ፕሮጀክቶች የወሰዱት ሲሆን፣ የመመለሱ ጉዳይ አጠራጣሪ በመሆኑ የተበላሸ ብድር ውስጥ የገባ ነው፡፡ ይኼ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው አምስት በመቶ ገደብ በ20.3 በመቶ ልቆ 25.3 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከገጠመው የተበላሸ ብድር ምጣኔ ለመውረድ በተለይ ለአዳዲስ እርሻ ፕሮጀክቶች አዳዲስ ብድሮች መስጠቱን በማቆየት፣ ከአደጋ ቀጣና መውጣት በሚያስችል ደረጃ ላይ የሚገኙትን በማስታመምና ተጨማሪ ብድር በመስጠት ከችግር ለመውጣት ያቀደ ሲሆን፣ ማገገም የማይችሉትን ደግሞ በመውረስ የተበላሸ ብድር ምጣኔውን ለመቀነስ አቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶች በችግር በመተብተባቸው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ብድር መስጠት አቁሞ ነበር፡፡ ባንኩ ብድር መስጠት በማቆሙ በርካታ ፕሮጀክቶች ችግር ውስጥ በመግባታቸው ቅሬታ ሲያሰሙ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከብዙ ጥናትና ውይይት በኋላ ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ባንኩ ብድር መስጠት መጀመሩን ቢያስታውቅም፣ ልማት ባንክ የተከተለውን አዲስ የብድር አሰጣጥ መመርያ ተገቢ አይደለም በማለት በባለሀብቶች አማካይነት ጥናት እየቀረበ ሲተች ቆይቷል፡፡

ይኼም ቢሆን ግን ከነባሮቹ በስተቀር አዲስ ብድር መስጠት ማቆሙን ባንኩ ይፋ በማድረግ፣ ነባሮቹ የባንኩ ደንበኞች ብቻ የሚገኙበት ነባራዊ ሁኔታ እየታየ እንደሚስተናገዱ አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአቶ ጌታሁን የሚመራው ግብረ ኃይል አዘቅት ውስጥ የገቡ ተበዳሪዎች የአስተዳዳር ሥራዎች ጭምር ጣልቃ በመግባት፣ ተጨማሪ የብድር መክፈያ ጊዜ ለሚያስፈልጋቸው ጊዜ በማራዘም ከችግር ለማውጣት እንደሚሠራ፣ ለሚንገዳገዱት ደግሞ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ሥራዎችን ማከናወን መጀመሩ ታውቋል፡፡

የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሁሉም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዲስትሪክቶች በጻፉት የውስጥ ማስታወሻ፣ ደንበኞች ያጋጠማቸውን ችግሮች ገምግሞ የተለያዩ መፍትሔዎች ለምሳሌ የብድር ማራዘሚያና ተጨማሪ ብድር መጠስትን መፍትሔ ያደረጉ ዕርምጃዎች እንዲወስድ ማሳሰባቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

አቶ ተሾመ ለሪፖርተር ጨምረው እንደገለጹት፣ እነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦችም የባንኩ ትልቅ ዕቅድ አካል ናቸው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች