Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ዕቅድ የለኝም አለች

ግብፅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ዕቅድ የለኝም አለች

ቀን:

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቀጥታ በቴሌቪዥን ለግብፃውያን ባስተላለፉት መልዕክት፣ አገራቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ዕቅድ የላትም ማለታቸው ተሰማ፡፡

‹‹በቀጣናው ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ጠንቅቀን የምናውቅ በመሆኑ ግብፅ በኢትዮጵያና በሱዳን የውስጥ ጉዳይ በመግባት የአገሮችን ሉዓላዊነት አትደፍርም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግብፅ ከወንድሞቿ ጋር ወደ ጦርነት አትገባም፡፡ ምክንያቱም ሰላም አንዱ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው፤›› ማለታቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ ‹‹ከማንኛቸውም ጎረቤቶቻችን ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት ዕቅዱም ሆነ ፍላጎቱ የለንም፤›› ሲሉ በቀጥታ በተላለፈው የቴሌቪዥን ሥርጭት መናገራቸውን የዜና አውታሮች ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በናይል ወንዝ ላይ ያለንን ታሪካዊ የውኃ መጠን እንዲቀነስብን አንፈቅድም፡፡ የናይል ወንዝ ለግብፃውያን የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤›› ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ድህነትን የመቅረፍ ጉዳይ የሞትና የሽረት ጉዳይ በመሆኑ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንደማታቆም መግለጿ አይዘነጋም፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በቅርቡ ኢትዮጵያ መጥተው በነበረበት ጊዜ፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር ከሱዳን ውጪ እንዲሆን ጥያቄ ማቅረባቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ግብፅና ሱዳን በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብ ላይ መሆናቸውን አህራም ኦንላይን የተሰኘው የግብፅ ሚዲያ ሰሞኑን ያስነበበ ሲሆን፣ ግብፅ ፊቷን ወደ ኤርትራ፣ ሱዳን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ማዞሯን ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በግብፅ ካይሮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ከግብፅ አቻቸው አልሲሲ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በቀይ ባህር አካባቢ ስላለው የፖለቲካ ትኩሳትና ሁለቱ አገሮች በጋራ ስለሚኖራቸው የጦር ቀጣና መምከራቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳላኝ ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካይሮ እንደሚያቀኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር  ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ነገሪ እንደተናገሩት፣ የግብፅና የኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ በ27 ጉዳዮች ላይ ከዚህ በፊት ስምምነት እንዳላቸውና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የግብፅ ጉብኝት አዳዲስ ስምምነቶችን ለመፈራረም ሳይሆን፣ የቆዩት ስምምነቶች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በቀይ ባህር በኩል እየተፈጠረ ያለው የጂኦፖለቲካ አንድምታ የተለየ ገጽታ እየያዘና አገሮቹ ጎራ እየለዩ መምጣቸውን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከካይሮ ወደ አስመራ የተመለሱት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሰሞኑን ለአገሪቷ ቴሌቪዥን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥትን መውቀሳቸውን፣ በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር ነገሪ፣ ኢትዮጵያ ብዙ የምትሠራቸው ሥራዎች እንዳሉባትና ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ጊዜዋን እንደማታጠፋ አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...