በቅርቡ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ፣ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አቀረቡ።
በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ዘርፍ የረጅም ዓመታት ልምድ ያካበቱት አምባሳደር ወይንሸት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኅብረቱ ኮሚሽን ሙሳ ፋኪ ማሃመት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ማቅረባቸውን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደሯ ቀደም ሲል በዚህ የኃላፊነት ቦታ ሲያገለግሉ የነበሩትንና በቅርቡ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተመደቡትን አምባሳደር ወሀደ በላይ ተክተው እንዲሠሩ መመደባቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አምባሳደር ወይንሸት በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ዘርፍ (Multilateral Diplomacy) የረጅም ዓመታት ልምድ እንዳላቸው፣ ከእነዚህም መካከል ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት ሥር የቆንስላ ኃላፊና በጄኔቫ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ልዑክ ከፍተኛ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ መሆናቸው ይነገራል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ በስዊድን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።