የእኛ አዲስ አበባ እንግዳ ወዳድ
በዶሮ በእንቁላል ቶሎ እምታለምድ
እንግዳ ተቀባይ በመሆንዋ መጠን
እሷ ዘንድ ያልመጣ ያልጠጣ ውኃዋን
አይገኝም ከቶ ካራቱ ማዕዘን፡፡
ኒውዮርክ ዋሽንግተን ሮማና ሞስኩ
ስዊስና ጀርመን ሁሉም በየመልኩ
ውስጣቸውን ለሚያውቅ የደስ ደስ አላቸው
ላገሩ ተወላጅ መመኪያዎች ናቸው
የኛ አዲስ አበባም ደግሞ በበኩልዋ
እንኳንስ ለሚያውቃት ለተወላጆችዋ
ዝናዋ ያጓጓል ለሩቅ ወዳጆችዋ፡፡
እንግሊዝ ሲመጣ እያለች ዌልካም
ጉድዊል እያለች አሜሪካንም
ቦን አሪቬ እያለች ፈረንሣዩንም
ዶብሮ ናም እያለች ዩጎዝላቩንም
ቤን ቬኑቶ እያለች ኢጣሊያኑንም
ተፈደል እያለች አረቦችንም
ታስተናግዳለች ያለማስቀየም፡፡
ኧረ ምኑ ቅጡ ስንቱ ይነገራል
ደግነትዋ በዝቶ ከመጠን ገንፍሏል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ የሚገኝ እንግዳ
አያልቅም ተቆጥሮ በጽሑፍ ሰሌዳ፡፡
ካራቱ ማዕዘን ተሰብስቦ ሁሉም
ግብረ በላ ሁኗል አይቶ አልጠገባትም፡፡
ካራቱ ማዕዘን ሁሉም የሚጎርፈው
መልክና ውበቷ አየሩዋ እየጣመው
ሰብስብ አላት እንጂ መቼ የጤና ነው፡፡
እህልዋን የቀመሰ ውሀዋን የጠጣ
ምንም ቢሆን አይችል ከቤትዋ ሊወጣ
ከመዋል ከማደር ከመሰንበት ብዛት
ተጋብተው ተዋልደው ሁነዋል ባለርስት
እንግዳ ወዳድ ናት እጅግ አለመጠን
ሰለቸኝ አታውቅም ከቶ ምንም ቢሆን፡፡
- ያሬድ ገብረሚካኤል ‹‹ይምጡ በዝና አዲስ አበባ›› (1958)