Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የሦስት አሠርታት የረድዔት ጉዞ

የካናዳ ክርስቲያናዊ የሕፃናት መርጃ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች ተሠማርቶ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ከጀመረ 30 ዓመት ሆኖታል፡፡ ድርጅቱ እስካሁን ባከናወናቸውና ወደፊት ሊሠራ ባቀዳቸው እንቅስቃሴ ዙሪያ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ፈለቀ ታደለ (ዶ/ር) ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለልማት ሥራ የምትንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ለልማቱ ሥራ እንዳወጣችሁና በተለይ በትምህርት ዘርፍ የምታደርጉትን እንቅስቃሴ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ድርጅታችን የሚንቀሳቀሰው ከኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ፣ አደአና አርሲ ነገሌ ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ሶዶ ዙሪያን ጨምሮ በስድስት ልዩ ልዩ ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ፣ በአቃቂ ቃሊቲና ንፋስ ስልክ፣ ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ነው፡፡ በእነዚህም ዞኖችና ክፍላተ ከተሞች በሕፃናት እንክብካቤ በትምህርት፣ በጤናና በድህነት ቅነሳ ዙሪያ በማገልገል ላይ እንገኛለን፡፡ በተጠቀሱት ሥፍራዎች ለልማት ማከናወኛ በየዓመቱ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በ30 ዓመታት ውስጥ ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ብር ውጪ አድርገናል፡፡ በተለይ ከውልደት እስከ ሦስት ዓመት ለሚደርሱ ሕፃናት ከምናደርግላቸው እንክብካቤዎች መካከል በአካባቢው ከሚገኙ እህሎች አካል ገንቢ ምግቦችን እንዲያገኙ ማድረጋችን ይገኝበታል፡፡ ይህም ተግባራዊ የሚሆነው ለወላጆቻቸውና ለአሳዳጊዎቻቸው በምግብ አዘገጃጀት ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሥልጠና በመስጠት ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ለዚህም በምንንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች 42 የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ገንብተናል፡፡ በእነዚህም ትምህርት ቤቶች ውስጥ መዋለ ሕፃናት ወይም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን አቋቁመናል፡፡ በተጠቀሱት መዋለ ሕፃናት ውስጥ ሕፃናቱ ከጨዋታ ጋር በተያያዘ መልኩ የቋንቋና ሌሎችንም ትምህርቶች እንዲከታተሉ ከማድረግ ባሻገር፣ በሕፃናት ዕድሜ ላይም ራሳቸውን እንዴት እንደሚያውቁ፣ አካላዊ አቅማቸው ለዕድሜያቸው በሚያስፈልገው ደረጃ ላይ መድረሱን፣ ከወላጆቻቸውና አብረዋቸው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የመግባባት ክህሎታቸው፣ በራስ የመተማመን ስሜታቸው የተረጋጋ፣ ጠያቂና ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ለመፍጠርና እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናቱን የምታስተምሩበት ዘዴ ምን ይመስላል? የበለጠ ትኩረት የምትሰጡት ለየትኞቹ ሕፃናት ነው?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ይህንን ተግባር እያከናወንን ያለነው ከየክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ነው ለሕፃናቱ የተጠቀሱት ትምህርቶችና የአዕምሮ ግንባታ ሥራ የሚከናወነው በቅድሚያ የመምህራኑን ክህሎት በማሻሻል ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ባቋቋምናቸው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚረዱ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን በዚህ መልኩ ከተከናወኑት ተግባራት ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ማደራጀት፣ ሕፃናት እየተጫወቱ የሚማሩባቸውን ልዩ ልዩ የትምህርት ሞዴሎች ወይም መርጃ መሣሪያዎች ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናት ከቅድመ መደበኛ እስከ 10ኛ ክፍል እስከሚደርሱ አስፈላጊውን መሠረታዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የበለጡ ትኩረት የሚሰጠውም ወላጅ ለሞተባቸውና ለከፍተኛ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋጡ ሕፃናት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከ40 ሺሕ በላይ ሕፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሕፃናት ዩኒፎርምና ልዩ ልዩ የመማርያ መጻሕፍት ስንሰጥ ለወላጆቻቸውና ለአሳዳጊዎቻቸው የገቢ ዘዴዎችን እንፈጥራለን፡፡ በየገጠሩ ለሚገኙ ወላጆችና አሳዳጊዎች በከብት ዕርባታ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ፣ እንዲሁም ለአባቶች በመስኖ እርሻ ተሠማርተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ ያላችሁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ፈለቀ፡- በተለያዩ የገጠር ቦታዎች ከጤና ኬላ እስከ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ድረስ የማስፋፋት ሥራ እያከናወንን ለመንግሥት እንዲያስተዳድረው እናስረክባለን፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ እንዲቻል የአምቡላንስ አገልግሎት ለጤና ተቋማት በመስጠት እየተባበርን ነው፡፡ የምንሰጠውም አምቡላንስ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው የባጃጅ አምቡላንስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከገጠራማ ሥፍራ የመኪና መንገድ ድረስ በሸክም ማጓጓዝ የሚያስችል ዘመናዊ ቃሬዛ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የባጃጅ አምቡላንስ አገልግሎትን ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ፈለቀ፡- የአምቡላንስ አገልግሎት የምንሰጠው እንደ መልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለምሥራቅ ሸዋ ዞን የባጃጅ አምቡላንስ፣ በአማራ ክልል ሸዋ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ደግሞ መልክዓ ምድሩ ለባጃጅ ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ በዘመናዊ ቃሬዛ እንዲገለገሉ አድርገናል፡፡ በመጀመርያ ታካሚዎች ቃሬዛ የአስከሬን ማጓጓዣ እንጂ ሰው በሕይወት እያለ የሚጠቀምበት አይደለም በሚል ከመገልገል ወደኋላ ብለው ነበር፡፡ እኛም ይህንኑ በመገንዘብ ቃሬዛውን ዘመናዊ በማድረግ አሻሻልነው፣ በኅብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ባጃጁንም ለጤና ተቋማት በነፃ የምንሰጠው ለአምቡላንስ አገልግሎት በሚውል መልኩ አሻሽለን ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ለሚገኙ ጤና ተቋማት ስድስት ባጃጆችን ገዝተንና አሻሽለን አስረክበናል፡፡ የአምቡላንሶቹ አገልግሎት ከገበሬ ማኅበራቱ እስከ ጤና ተቋማቱ ድረስ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም አቅርቦት የእናቶችን በጤና ተቋም የመውለድ አገልግሎት አስፋፍቷል፡፡ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ሞት ለመቀነስና ቤት ውስጥ መውለድን በማስቆም ረገድም አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ አቅርቦት ተግባራዊ በመደረጉ የተነሳ እጃቸውን አጣምረው መቀመጥ ግድ ለሆነባቸው የልምድ አዋላጆች በሌላ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናት ለችግር ሲጋለጡ ኅብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ለማጠንከር የሠራችሁት ሥራ አለ?

ዶ/ር ፈለቀ፡- አዎ አለ፡፡ ይህንንም ለማድረግ በምንንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ሁሉ በኅብረተሰብ አቀፍ የልማት ማኅበራት የተደራጁ ወደ 120 ተቋማት ተመሥርተው ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ለእነዚህም ተቋማት የተለያዩ የገቢ ማስገኛዎችን በመፍጠር ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሕፃናትን እንዲረዱ የማድረግ ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ይህ ሌላ ተቋማት ሄደው ልጆቻችንን ስፖንሰር አድርጉልን የሚሉበት ሳይሆን፣ ራሳቸው ተንቀሳቅሰው ትርጉም ያለው ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቢሾፍቱና አዳማ የሚገኙ ማኅበራት አመርቂ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ ለችግር የተጋለጡ እናቶችና አባቶችን ለቀሩት ለእነዚህ ማኅበራት በልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛዎች ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ድርጅታችን ድጎማ ያደርጋል፡፡ ማኅበራቱም በዚህ ድጎማ ተጠቅመው የየራሳቸው ገቢ ማስገኛ ላይ ይሠማራሉ፡፡ ይህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ በውጭ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በቀጣይ ደግሞ አዲስ ተጋላጮች ቢመጡ ማኅበራቱ እየደጎሙ ያቋቁማቸዋል፡፡ እነዚህ ማኅበራት በሕፃናት እንክብካቤ ዙሪያ መሠረታዊ ናቸው፡፡ መንግሥት፣ የውጭና አገር በቀል የሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚሠሩት በላይ በተጨማሪ ኅብረተሰብ አቀፍ የሆኑ ተቋማት የሚሠሩት ልማት ዘላቂነት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ እነሱን ማጠንከር፣ ማደራጀትና የገቢ ማስገኛ እንዲኖራቸው ማስቻል መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የመሳሰሉትና ሌሎችም ጎጂ ልማዶች እንዲቆሙ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ደኅንነት ጥበቃ የሚል ፕሮግራም ቀርፀን ለባለድርሻ አካላት፣ ለወላጆችና ለየአካባቢው ኅብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየሰጠን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምትሠሩት ልዩ ልዩ የልማት ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የምታረጋግጡበት ግብረ መልስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ከውልደት እስከ ሦስት ዓመት ከዚያም የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በድርጅቱ ድጋፍ የተማሩ ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ዛሬ በተለያዩ ሥራዎች በመሠማራት ራሳቸውን፣ ወላጆቻቸውንና አሳዳጊዎቻቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከልማት ርቀው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በአሁኑ ጊዜ የልማትና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ለሌላ ልማት እንዳነሳሳቸው በመንግሥትም ዘንድ ትኩረት እንዲያገኙ፣ የልማት ጥያቄ እንዲያቀርቡ፣ በልማትም እንዲደጎሙ አድርጓል፡፡ የቀድሞ ሕፃናት ኮሚሽን ‹ምርጥ ምርጡን ለሕፃናት› በሚል መርህ በተለያየ ደረጃ ለሕፃናት ትኩረት የሚያደርግበት አሠራሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ወጥ የሆነ የሕፃናት ፖሊሲ የመጣው የዛሬ ዓመት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል የጤና ተቋማት ገንብታችኋል? ወይም አስፋፍታችኋል? ወጥ የሆነ የሕፃናት ብሔራዊ ፖሊሲ የወጣው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ ከመውቱ በፊት ባካሄዳችሁት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያጋጠማችሁ ችግር አለ?

ዶ/ር ፈለቀ፡- የገነባነው ወይም የሠራነው ጤና ተቋም የለም፡፡ ነገር ግን በምንንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ለእናቶችና ሕፃናት አገልግሎት የሚሰጡ 70 የጤና ተቋማት የማስፋፋትና የውስጥ ድርጅታቸውን የማሟላት ተግባር አከናውነናል፡፡ ባከናወንናቸው ሥራዎች ላይ ያጋጠመን ችግር የለም፡፡ ምክንያቱም በ1983 ዓ.ም. የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ጥበቃ ድንጋጌን ኢትዮጵያ ተቀብላ በሕገ መንግሥት ስላካተተችው ለሠራነው ሥራ ሁሉ አስተዋጽኦ አድርጎልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለብሔራዊ ሕፃናት ፖሊሲ ተግባራዊነት በምን መልኩ ነው ለመንቀሳቀስ ያሰባችሁት?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲው መውጣቱ ጥሩ ሆኖ ነገር ግን በአስፈጻሚ አካላት፣ ተጠቃሚ በሆኑ ሕፃናት፣ ወጣቶች እንዲሁም በወላጆችና በኅበረተሰቡ ክፍል ዘንድ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ ይህን ፖሊሲ ግንዛቤ ከማስጨበት በተጨማሪ ውጤት ማምጣት አለበት፡፡ የሕፃናት ተሳትፎ በልማት ውስጥ እንዲዳብር ከመሠረቱ ጀምሮ ሕፃናቱ ወጣትና ጎልማሶች እስከሚሆኑ ድረስ ያሉትን ሥራዎች የተለያዩ ተቋማት ቀጣይነት ባለው መልኩ የሥራ ሒደት፣ በጀትና የሰው ኃይል ተመድቦላቸው የሚሠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ማጠንከር እንፈልጋለን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ለችግር ለየተጋለጡ ሕፃናት የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ወጥቶ ድርጊቱ በከተማና በገጠር እየተሸጋገረ ነው፡፡ በዚህም ሕፃናቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በትምህርት በቤት ውስጥና በኅብረተሰብ ዘንድ የሕፃናቱን ዕድገት ሊያበረታቱ የሚችሉ የሕፃናት መዋያዎች፣ ክለቦችና የሕፃናቱን ክህሎት የሚያዳብር ትምህርት ተቋማት የውድድር የዕውቀት ገበያ እንዲሆኑ የሚያስችሉን ሥራ የበለጠ አጠንክረን እንሠራለን፡፡ መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ ልዩነት ከፈጠርንባቸው ሥራዎች ጋር አዋህደን በቀጣይ ለመሥራት አቅደናል፡፡ መንግሥትዊ ያልሆኑ ድርጅቶ ተፅዕኖ መፍጠርና ለውጥ ማምጣት የሚችሉት ከመንግሥት ዕቅድና ድጋፍ ጋር አብሮ መሥራት ሲቻል ነው፡፡ ይህም የሚሆነውና የተወሰነውን ነገር ስናሟላ ኅብረተሰቡ ሌላውን ነገር በተሳትፎ ሲደጉምና መንግሥት ደግሞ ያንን አሻሽሎ ሲያስፋፋ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ትስስር ባለበት ነው በጀት መመደብ የሚኖርበት ሁለተኛው ደግሞ ፈጣሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ሥራችሁን ለማከናወን ከካናዳ መንግሥና ሕዝብ የምታገኙት ድጋፍ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ፈለቀ፡- ካናዳ ውስጥ ወደ 40,000 ፈቃደኛ የሆኑ ስፖንሰሮች ወይም የወላጅ ደጋፊዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች ከሚገኘው ድጋፍ በተጨማሪ የካናዳ መንግሥት ሥራዎቻችንን ዓይቶ በያዝናቸው ሥራዎች በበለጠ እንድንሠራ እያበረታታን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከካናዳ መንግሥት ተጨማሪ የድጋፍ ምንጮችን ለማግኘትና በተጓዳኝ ደግሞ የካናዳ የግል ድርጅቶች በዚህ ልማት ላይ እንዲሳተፉ ጥረት እናደርጋለን ብለን አቅደናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች