የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዓመት በፊት ከነበረው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ጀምሮ ለስደተኞች ያላቸው አቋም አሉታዊ ነው፡፡ ‹‹ወንጀለኞች ናቸው›› የሚሏቸውን የሜክሲኮ ስደተኞች ለመቆጣጠር በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር መካከል ግንብ እንደሚያስገነቡም የተናገሩት በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ነበር፡፡ ስደተኞች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉም እንዲሁ፡፡
አልተሳካም እንጂ ፕሬዚዳንት ከሆኑም በኋላ ሽብርን ለመዋጋት የዘየዱት መላ የሰባት ሙስሊም አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማገድ ነበር፡፡ ሰለሞኑን ደግሞ ‹‹ብለዋል›› ወይም ‹‹አላሉም›› የሚለው ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ ነው ባይባልም፣ የአሜሪካንም ሆነ የአፍሪካንና የሌሎች አገሮችን ዲፕሎማቶች ያስቆጣ ንግግር ከሴኔት አባላቶቻቸው ጋር በነበራቸው የስደተኞች ጉዳይ ስብሰባ ላይ አንፀባርቀዋል ተብለዋል፡፡
ትራምፕ በስብሰባው ላይ አፍሪካውያንንና የሌሎች አገር ስደተኞችን ከቆሻሻ ሥፍራ የመጡ ሲሉ፣ የሐይቲ ስደተኞችን ደግሞ ከምድረ አሜሪካ እንዲወጡ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ቢቢሲ በስብሰባው ላይ የነበሩትን የዴሞክራቱን ሴናተር ሪቻርድ ዱርቢን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ አሜሪካ ስደተኞችን ትራምፕ ቆሻሻ ከሚሏቸው አገሮች ከምታስገባ ይልቅ ‹‹ከኖርዌይ ብናስገባስ?›› የሚል ጥያቄም ሰንዝረው ነበር፡፡
በአገረ አሜሪካም ሆነ ተሰድበዋል በተባሉ አገሮች ነቀፌታ የተሰነዘረባቸው ትራምፕ፣ አሉታዊውን ንግግር አድርገዋል በተባሉ ማግሥት፣ ‹‹ንግግሬ ጠንካራ ነበር፣ ሆኖም ይህ እኔ ያልኩት አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ምን ይመስላል?
ትራምፕ ተናግረውታል የተባለውን አንቋሻሽ ንግግር የተለያዩ አገሮችና ተቋማት ነቅፈውታል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ቢሮ የትራምፕን አተያይ፣ ‹‹አስደንጋጭና አሳፋሪ፤›› ብሎታል፡፡ በጄኔቭ የድርጅቱ ቃል አቀባይ፣ ‹‹አዝናለሁ! ለንግግሩ ዘረኛ ከማለት ባለፈ ሌላ ቃል የለኝም፤›› ብለዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ የትራምፕን ንግግር፣ ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል፤›› ብሎታል፡፡
የኅብረቱ ቃል አቀባይ ኤባ ካሎንዶ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንዳሉት፣ በርካታ አፍሪካውያን በባርነት ወደ አሜሪካ ተወስደዋል፡፡ የትራምፕ ንግግር የተሰነዘረውም አፍሪካውያን ሁሉንም ባህሪና ድርጊት ተቀብለው በሚኖሩበት አገር ነው፡፡
በቦትስዋና የአሜሪካ አምባሳደር፣ በቦትስዋና መንግሥት ተጠርተው የትራምፕ ንግግር ቦትስዋናን ይጨምር? አይጨምር? እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሲጠየቁ፣ በፓናማ የአሜሪካ አምባሳደር ደግሞ ለትራምፕ አስተዳደር ከዚህ በኋላ እንደማይሠሩ በማስታወቅ የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡
በሐይቲ የግራ ዘመም ፖለቲከኛው ሬኒ ሲቪል፣ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካውያንን ጭምር ከባርነት ለማውጣት አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ መስዋዕትነት በከፈሉት አፍሪካውያን፣ እንዲሁም በሐይቲ ሕዝብ ፊት ይቅርታ እንዲጠይቁ አሳስበዋል፡፡ የሐይቲ መንግሥትም፣ ‹‹የትራምፕ አስተያየት በሐይቲ ማኅበረሰብ ላይ ያላቸውን ዘረኛ አመለካከት ያሳያል፤›› ብሏል፡፡
ከናይጄሪያ ‹‹የአፍሪካ አገሮች ቆሻሻ መባላቸው መጥፎ ነው፡፡ የየአገሮች ዜጎችም ከዚህ ንግግር ተምረው በአገራቸው የአገራቸውን ሀብት በመጠቀም መሥራት አለባቸው፤›› ሲባል፣ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ፣ ‹‹የእኛ አገር ቆሻሻ አይደለም፡፡ ሐይቲም ሆኑ ሌሎች በስቃይ ውስጥ ያሉ አገሮችም ቆሻሻ አይደሉም፡፡ ሚስተር ትራምፕ ከአሜሪካ ፖሊሲና ከአገሮች ጋር ያላት ግንኙነት የማይፈቅደውን ንግግር መናገራቸው የሚያስቆጣ ነው፤›› ብላለች፡፡
በሐይቲ የተወለዱት የካናዳ የቀድሞዋ ገዥ ሚሼል ዦን የትራምፕን ንግግር ካወገዙት መካከል ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ጃንዋሪ 12 በሐይቲ ከስምንት ዓመት በፊት በተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ ብዙዎች ያለቁበት ቀን ነው፡፡ ከስምንት ዓመት በኋላ በዚሁ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደሃዋን አገሬን ሐይቲንና ሁሉንም የአፍሪካ ዜጎች ከቆሻሻ ሥፍራ የመጡ ማለታቸው በሰብዓውያን ላይ የተሰነዘረ ስድብ ነው፡፡ ከአሜሪካ መሪ ይህንን ንግግር መስማት የሚያስቆጣና የሚያናውፅ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የእንግሊዟን ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን ጨምሮ በርካቶች የትራምፕን ንግግር የተቃወሙት ሲሆን፣ የአሜሪካ ዴሞክራቶች ደግሞ ንግግሩ የዶናልድ ትራምፕን ዘረኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
‹‹ሚስተር ትራምፕ ሁልጊዜም ቢሆን የሌሎች አገሮች ዜጎችን እንደማይወዱ እናውቃለን፡፡ አሁን ደግሞ መቶ በመቶ ፕሬዚዳንቱ ዘረኛ ስለመሆናቸውና የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ያስቀመጠውን የሌሎችን እሴት መቀበልና ማክበር እንደማይፈልጉ አረጋግጠናል፤›› ሲሉ የኮንግረስ አባሉ ሉዊስ ጉተሬዝ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምን አሉ?
‹‹በአሜሪካ ለስደተኞች ቦታ የለም፤›› የሚሉት ትራምፕ፣ የአገሪቱ ስድስት ሴናተሮች በተገኙበት የስደተኞች ጉዳይ ስብሰባ ላይ፣ አገሮችን በመጥቀስ ከቆሻሻ አገር የመጡ ስለማለታቸው አያምኑም፡፡ ዋይት ሐውስ ትራምፕ ፀያፉን ቃል ስለመናገራቸው ባያስተባብልም፣ እሳቸው ግን በስብሰባው ላይ ጠንካራ ንግግሮችን ስለመናገራቸው እንጂ የተባለውን አጠልሺ ንግግር አልተናገርኩም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ሆኖም ለሕግ አዋቂዎችና ለጓደኞቻቸው በመደወል የእሳቸውን አስተያየት እንዲተቹላቸው ሲጠይቁ እንደነበር አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ትራምፕ በበኩላቸው፣ ‹‹የግል ሚስጥራዊ ንግግሮችን ፈቃድ ሳያገኙ የሚገልጹ መገናኛ ብዙኃን መልዕክት አዛብተው በማስተላለፋቸው የተፈጠረ ችግር ነው፤›› ሲሉ ሚዲያውን ወቅሰዋል፡፡
ትራምፕ ከብዙ አገሮች የደረሰባቸውን ነቀፌታና ‹‹ዘረኛ ነው›› መባላቸውን አስመልክቶም ‹‹እኔ ዘረኛ አይደለሁም፤›› ብለዋል፡፡
በፍሎሪዳ ዌስት ፓልም ቢች ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታም፣ ዘረኛ ነዎት? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በፍፁም! ዘረኛ አይደለሁም፡፡ እስካሁን ቃለ መጠይቅ ካደረጋችሁላቸው ሰዎች ሁሉ የመጨረሻው ዘረኛ ነኝ፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
ከትራምፕ ጋር ስብሰባ የተቀመጡ ሴናተሮች ምን አሉ?
የስደተኞች ወደ አሜሪካ የመግባት ጉዳይ የትራምፕ አጀንዳ የሆነው ዛሬ አይደለም፡፡ ከምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ጀምሮ አገራቸው የስደተኞች መናኸሪያ እንደማትሆን ይልቁንም አሜሪካውያን የሚሠሩባት፣ ዕፅ የማይዘዋወርባትና ወንጀል የማይፈጸምባት እንድትሆን እንደሚሠሩ ተናግረው ነበር፡፡
ትራምፕ እንደሚሉት፣ በአገራቸው ወንጀል የሚፈጽሙት ስደተኞች እንጂ አሜሪካውያን አይደሉም፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ለስደተኞች የከፈተችውን በር ማጥበብ አለባት፡፡ በመሆኑም በስደተኞች ጉዳይ ዙሪያ ዴሞክራቶቹንም ሆነ ሪፐብሊካኑን ለማሳመን ስብሰባ መቀመጥ፣ ከስምምነት መድረስ አለባቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት ማብቂያም የውይይታቸው አጀንዳ የነበረው፣ ‹‹የሕፃናት ስደተኞች አገባብ ላይ የተለየ መሥፈርት እንዲቀመጥ ለመምከርና ከስምምነት ለመድረስ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይም ዴሞክራቶች ከስምምነት ይደርሳሉ የሚል እምነት እንደ ሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ አገራችን ሰዎች እየጎረፉ ነው፡፡ ዴሞክራቶች በድንበር አካባቢ የደኅንነት ጥበቃ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ዕፅ ማዘዋወር እንዲቆምም አይፈልጉም፡፡ እነሱ የሚፈልጉት ለመከላከያ ኃይላችን የመደብነውን ብር ለስደተኞች ማዋል ነው፡፡ ይህን አናደርገውም፤›› ብለዋል፡፡ በንግግራቸው መሀል ደግሞ ከቆሻሻ የአፍሪካ፣ የሐይቲና የኤልሳልቫዶር አገሮች የሚመጡ ስደተኞችን ለምን እንቀበላለን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ በስብሰባ የተገኙ ሴናተሮች ደግሞ የሚያስታውሱትን እንዲህ ተናግረዋል፡፡
የጆርጂያ ሴናተር ዴቪድ ፔርዱ፣ ‹‹ትራምፕ ቃሉን አልተጠቀሙም፤›› ሲሉ የአርካንሰስ ሴናተር ቶም ኮተን ደግሞ፣ ‹‹ማለቱን አልሰማሁም፣ ከትራምፕ አቅራቢያ ነበር የተቀመጥኩት፤›› ብለዋል፡፡ በኤሊኖይስ የዴሞክራቲክ ሴናተር ዱርቢን፣ ‹‹ትራምፕ ጥላቻ የተሞላበት፣ መጥፎና ዘረኛ ቃላትን በስብሰባው ላይ ተጠቅሟል፤›› ብለዋል፡፡ ሴናተር ሊንድሴይ ግርሃም፣ ‹‹ትራምፕ ተናግሯል የተባለውና ሚዲያዎች ይዘው የወጡት አንድ ነው፤›› ሲሉ፣ የደቡብ ካሮላይና ሴናተር ቲም ስኮት ደግሞ፣ ‹‹ትራምፕ አፍሪካውያንን የሚያጠለሸውን ንግግር መናገራቸውን ግርሃም አረጋግጦልኛል፤›› ብለዋል፡፡
ትራምፕ ግን፣ ‹‹በስብሰባው ላይ ጠንካራ አስተያየቶችን ሰጥቻለሁ፡፡ ቋንቋ አጠቃቀሜም ጠንካራ ነበር፡፡ ሆኖም እንደሚወራው አላልኩም፤›› ሲሉ አስተባብለዋል፡፡