Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አካል ሲፈታ ህሊና ምን ይሁን?

ጉዟችን ተጀምሯል። እነሆ ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ። ምድር ትውልድን በትውልድ እየተካች የደከመውን በሞት ሸኝታ፣ ለጋውን እያሳደገች ፋታ አሳጥታ ታራውጠናለች። በዓል ሲያልቅ በዓል ይተካል። ሳቅ ሲፈዝ ሳቅ ይደምቃል። የሕይወት ዙር በየአቅጣጫው በድግግሞሽ ጉልበት ከልደት ወደ ጥምቀት፣ ከጥምቀት ወደ ትንሳዔ፣ ከትንሳዔ ወደ ሞት፣ ደግሞ ከሞት ወደ ልደት እያመጣ ያስጉዘናል። በዚህ ሁሉ ጥልፍልፍ ድግግሞሽ መሀል ተስፋ ዙሩን ሳይከተል ደምቆ ውሎ ያድርና ዓውድ ሞልቶ ዓውደ ዓመት ይመጣል። ተስፋ አይሞትምና። እውነት ለመሰለን ሁሉ እየደከምን በባዶ እንደ መጣን በባዶ እስክንሸኝ እንደክማለን። እርቃናችንን እንደ መጣን እርቃናችንን እንቀበራለን። በዚህ የጅማሬና የፍፃሜ ዘመን ሰው በሕይወት ዘመኑ የሚታየው እጅግ አድካሚ ሠልፍ ብቻ ነው። ገሚሱ ተርፎት ሲደርብ ገሚሱ አንዳችን ሳይኖረው፣ አንዱ ሞቆት ሲጨነቅ ያኛው ውርጭ በማጣት ሰቀቀን ጭምር እየተቀጣ ይኖራል።

እሴትን ሲሸራርፍ ነው የሰው ልጅ ዘመኑ እዚህ የደረሰው፡፡ መተሳሰብ ጠፍቶ ለራስ ብቻ የሚሮጠውን ሩጫ ከጎዳናው ላይ  ቆመው ሲያዩት ያሳቅቃል። ምንም ባልበደለ፣ ከፍጥረቱ በድህነት የሚማቅቀውን ዓይተን ሳንጨርስ፣ ያለ ፅድቁ ንዋይ ተርፎት በምቾት የሚንፈላሰሰውን ስናይ ጉድ ማለት ብቻ ነው፡፡ ማጣትና ማግኘት የጎዳናው ነባር አራጋቢዎች ናቸው። ከዚህ ሁሉ በላይ ስሜት የሚያደማ ሀቅ ቢኖር ልጅነት ሲገረጅፍ፣ አበባነት ሲጠወልግ ማየት ነው። ይኼም ቢሆን የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ማብራርያ አያጣም። ማብራርያው ሁሉ የፖለቲካ አጥር የሚታከክ ነው። የዕድሜ፣ የማጣትም ሆነ የማግኘት፣ የደስታና የሐዘን ስሜቶች ሳይቀሩ ሁሉም መነሻቸው ከዚያ ፖለቲካ አጥር ሥር ነው። አገዛዝ ሲያደቃት በኖረ አገር ጥያቄዎች ሁሉ የፖለቲካ መሆናቸው ምን ይገርማል?

 ጉዟችን ተጀምሯል። “የስሜቴ ጌታ የዕድሌ ባለቤት፣ የምወዳትን ልጅ አርግልኝ ጎረቤት…” ይላል ለዛው የማይነጥፈው መስፍን አበበ። ተጓዡ ይወዛወዛል። “ዋ ሰው መሆን?” ይላል አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት። “ምኑን አይተኸው ደግሞ በዚህ ዕድሜህ? ባይሆን በእኛ ያምራል…” ይሉታል ከጀርባችን የተሰየሙ ጎበጥ ያሉ አዛውንት። “ደግሞ ብለን ብለን በሚያምርብንና በማያምርብን እንጣላ? ኧረ በጥምቀቱ? ኧረ በዮሐንስ?” ሲላቸው ከአንገታቸው እየተወዛወዙ በዝምታ አለፉት። ይኼኔ አዝማቹን ጨርሶ መስፍን ቀጥሏል። “ወይ አንተ አሞራ ና ተላከኝ ና፣ ዋ ብሎ መለየት ባንተ ያምራልና…” ይላል። ተሳፋሪው ትዝብቱን ከአዝማቹ እኩል በ‹አቤት አቤት› ይቃኛል። መገረሙን የለመደው ፈዞ ተቀምጧል። “የዘንድሮ ነገር የተገላቢጦሽ አህያ ወደ አደን ውሻ ወደ ግጦሽ፣ የዘንድሮ ጉዴን እኔ ምን አውቃለሁ፣ እንዲሁ በሆዴ እብሰለሰላለሁ…” ሲል “መብሰልሰልስ ቢሉህ መብሰልሰል ነው እንዴ?” ይላሉ አዛውንቱ አቀንቃኙን በአካል እንደሚያናግሩ ሁሉ።

ከሚናገረው የማይናገረው በዝቷል።  አዛውንቱና ያ አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት እየቆያዩ የዘፈኑን ግጥም ተከትለው አንድ አንድ ይላሉ። ደርሶ ሆድ የሚብሰው ሰው አየኝ አላየኝ ሳይል በዓይኑ ያቀረረ እንባውን አንኳሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ሶፍት ይዛችኋል?” ብሎ አጠገቡ ያሉትን ይጠይቃል። ‘አልያዝንም’ የሚለው ሲበዛ ሲያልፍ ሲያገድም፣ ከእኔም ከእሷም ከእሱም በተነካካበት ወዛም መዳፉ ጉንጩን ይጠርጋል። ይኼን በሰያፍ ያስተዋሉት አዛውንት ቀና ሳይሉ ዘወር ሳይሉ፣ “አይዞህ ወንድ ልጅ ዋጥ ነው፤” ይላሉ። ማን ለማን፣ ለምን በምን ምክንያት እንደሚናገር፣ እንደሚያነባ፣ እንደሚስቅ ግራ ያጋባል። መንገድ የሁሉም ነውና ዛሬም በትናንትናው ጎዳና በተዳከመ፣ በተሰላቸ፣ በተበራታና ተስፋ በሰነቀ ዝብርቅርቅ የስሜት ምት ተሰባስቧል። መንገድ ሁሉን እንደ ቅኝቱና እንደ ዜማው እያገጣጠመ ደግሞም ‹እያሸዋወደ› ያስጉዘዋል። እነሆ ወደፊት!

እየተጓዝን ነው። ይኼ እረፍት የሚሳነው ጎዳና እፎይታ የከዳው መንገድ፣ እያንከለከለን ሳናስበው ከተገኘንበት አቅጣጫ አስበን የምንደርስበት ወደመሰለን መስመር ይወስደናል። ለምሳሌ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የተሰየመ አንድ ለአገሩ እንግዳ የሆነ ባይተዋር ፈረንጅ ከወያላው ጋር ይጨቃጨቃል። “ሜክሲኮ ስል እየሰማ አራት ኪሎ ይለኛል? አንደኛህን የአገርህን ታክሲ ይዘህ አትመጣም ከመጀመርያው? ምን ዓይነት ነገር ነው እባካችሁ? ፈረንጅም ደንቁሮ ማደናቆር ያውቃል ለካ?” ይላል ወያላው ተማሮ። “ተወው እስኪ። በይቅርታ እንተራረም እያልን እርስ በእርሳችን ታርቀን ሳንጨርስ ጭራሽ ከባዕዳን ልታጣላን ነው? ይልቅ እንግዳ ተቀባይነታችንን ለማንፀባረቅ መጨረሻ ላይ ያልካትን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመህ ለራሱ ንገረውማ። ቋንቋችን እየሞተም ቢሆን ቱሪዝማችን ካደገ አንድ ነገር ነው፤” ይላል ሾፌሩ እየሳቀ። “ሰላይ ሊሆን ይችላል አደራ እንዳታስበላን፣ ከአፍህ ምንም አይውጣ…” መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንዲት ፍልቅልቅ ወያላውን ታስፈራራው ጀመረች። “ከተበላንማ ቆየን፤” ጋቢና ያለው ነው ይኼን የሚለው። “ሰላይ?” አዛውንቱ ፈረንጁን አፍጥጠው እያዩ ቃሉን ደጋገሙ።

ፈረንጁ አጠገቡ ወደተቀመጠችው ተሳፋሪ ዞሮ “What’s Going On?” ይላል። ከእንግሊዝኛ ይሁን ከነገር ሽሽት ማንም የሚመልስለት ሰው ጠፋ። ያቺ ነገረኛ ፍልቅልቅ ሆነ ብላ ያስነሳቸው የጥርጣሬ ወሬ በአንዴ ታምኖ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ። “ምን ይታወቃል ትራምፕ አዲስ አበባ ሊመጡ አስበው፣ እስኪ የመንገዱንም የሰውንም አካሄድና አጠማዘዝ ቃኘው ብለው ልከውት ይሆናል፤” ሲል አንዱ፣ “ታዲያ ሠልፍ በሠልፍ እንደሆን ለምን አሁኑኑ አንድ ላይ ተባብረን አናስረዳውም? እ? ጎበዝ! በቢሮክራሲና በዴሞክራሲ ሠልፍ፣ በትራንስፖርት ዕጦት ሠልፍ፣ በመኖሪያ ቤት ዕጦት ሠልፍ፣ እንዲያው በሁሉ ነገር ሠልፍ ላይ መሆናችንን ነግረነው ይናገርልን፤” ይላል ሌላው። ፈረንጁ አንዴ ወደ ተናጋሪው አንዴ ወደ አድማጩ እያማተረ ተደናግጦ ተቀምጧል። መቼም በገዛ አገራችን ተሳቀን የሰው አገር ሰው ስናሳቅቅ የሚደርስብን ያለ አንመስልም። ወይ እንግዳ ተቀባይነት!

 ፀጉሩን በመቆጣጠር ‹ቢዚ› የሆነው ወያላችን ሒሳብ ማለት ጀምሯል። “ብንሰጥህስ ሌላ ሥራ ይዘህ ለመቀበል እንዴት ይመችሃል?” ይሉታል አንድ አዛውንት እየሳቁ። ወያላው የንግግራቸው አቅጣጫ የት ጋ ሄዶ እንዳረፈ ገብቶታል። “አይ ሰው! ስንት የሚተሳሰብበት ነገር እያለ ነቀፌታ ላይ ጊዜውን ያጠፋል። ይልቅ እኔን ትተህ ራስህን ለጥምቀተ ባህሩ አዘጋጅ” ይላል ወያላው ምፀታዊ ሳቁን እየሳቀ ወደ ሾፌሩ ሰገግ ብሎ። ሾፌራችን፣ “ለጥምቀተ ባህሩ ነው ለጥምቀተ ጠበሳው? ትንሽ ፂምህ ሲረዝም ፀረ ልማት የማትመስለው፣ ፀጉርህ ከፍ ሲል በዘመነ ዴሞክራሲ ሽሽት እንደ ጀመርክ አድርጎ የማይቆጥርህ እኮ የለም። መቼም በታሪካችን ወደ ጃንሜዳ ለመሰደድ ብሎ ፀጉሩ ላይ የተቀኘ የለም፤” ሲለው ወያላው ቀበል አድርጎ፣ “ይቅርታ እያለ ደግሞ ዴሞክራሲ ምን ይሆናል? ባይሆን ቢሮክራሲ በል። ግን እንዳልከው በገዛ ራስህ ተፈጥሮና ኑሮ ለተከዝከው የሚተክዝብህ ብዙ ነው። እውነት የፀጉር መንጨባረርን የሚጠላውን ያህል ሙስናን ቢጠላ ይኼ ሕዝብ የት በደረሰ ነበር፤” ይላል።

“ታዲያስ እንደ እሱ ያለው ቁም ነገር ላይ ሚዛን የሚደፋ ድጋፍናና ጥላቻ ቢኖረንማ ስንት ነገር አስተካክለን ነበር እስካሁን። ምን ዋጋ አለው ስንት ሥራ እያለ ሰው ሥራው ስለሰው ሆነ እንጂ። ድራማውም ፖለቲካውም ሰው በሰው…” እያለ አንድ ጎልማሳ አስተያየቱን ያዋጣል። ‘ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው’ ብሎ ወያላው ዜማውን ጩኸት አድርጎ ያንባርቅብናል። “ኧረ ተረጋጋ! ሥራ ላይ መሆንህን አትርሳ?” ይለዋል ሾፌሩ። “ምን ላድርግ ብለህ ነው? ሁሉም የራሱን ነገር እያዋደደ ሲያወራ ስለምበሽቅ እኮ ነው። ከእኔ ወንድሜ ወይም፣ ልጄ ይሻላል ይባላል እንጂ፣ ከአብራካቸው እንዳልወጣን ለምንድነው እንዲህ የሚጨፈጭፉን?” ሲል የምሩን መናደዱ ታወቀበት። “እነማን ናቸው እነሱ እንዲህ የሚያናግሩህ?” ሲለው ጎልማሳው፣ “ካለኛ አገር አስተዳዳሪ፣ ተመራጭ፣ ባለ ራዕይ፣ ለሕዝብ አሳቢ፣ ዴሞክራት የለም የሚሉን ናቸዋ!” ብሎ ወያላው ሒሳብ ለሚሰጡት ሰዎች መልስ ማዘጋጀት ነበረበት። አዛውንቱ በትዝብት ከመመልከት ሌላ ቃላት ሲቀምሩ አይታዩም። ሌላ ማንም ሰው ሊናገር የዳዳው የለም። ትዝብት ብቻ ነው ፊቱ ላይ የሚታየው። መተዛዘብ ብቻ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “የታሰረው ሁሉ በምሕረት ሲለቀቅ እኛን የሚፈቱን መቼ ይሆን?” ይላል አንዱ። “ያሰረን አለ እንዴ?” ትለዋለች ከጎኑ። “ያሰረን ሰው ባይኖርም ያሰሩን ብዙ ነገሮች ያሉ ይመስሉኛል፤” ይላታል። “ነገርን ለነገረኛው ተውለት፤” ይለዋል ከወዲያ ማዶ ወደ መጨረሻ ወንበር “ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤” ሲሉ ደግሞ ጠና ያሉት፣ “የትኛው መጽሐፍ አባ?” ይላቸዋል አንዱ ተንኳሽ። “የትኛው? ስንት መጽሐፍ ኖሯል? አንዱ ነዋ፤” አሉት። “አንዱ ስንት ነው?” ሲላቸው፣ “በተሰቀለው!” ብለው ጮሁ። ታክሲያችን በሳቅ ታጀበች። “እውነትም እናንተ ክፉኛ ታስራችኋልሳ?” ሲሉ መልሰው ወያላው፣ “በቃ እኔ ልፍታችሁ የዛሬን፤” ብሎ “መጨረሻ” አለን። ወርደን በየፊናችን ስንዳክር፣ “የታሰረን አንጀት ያላሰረ አይፈታ…” አንዱ በዜማ ቅላፄ ሲያንጎራጉር፣ ሌላው ደግሞ አንገቱን እያሰገገ፣ ‹‹ከአካል በፊት ህሊና አይሻልም?›› አለ፡፡ መጀመርያ መፍታትስ ህሊናን ነው ማለቱ ይሆን?  መልካም ጉዞ!

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት