Monday, December 4, 2023

ሕገ መንግሥቱን እንደገና መተርጎም አስፈላጊ መሆኑ የተብራራበት የውይይት መድረክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ወ/ሮ ዓለሚቱ ገብሬ ነዋሪነታቸው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በከፋ ዞን በጊንቦ ወረዳ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ሁለት ሔክታር መሬታቸውን አቶ ጫኔ ደሳለኝ ለሚባል ግለሰብ ለአምስት ዓመት እንዲጠቀምበት ያከራዩታል፡፡ አቶ ጫኔ ኪራዩ 50 ዓመት ነው በማለት በይዞታው ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማውጣት ይዞ እንደተገኘ፣ ወ/ሮ ዓለሚቱ ያቀረቡት አቤቱታ ያስረዳል፡፡ በዚህም መሬቴን ይልቀቅልኝ ሲሉ ለጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ይመሠርታሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ተጠሪ አቶ ጫኔ ደሳለኝ ለ16 ዓመት የይዞታ ደብተር ማውጣቱን በማረጋገጥ፣ የአመልካችን ክስ በይርጋ ውድቅ ማድረጉን ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ የጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔም እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ ቀርቦበት እንደነበረ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አያስቀርብም በሚል ውሳኔውን ማፅናቱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወ/ሮ ዓለሚቱ መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. አቤቱታቸውን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽፈው ያቀርባሉ፡፡ በገጠር የሚገኝ የእርሻ መሬት ይዞታቸውን ክርክርና ውሳኔ በተመለከተ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው ተብራርቷል፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ የቀረበለት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ተደረገ የተባለው የ50 ዓመት የእርሻ መሬት ኪራይ ውል በራሱ አርሶ አደሩን ከመሬት የሚያፈናቅል ተግባር እንደሆነ በመተቸት፣ ተጠሪ ለ50 ዓመት በኪራይ ወስጀዋለሁ በሚለው ይዞታ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማውጣቱ ብቻ፣ በፍርድ ቤቶቹ የተሰጠው ውሳኔ አመልካችን ከይዞታቸው የሚያፈናቅል እንደሆነና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 4 ይቃረናል በማለት የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዳቀረበ ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱም በአምስተኛው የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው መጋቢት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የጉባዔውን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበል ውሳኔ እንደሰጠ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል እንደ ማሳያ የቀረበ ነው፡፡

ይህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል ለማሳያነት የቀረበ መሆኑን፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጠቁሟል፡፡ በዚህና በሌሎች መሰል የሕገ መንግሥት ትርጉም በሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ ቅዳሜ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ ውይይቱ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ጋር በመተባበር ነው፡፡ ውይይቱ ‹‹የሕገ መንግሥት አተረጓጎም በኢትዮጵያ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን፣ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ አቶ ዳኜ መላኩ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ፣ የክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላትና ሌሎች ግለሰቦችና ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ዳኜ፣ ‹‹ልማዳዊ አሠራሮችና የባለሥልጣን ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር መቃረናቸው ተፈትሾ ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የሚደረገው ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ያለው በበኩላቸው ኅብረተሰቡ በሕገ መንግሥታዊ መብቱ ዙሪያና ስለአጣሪ ጉባዔው ምንነትና ተግባር ያለው ግንዛቤ እያደገ እንደመጣ፣ የሚቀርቡ አቤቱታዎች መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደሆነ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡ ለጉባዔው የሚቀርቡት ጥያቄዎች ይዘት ሲታይ በዋናነት ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም መብት፣ የእርሻ መሬት ክርክር፣ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ፣ የውል፣ የወንጀልና የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደሚገኙበትና እነዚህ ጥያቄዎች የሚቀርቡት በዋነኛነት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40፣ 37፣ 35፣ 34፣ 25 መሠረት አድርገው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጥያቄዎቹ የሚቀርቡት በብዛት በግለሰቦች እንደሆነና በዋነኛነትም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ በሚኖሩ ግለሰቦች መሆኑን አውስተዋል፡፡

ጉባዔው ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 2,700 መዝገቦች ቀርበው እንደነበረ፣ ከእነዚህ መካከል 45 መዝገቦች የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም መቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ32 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መተላለፉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የጉባዔውን ተግባርና ኃላፊነት አውቆና የሕገ መንግሥቱን ጽንሰ ሐሳብ ተረድቶ የሕገ መንግሥት አቤቱታዎችን በማቅረብ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉ፣ አብዛኛዎቹ የሕገ መንግሥት ጥያቄ የማያስነሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ለውይይት መነሻነት የሚያገለግሉ ሦስት ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ የመጀመርያው የውይይት መነሻ ጽሑፍ የቀረበው ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ተሳታፊና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕግ አማካሪ በነበሩት ፋሲል ናሆም (ዶ/ር) ነው፡፡ እሳቸው ያቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ 12 ገጽ ሲኖረው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን የተደረሰበት ደረጃ›› የሚል ርዕስ አለው፣ ሁለተኛውን የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደግሞ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ናቸው፡፡ ያቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ ‹‹በሕገ መንግሥት አተረጓጎም ሥርዓት የኢትዮጵያ ተሞክሮ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ነበር፡፡

ሦስተኛውን የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የቀድሞው ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ናቸው፡፡ እሳቸው ያቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ከተሰጠባቸው መካከል ለማሳያ የቀረቡ ጉዳዮች›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ነበር፡፡

ዶ/ር ፋሲል በውይይት መነሻ ጽሑፋቸው ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ አበቃላት፣ ተሰነጣጥቃ ትከፋፈላለች፣ ሕዝቦቿም ይበተናሉ ስትባል እንደነበረና በአንፃሩ አንድነቷን ጠብቃና የሕዝቦቿ ውህደትን አጠናክራ በመራመድ ላይ ትገኛለች፡፡ ‹‹በተለይ ከኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ አንፃር ያየነው እንደሆነ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻው ዘመን ኢትዮጵያ የ25 ሚሊዮን ዜጎች አገር፣ በደርግ ዘመን የ50 ሚሊዮንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ዜጎች ያሉባት አገር መሆኗ ለውጡን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ትናንት በድርቅ፣ በረሃብና በጦርነት ስትታመስ የኖረች ፊውዳል (እንዲሁም ማርክሲስት) ኢትዮጵያ ዛሬ ሰላም ተጎናጽፋ፣ አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲን ያራመደች፣ የሕዝቦቿን ልማት ለማፍጠን ደፋ ቀና እያለች ያለች አገር መሆኗ ሚስጥሩ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቷ ጋር የተያያዘ መሆኑን ግልጽ መሆን ይኖርበታል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል ባለፉት ዘመናት የነበሩት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቶች የየራሳቸውና የየግላቸው የሆነ ፍልስፍናዊ መነሻ ያላቸው እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አፄያዊ ሥርዓቱ የሚገዛው ሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ፣ ከሕዝባዊ ፍላጎት ይልቅ ከላይ የተላከ አፄያዊ ሥርዓት እንደሆነ የሚያምን ሥርዓት ነበር፡፡ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥቱ በጽሑፍ ሲቀርብም ለምንወደው ሕዝባችን ይህን ሕገ መንግሥት ሰጥተናል በሚለው አፄያዊ አገላለጽ በስጦታ መልክ የቀረበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

የዛሬው ሕገ መንግሥት በተቃራኒው ሲፀድቅ ሕዝቡ በሰፊው ተወያይቶ እንደ ተቀበለውና ሕዝባዊ ሕገ መንግሥት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች… ይህ ሕገ መንግሥት በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባዔ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. አፅድቀነዋል፤›› በሚል መነሻ የቀረበ የሉዓላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ለልማትና ለዴሞክራሲ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥት ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ እንዲሆን የሚያስገድድ ሕገ መንግሥት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግሥት ሲባል ደግሞ ከፖለቲካል ሊብራሊዝም የተለየ እንደሆነና ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ የተሠረተ ፍልስፍናና አሠራር የሚያራምድ ሕገ መንግሥት ማለት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የቡድን መብቶች በሕገ መንግሥቱ በመታወጃቸው ሕገ መንግሥቱ ለግል መብቶች ቦታ ያልሰጠ ተደርጎ የሚነሳው ትችት ከእውነታ የራቀ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ከመያዙ ባሻገር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ዲክላራሲዮን ባስቀመጠው መልኩ አንድ ሳያስቀር ልቅም አድርጎ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ መብትና ነፃነትን ሲያውጅ ገደብም እንዳስቀመጠ አስታውሰው፣ ‹‹ገደቡ የኅብረተሰቡን መብትና ነፃነት ከመጠበቁ አንፃር  የሚመጣ ሲሆን፣ አንዳንድ ተቺዎች ገደብ የለሽ አናርኪ (ሥርዓት አልበኝነት) የሚያውጅ ነው በማለት ይተቺታል›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ይህ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል የጠቀሱት ዶ/ር ፋሲል፣ ሊያወያይ የሚችለው የገደቡ መስፋትና መጥበብ እንጂ ሥርዓተ አልበኝነት በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ቦታ ሊኖረው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ግዑዝ ሳይሆን ሕይወት ያለው ኦርጋኒክ ሥርዓት እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ፋሲል ኅብረተሰቡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ አስተሳሰቡና አኗኗሩ እየተለወጠ ሲሄድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲሁ እየሰፋና እየጎለበተ መሄድ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህም ሕገ መንግሥቱን እንደገና መተርጎምን ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በ106 አጫጭር አንቀጾች የቀረበ ሕገ መንግሥት በጣም ሰፋፊና ጥልቀት ያላቸው የኅብረተሰቡን ራዕይ ለመተግበር የተነሱ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ የተሠረተ በመሆኑ፣ የፈጠራ ችሎታችንን በማዳበር ነው ሊተረጎም የሚችለው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሕገ መንግሥት ለምን ይተረጎማል? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ኅብረተሰቡ እየተለወጠ ሲሄድ መብትና ነፃነቱ ላይ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማራመዱ አስፈላጊ ስለሆነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል በምሳሌ ሲያብራሩም፣ ‹‹ዛሬ ዓይኑን አጥፍቶ ፍርድ ቤቶችን ባያስቸግርም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በአገራችን እየጎለበተ ሲሄድ፣ በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 26 ላይ የተደነገገው የግለ ሕይወት መብት ከዚህ በፊት በጨረፍታ ሲታይ ከነበረው በተለየና ጠለቅ ባለ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም የምንገደድበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምን ዓይነት ጉዳዮች ናቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚሹት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ በሦስት ከፍለው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ፣ በሕገ መንግሥት የተቋቋሙት የመንግሥት አካላት የሥልጣን ጥያቄ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊያሻው እንደሚችል አውስተዋል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በክልል ወይም በክልልና በክልል መካከል በአንድ ጉዳይ ላይ የሥልጣን ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ዳር ድንበርን ማካለል፣ ለብሔረሰብ ዕውቅና መስጠት፣ ክልልን መክፈል፣ በታክስና ግብር አጣጣል ውሳኔ መስጠትና ሌሎችን ሊያጠቃልል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ሌላው የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊያስፈልገው የሚችል ጥያቄ መሠረታዊ መብትና ነፃነትን የተመለከተ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥትን መተርጎም አስፈላጊ የሚሆንበት ጉዳይ ሊነሳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በማን ይተረጎማል? ለሚለው ጥያቄም ሕገ መንግሥቱ ራሱ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ይህን ጥያቄ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በመጀመርያ ደረጃ እያንዳንዱ ዜጋ በዜግነቱና የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት መንግሥታዊ ቢሆኑም ባይሆኑም፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ዜጋና ተቋም ሕገ መንግሥቱን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አገናዝቦና ተርጉሞ ነው ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ሊሆን የሚችለው፡፡ ይህ ማለት ሁላችንም በየቀን ተቀን ኑሮአችን የሕገ መንግሥቱ ተርጓሚዎች ነን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በሌላ በኩል ግን ሕገ መንግሥቱ ባልሆነ መንገድ ተተርጉሟል የሚል ጥያቄ ሲነሳ ጥያቄው እልባት የሚያገኘው የት ነው ለሚለው ሕገ መንግሥቱ ግልጽ መልስ ሰጥቶታል፡፡ የሕገ መንግሥቱ የመጨረሻ ትርጉም የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት ሕገ መንግሥቱ የሚተረጎመው የሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊ ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተወካዮቻቸው አማካይነት በሚሰጡት ውሳኔ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል ሕገ መንግሥቱ እንዴት ይተረጎማል? ለሚለው ጥያቄም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲተረጎም ሜካኒካል በሆነና በጠባቡ ሳይሆን የሕገ መንግሥቱን መንፈስ፣ ምንነት፣ ዓላማና ራዕይ ተግባራዊ ሊያደርግ በሚችል መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሙሉውን ሰነድ እንደ ሰነድ በመወሰድ ሊተረጎም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል በውይይት የመነሻ ጽሑፍ ማጠቃለያቸው ላይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ መስኮች ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢገኙም፣ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማለፍ የተገደደችበት የፀጥታ ችግር መፈጠሩንና አሁንም ችግሮች ያገረሹበት ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከእነ ሕጋዊ መሠረቱ ዴሞክራሲን፣ ልማትንና ሰላምን ለማጠናከርና ለማፋጠን እየተተረጎመ በሥራ ላይ እየዋለ እንደሚገኝ፣ ነገር ግን በአፋጣኝ ተጨማሪ ሕገ መንግሥታዊ ሥራዎች መከናወን እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ ቀሪ የውይይት መነሻ ጽሑፎች በአቶ ሚሊዮን አሰፋና በአቶ ደሳለኝ ወዬሳ ከቀረቡ በኋላ ጥያቄዎችና አስያየቶች ከተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል፡፡ ከተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል፣ መላው የአገሪቱ ሕዝቦች ስለሕገ መንግሥቱ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ከመወጣት አኳያ ብዙ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉባቸው ተጠቁሟል፡፡ ችግሩ መቀረፍ እንዳለበትም ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡

ሌላው የተነሳው ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ሲተረጉም በሕገ መንግሥቱ የተረቀቀ ገደብና ሥርዓት አለው ወይ? የሚል ሲሆን፣ በተሰጠው ምላሽ ቢኖርም ወደፊት ግልጽና የማያሻሙ መመርያዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ የግለሰብና የቡድን መብት አንዱ አንዱን ሳይጨፈልቅ መሄድ አለበት ለሚለው እሳቤ፣ ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ የሚፈታበት መንገድ አለ? ምናልባት ለብሔር ብሔረሰቦች መብት በማድላት በግለሰቦች መብት ላይ ጥሰት ሊከሰት አይችልም ወይ? ለሚለው ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንደተሰጠው ተብራርቷል፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ብቻ ስለሆነ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ጥያቄ ቢያነሱ መብትን ለማስከበር ጽሕፈት ቤቱ ምን ያህል ተደራሽ ነው? ለሚለው ጥያቄም ወደፊት ለማስፋትና ለሕዝቡ ተደራሽ ለመሆን እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት ሊዳብር የሚችለው በልምድ ነው በመባሉ፣ ሕገ መንግሥት በልምድ ብቻ ነው ወይ ሊዳብር የሚችለው? ይልቁንስ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተሻለ ሊሆን አይችልም ወይ? የሚለው ጥያቄ በቂ ማብራሪያ ሳይሰጠው ቀርቷል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊያስነሱ የሚችሉትን ሊያስነሱ ከማይችሉት ለመለየት የሚያስችል አሠራር አለ? በሕገ መንግሥቱ መሬት አይሸጥም ከተባለ ተፈጻሚነቱ ከመቼ እስከ መቼ መሆኑ ለምን በግልጽ አልተቀመጠም? የሚሉ ጥያቄዎች ከመድረኩ ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉትንና የማይችሉትን በተመለከተ በግልጽና በዝርዝር በሕገ መንግሥቱ መሥፈሩንና ችግሩ ግንዛቤ ከማዳበርና ከማስረፅ እጥረት የሚመነጭ መሆኑ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ሁለት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እኩል ለእኩል የሚመጡባቸው ጉዳዮች ስላሉ፣ እነዚህ በሚመጡበት ወቅት የትኛውን እናስቀድም በሚለው ላይ ግልጽ መርሆዎች የሉም የሚል ጥያቄ ከመድረኩ የቀረበ ሲሆን፣ ከኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ የትኛው መቅደም እንዳለበት በግልጽ መቀመጡን ኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡  

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል? አያስፈልጋቸውም? የሚለውን ለመወሰን መሥፈርቶች ምንድናቸው? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነስተው፣ በተወሰኑት ላይ አጫጭር ማብብራሪያ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -