ዛሬ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀትር በኃላ ለዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ቤት መለቀቃቸውን ተከትሎ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በዶክተሩ መኖሪያ አካባቢ ተገኝተው አቀባበል አደረጉላቸው። የተጠረጠሩበት ክስ በመንግሥት ተቋርጦ ከእስር ቤት የተለቀቁት ዶ/ር መረራ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በሚወስደው ዋና መንገድ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከቀትር በኃላ ገብተዋል፡፡ለዶክተር መረራ ከበርካታ ኪሎ ሜትሮች ጀምሮ እስከ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ጎዳና ወጥተው የሞቀ አባበል አድርገውላቸዋል።
መኖሪያ አካባቢያቸው ተገኝተው አቀባበል ላደረጉላቸው ደጋፊዎቻቸውም ዶ/ር መረራ በኦሮሚኛ ቋንቋ ንግግር አድርገዋል። ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከገቡ በኃላም ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች አጭር መግለጫ አድርገዋል።
በዚህ መግለጫቸውም ከእስር መለቀቃቸውን ያደነቁ ሲሆን፣ በቀጣይ ስለሚያደርጉት የፖለቲካ ትግል ከፓርቲያቸው ጋር በመመካከር እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል። ሌሎች ፖለቲከኞችም ይፈታሉ የሚል እምነታቸውንም ተናግረዋል።