Thursday, February 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ቆንጆዎቹ!›› ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ገና አልተወለዱም

ቶፊቅ ተማም

 በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኅትመት ብርሃን የሚያገኙ መጻሕፍት ቁጥር እያሻቀበ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ በይዘታቸው በከፍተኛ ደረጃ የተዋጣላቸው ጥቂት መጻሕፍትም በኅትመት ገበያው ላይ መታየት ጀምረዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆነው ዓምና በሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በረዥም ልብወለድ ዘርፍ ከታጩት አምስት መጻሕፍት አንዱ የሆነውና ብዙም ያልተወራለት ወሰብሳቤ አንዱ የነበረ ሲሆን፣ የመጽሐፉም ደራሲ ያለው አክሊሉ ነው፡፡ ደራሲው ከወሰብሳቤ በኋላ በቅርቡ አሻሮ መንጋ የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ መጽሐፉ በተለይ በዋነኛነት በአገሪቱ ያሉ ዓበይት የፖለቲካ ችግሮችን እየነቀሰ ካለፈው ስህተት እንድንማር የሚጋብዝ፣ በአገሪቱ ፖለቲካ በፊትም ይሁን አሁን ተሳትፎ ያላቸው አካላት የሄዱባቸውን አሁን እየሄዱ ያሉበትን የተሳሳተ መንገድ ይጠቁማል፡፡ ከዚህ ባለፈም በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉ እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበሩ ፓርቲዎች የነበሩባቸውን ድክመቶች እየተፈተሸ በነሱ ምክንያት በአገሪቱ  ላይ ያደረሰውን ዳፋ በግሩም ሁኔታ ይገልጻል፡፡ መጽሐፉን አስመልክቶ ሒስና ዳሰሳ ለማድረግ የንባብ ቁመናዬ የማይፈቅድ ቢሆንም፣ አንዳች የጎላ የሚሔስ ነገር የሌለው መሆኑ ይሰማኛል፡፡ መጽሐፉ በተለይ ከፓርቲዎች ጋር ተያይዞ ያነሳቸውን ወሳኝ ሐሳቦች ከራሴ ሐሳብ ጋር በማዋሃድ የግሌን ሐሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ 

ጸሐፊው የፓርቲዎች ሁኔታ ከቀደምት ዘመናት በመጀመር ሲገለጽ በተለይ ከደርግ ዘመን በመነሳት ሲሆን፣ በጊዜው የተነሱት ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የሰጡት ነገር የለም ብሎ መደምደም አዳጋች ቢሆንም ከሰጡት ይልቅ ያሳጡት ነገር እንደሚበዛ በመጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡ ይህንንም በገጽ 81 ላይ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፤ ‹‹ርቀን መሄዱን እንተወውና ከደረስንበት ከደርግ ዘመነ መንግሥት ብንነሳ ፍትሕ ጠፋ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍትሕ ትንሣኤ ተነስተናል ሲሉን አይተናል፤ የተፀነሱት ሁሉ ግን ተወልደው አላደጉም፣ የተወለዱትም ከፍትሕ ረሃብ አላላቀቁንም፤ ስሙን እንጂ ግብሩን የማያውቅ አሻሮ መንጋ እስኪሰለቸን ድረስ በስማችን ነገደ፣ በሀብት ንብረታችን ቀለደ፣ በየዋህነት አምኖ የተከተለ ዜጋ ታሰረ. . . ተሰደደ፣ ፍትሕ ከተፈቀደችበት ሰንሰለት ሳትፈታ ምሥጢሯ ሲመረመር ዓመታት ነጎዱ . . .›› ይሉናል፡፡

ጸሐፊው በተለይ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የተፈጠሩ ፓርቲዎች አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መታዘብ እንደቻለው የራሳቸው የሆነ ጠንካራ አደረጃጀት፣ ተጨባጭ የሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም ጠንካራ የፓርቲ ዲሲፕሊን አለመኖር፣ የፓርቲዎችን ሥራዎች በአግባቡ ለመደገፍ የፋይናንስ አቅርቦት ማነስ፣ ወጥ ያልሆነና ምርጫን ተገን በማድረግ ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ፣ ፋይናንስን በተመለከተ ከዳያስፖራው ላይ ጥገኛ የመሆን አባዜ እንዲሁም የራስን የገቢ ምንጭ ከመፍጠር አንፃር የሚታዩ ውስንነቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ከላይ ለአብነት የተጠቀሱ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ፓርቲዎች ወደ ተሻለ ጎዳና ከመራመድ ይልቅ አብዛኞቹ ፓርቲዎች በሁለት እግር መቆም ተስኗቸው በውስጣቸው ያለው መቆራቆዝ በየጊዜው አደባባይ እየወጣ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው ያልተቀደሰ ጋብቻ ሲያከናውኑ ይኽንም ተከትሎ በማግሥቱ ሲፋቱ፣ በእኔ ልምራ እኔ ልምራ ሲራኮቱ፣ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ ማልያ ቀይረው ሲዛውሩ፣ ከዳያስፖራው በሚለቀቀቅ ገንዘብ መስማማት ሲያቅታቸው መታዘብ ችለናል፡፡ ለአብነት ያህል እንኳ በቅርቡ የኢዴፓ ፓርቲ  ያጋጠመውን ችግር መገንዘብ የሚቻል ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ኅብረተሰቡ ከነሱ የሚጠብቀው አዲስ ነገር እጅጉን እየሳሳ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

ይህንኑ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ፓርቲዎች ያለባቸውን መሠረታዊ ችግር አስመልክቶ ጸሐፊው በገጽ 149 ላይ ይህንን አስፍሯል ‹‹. . . አንዳንዶች ለራሳቸው ፓርቲ እንኳ የማይገለጽባቸው ግብ ይዘው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ፍፁም ሥልጣኑን እንደማይለቅ እያወቁ፣ ነገር ግን በዚህ መሀል በሚፈጠር ድብልቅልቅ ሁኔታ ወያኔን ከሾሙት ምዕራባውያን አለቆች ጋር አቃቅረን ቢያንስ ለወደፊቱ የትግል መደላደል እናመቻቻለን በሚል መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲ በሚባል ቅፅል የሚረኩ ከዚህ የሚገኝ ምናምንቴ ካለ እሱን ለመቃረም የማይታክቱ አባላትም፣ ቤትም የሌላቸው ልብ አውልቆች ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ መንግሥት ከከፈተው የዘር ፖለቲካ የሚገባኝን ሳላገኝና ይኼን አጋጣሚ ተጠቅመን ለነፃነት ትግላችን የሚረዳ ግብዓት እንፍጠር በሚል በሰምና ወርቅ የተለበደ ለምድ ለብሰው የሚኳትኑ ጋዜጠኞች ሲሆኑ፣ የተረፉት ደግሞ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ተወካዮች ናቸው፤ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ አይለፍልህ የተባለ ሕዝብ ሳይለየን ዘንድሮን ሳይታክት ይዘምራል በማለት በአሁኑ ወቅት ያሉት ፓርቲዎች ያለባቸውን ክፍተት ያስቀምጣሉ፡፡››

ጸሐፊው በተወሰነ መልኩም ቢሆን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኙ ፓርቲዎች ቢኖሩም በነበረባቸው የራሳቸው ክፍተት ምክንያት ለአገር ሊያበረክቱ የነበረውን በጎ ነገር ችላ በማለት ድጋፉን ለሰጣቸው ሕዝብ የተሻለ ነገር ከማድረግ ይልቅ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በነሱ ችግር ምክንያት ለሕዝብ የማይሽር ጠባሳን ጥለው ማለፋቸውን በተለይም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሕዝቡ አምኖ የሰጣቸውን ድምፅ በተለይ በአዲስ አበባ በቅጡ መጠቀም አለመቻላቸውን አሰመልክቶ ይመስላል በገጽ 167 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡፡ 

‹‹ቅንጅት እንደ ሰደድ እሳት እየተግለበለበ ከመሀል እስከ ጠረፍ በተስፋፋበት ጊዜ ብዙዎች በተስፋ ሲናውዙ አንዳንዶች እንዳይሆኑ ታይቷቸው አምርረው ሲተክዙ ከቆዩት ወገኖች ጋር በነበር ግዙፍ ቀውስ ያስከተለ ጭንጋፍ ራዕይ፣ ሚሊየኖችን ትግልን እንደ ጣዕረ ሞት እንዲፈሩት ስንፍናን ትቶ ያለፈ ጠባሳ በጋራ ተሠልፎ በግል ተናቁሮ መለያየትን ያመለከ፣ ከንቱ ግርግር ግላዊ ጥቅም፣ ዝናና ክህደትን ከአገር ክብርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ ያዋለ የዘመን ማፈሪያ በወጣቶች ነበልባላዊ የትግል ወኔ በረዶ ከልሶ ካለ ዕድሜአቸው እንዲያረጁ ክፉ ምልክት የጠራ ስልት አልባ ድንፋታ. . .›› ሲሉ ፓርቲዎች ያገኙትን መልካም አጋጣሚ ባለመጠቀማቸው የደረሰውን ኪሳራ ይገልጻሉ፡፡

የፖለቲካ ትግል በባህሪው መንገዱ ጠመዝማዛ ድሉንም በቀላሉ ሊያሸቱት የማይችሉት መሆኑን ከግምት ሊገባ የሚገባው ሲሆን፣ ይህም ባለመሆኑና የፓርቲ አመራሮችና አባላት አርቆ አሳቢ እንዲሁም የሚፎካከሩትን ፓርቲ ጥንቅቅ አድርገው በማጥናት የተጠና እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ሳቢያ ነገራቸው ሁሉ ውል አልባ መሆኑንና ያተረፉት ነገር ቢኖር አቶ ያለው በመጽሐፋቸው በገጽ 169 ላይ እንዳሉት ‹‹. . . እንዲያው ዝና ቁፋሮ፤ እንዲያው ባዶ አተካሮ፤ እንዲያው እርስ በርስ ተጠላልፎ ሲወድቁ ለፀፀት እንጉርጉሮ፤ እንዲያው ቃሊቲ ተወርውሮ . . . ታሪክ ለመጻፍ ነበር እንዴ ግብግቡ. . .›› ሲሉ በእጅጉ በተጠና እንቅስቃሴ ፓርቲዎች ሊያልፉ ይገባቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ በአገሪቱ ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲ በመገንባት ረገድ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የተጫወተው ሚና የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን በቀላሉ መገንዘብ የሚቻል ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ገዥው ፓርቲ ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲዎች  በአገሪቱ ያብቡ ዘንድ ቀሪ የቤት ሥራውን ሊሠራ የሚገባ ሲሆን፣ ይህንን አለማድረጉም ፓርቲው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፈው የውሳኔ አቅጣጫ ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹በአገራችን የሚገነባው ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በፍላጎትና ጥቅሞች ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በድርጅትና በመንግሥት መሪነት ለ25 ዓመታት የቀጠለ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአስተሳሰብ ብዝኃነት በአግባቡ እንዲገለጽ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ እየተዳከመ መጥቷል፤›› በማለት ይብዛም ይነስ ለፓርቲዎች ድጋፍ አለማድረጉ ችግር ውስጥ እንደከተተው አምኗል፡፡ ይኽም የመጣው ኢሕአዴግ በ2007 አገራዊ ምርጫ ያስመዘገበው ‹‹መቶ በመቶ ድል›› ያመጣው መዘናጋት ይሆን?

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ መፍትሔ ያለውና አገሪቱን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚወስድ ፓርቲ ይፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችል ፓርቲ እስካሁን አለመገኘቱም ጸሐፊው በሐዘኔታ በገጽ 278 ላይ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹. . . በሩብ ምዕት ዓመት ጉዟችን የዚችን አገር መዳኛ አብጠርጥሮ አጥንቶ አማራጭ ይዤ መጣሁ የሚል በሳል ድርጅት ያለማግኘታችን ያሳዝናል፡፡ ቢፈጠር ጀብደኛ፣ ብቅ ቢል ዘረኛ፣ ቢታይ አድር ባይ መጣሁ ቢል አስመሳይ. . . ቢያቅራራ ዝና ወዳድ የሥልጣን ህልመኛ. . .›› በማለት አሁንም ቢሆን ሁነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ አለመፈጠሩን በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡  

ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት አሁን ላሉ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ የሆኑት በውጭ የሚኖሩ ወገኖችም በአገሪቱ የተሻለ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይዘረጋ ዘንድ የተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲ ይገነባ ዘንድ በአግባቡ ከመርዳት ይልቅ ለመተላለቅ፣ ለመዘራረፍ፣ ለመከዳዳትና ለመበታተን የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ገታ ማድረግ የተሻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይፈጠሩ ዘንድ አዎንታዊ ሚናቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ አገሪቱን እየመራ ያለው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለጀመራቸው በጎ ሥራዎች ምስጋና ሊቸረው ቢገባም፣ አሁን ኅብረተሰቡ ከፓርቲው ጋር ያለው ቅራኔ በጎዶሎ ተግባራት ላይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ፓርቲው ሰሞኑን እንደገለጸው ራሱን የበለጠ ለማጠንከርና የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የገባውን ቃል ሊያከብር የሚገባው ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በ1960ዎቹ መጨረሻ በጋናዊው ደራሲ አይ ኩዊ አርማህ የተጻፈውና የድኅረ ቅኝ ግዛት የጋናን ብልሹ አሠራር ተመርኩዞ የጻፈውን ‹‹The Beautiful are Not Yet Born›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) በሚል ርዕስ የጻፈውን መጽሐፍ ርዕስ በመዋስና መነሻ በማድረግ ከላይ በግርድፉ እንደተገለጸውና በአሻሮ መንጋ መጽሐፍ አቶ ያለው አክሊሉ በደንብ እንደገለጹት፣ በአገራችን ያሉትን ፓርቲዎች ከገዥው አስከ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድረስ ያሉትን ሰፊ ክፍተቶች ስንመለከት ‹‹ቆንጆዎቹ›› ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ገና አልተወለዱም ብለን በልበ ሙሉነት ለመናገር ያስችለናል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

                

 

 

  

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles