Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየልብስ ሰፊዎቹ ስኬት

የልብስ ሰፊዎቹ ስኬት

ቀን:

ቦሌ አካባቢ ከሚገኙ ግዙፍ ሕንፃዎች በአንደኛው ነው፡፡ ሕንፃው የተለያዩ ሱቆች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ፋርማሲና ሌሎችም አገልግሎት በሚሰጡ ሱቆችና ድርጅቶችን ይዟል፡፡ ቅንጡ ከሚባለው ከዚህ ሕንፃ ግርጌ ጨለማ ከዋጠው ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ጥግና ጥግ የመጋዘኖችና ልብስ ስፌት ሱቆች ይገኛሉ፡፡ መጋዘኖቹን የሚጠቀሟቸው የላይኛውን የህንፃውን ክፍል የተከራዩ ሬስቶራንቶችና መጠጥ ቤቶች ሲሆኑ፣ የስፌት ሱቆችን ደግሞ የተቀደደን የሚጠግኑ፣ የተበላሸ ስፌትን በትነው የሚያስተካክሉ ልብስ ሰፊዎች ናቸው፡፡

ደንበኛ በሚበዛበት አንደኛው ልብስ ስፌት ቤት በልብስ የተሞላ ነው፡፡ ደንበኞች በወላለቁ ወንበሮች ላይ እንደ ምንም ተቸግረው ተቀምጠዋል፡፡ በየማዳበሪያው ተሞልተው በተደረደሩ የልብስ ክምሮች ላይ የተቀመጡም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ፊታቸውን ጥለዋል፡፡ ዛሬ ነገ እየተባሉ በቀጠሮ የተመለሱት ወይዘሮ፣ ‹‹በቃ ልብሴን ስጠኝ፡፡ አትስፋው ይቅር፤›› አሉት ረዘም ላለው ወጣት፡፡፡ እሱም ዓይናቸውን ላለማየት እየጣረ ‹‹አልቋል መተኮስ ብቻ ነው የቀረው፤›› አላቸውና እስከ ጣሪያ ድረስ ወደ ወጣው የልብስ መደርደሪያ መሰላል ይዞ ተጠጋ፡፡ ወዲያው መለስ ብሎ ‹‹ተሰፍቶ አልቋል›› ካለ በኋላ ‹‹ምን ኣይነት ነበር ልብሱ?›› ሲል ሲፈራ ሲቸር ጠየቃቸው፡፡ ወይዘሮዋም ተስፋ ቆርጠው ተመናጭቀው ወጡ፡፡

ቤቱን ከሞሉት አልባሳት መካከል ከፊሎቹ ገና ምናቸውም ያልተነካ ቢሆንም፣ ወጣቱ ደንበኞቹ በላይ በላይ የሚያመጡለትን ሥራ የሚቀበለው ሳያቅማማ ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ተመለሱ እያለ ወዲያው የሚጨርሰው ሥራ መሆኑን አሳምኖ ይልካቸዋል፡፡ አንዳንዶቹን እዚያው አስቀምጧቸው ፊታቸው ላይ ሰፍቶ ይሰጣቸዋል፡፡

 ውድ ጊዜያቸውን በዋዛ እንዳስጠፋቸው የሚሰማቸው ደግሞ ዱላ ቀረሽ ቁጣ ያወርዱበታል፡፡ ሁኔታቸው ከአሁን አሁን ተያያዙ የሚል ሥጋት የሚፈጥር ቢሆንም፣ አንገቱን ደፍቶ መልስ ስለማይሰጣቸው ንዴታቸው ሲበርድላቸው ‹‹ነገ ባትጨርስ ግን›› ብለው አስጠንቅቀውት ተመልሰው ይሄዳሉ፡፡ አንድ ልብስ ለማስተካከል የሚጠይቃቸው ዋጋም በትንሹ ከ50 እስከ 600 ብር መሆኑን ታዝበናል፡፡ ሥራው ግን ከአብዛኞቹ የተሻለ ነውና ብዙዎች ፈልገውት ይሄዳሉ፡፡

ልብስ ከሱቅ ከመግዛት ይልቅ በልካቸው አሰፍተው መልበስ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁነኛ ባለሙያ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ያገኙ ከመሰላቸው ደግሞ ደንበኝነታቸው ለዓመታት ይቆያል፡፡ እንዲያም ሆኖ የልባቸውን የሚያደርስ ሥራ ላያጋጥማቸው ይችላል፡፡ለዚህም ንትርክ ሊበዛና እንደገና ተፈተው የሚሠሩ ልብሶች ሊበዙ ይችላሉ፡፡ የተገኘው ቦታ ሄዶ ማሰፋት ብዙም አልተለመደም፡፡ ጥሩ ለመልበስ ሁነኛ ሰፊዎችን ሰው በሰው ማፈላለግ ይጠይቃል፡፡ የረዘመ ሱሪን ለማሳጠር ሳይቀር የሚታወቅ ሰው የሚያፈላልጉ ብዙ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ ጠጋኞቹ ወጥ ልብስ ሰፍተው በብዛት የሚያስረክቡ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ እንደ 22 ያሉ በልብስ ሱቆች የተጨናነቁ አካባቢዎች ደግሞ የዩኒፎርም ማምረቻና መሸጫ እየሆኑ ነው፡፡ ከቦሌ 17 ጤና ጣቢያ መገንጠያ ጀምሮ እስከ ጎላጎል ድረስ ብቻ በግራና በቀኝ የተደረደሩ የዩኒፎርም መሸጫ ሱቆች ብዙ ናቸው፡፡ ከአካባቢው ዩኒፎርም መሸጫ ሱቆች መገኛ እየሆነ በመምጣቱም  ሌላ ቦታ የነበራቸውን ሱቅ ዘግተው 22 የሚከራዩ አሉ፡፡

ከእነዚህ ሱቆች መካከል የስ ጋርመንት አንዱ ነው፡፡ የስ ጋርመንት 22 አካባቢ ከተከፈተ ዓመት ሆኖታል፡፡ የድርጅቱ ባለቤት የ27 ዓመቱ ብርሃን ዓለሙ እንደሚለው፣ ከዚህ ቀደም ይሠራ የነበረው ሳሪስ አካባቢ ነው፡፡ ወደ 22 መዘዋወሩን የመረጠው ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ 22 ዩኒፎርምም ሆነ አልባሳት መሸጫ እየሆነ በመምጣቱ የተሻለ ገበያ ለማግኘት እንደሆነ ይናገራል፡፡

 ለሙያው ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው ብርሃን፣ ከአሥር ዓመቱ ጀምሮ በወላጆቹ ቤት በነበረ የስፌት ማሽን ለመሥራት ይሞክር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በነበረው አንድ የስፌት ማሽን የተቀደደን የመጠገን፣ የሰፋና የረዘመውን ደግሞ በልክ የማስተካከል ሥራ ሲሠራ በቀን እስከ 100 ብር ድረስ ያገኝ እንደነበር ይናገራል፡፡

‹‹ሥራው አድካሚና አሰልቺ ነው››  የሚለው ብርሃን፣ ወደ ሌላ ንግድየመግባት ፍላጎት እንደነበረው ይናገራል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሙያ ልዩ ፍቅር ስለነበረው ወስኖ ከመውጣቱ በፊት ለራሱ አንድ ዕድል ሰጠ፡፡ 100 ሺሕ ብር መነሻ ገንዘብ ይዞ 22 አካባቢ የዩኒፎርም አልባሳት መስራት ጀመረ፡፡ ውጤቱም አመርቂ ነበርና በውሳኔው ተደሰተ፡፡ በአሁኑ ወቅት ስምንት ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽኖች ማፍራት፣ ለ15 ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ካፒታሉ ከ400 ሺሕ ብር በላይ እንደደረሰ ይገልጻል፡፡

ደንበኞቹም የተለያዩ ሆቴሎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ፋብሪካዎችና ሌሎችም ዩኒፎርም የሚጠቀሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሥራውን የሚያገኘው በጨረታ ሲሆን፣ በአንድ ልብስ እስከ 20 ብር ትርፍ እንደሚይዝና ከብዛት እንደሚያተርፍ ይናገራል፡፡ አንድ ልብስ የሚሸጥበት ዋጋ እንደ ጨርቁ የጥራት ደረጃ የተለያየ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሞች እስከ 1,000 ብር ይሸጣሉ፡፡    

‹‹በመጀመርያ መገናኛ አካባቢ ነበር የምሠራው፡፡ መገናኛ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የአልባሳት መሸጫዎች ሃያ ሁለት ስለሆኑ ነው ወደ 22 የተዘዋወርኩት፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም፤›› የሚለው ደግሞ የሐበሻ ጋርመንት ባለቤት አቶ አብርሃም አሰፋ ነው፡፡ እንደ ብርሃኑ ሁሉ ከሙያው ጋር የተዋወቀው በልጅነቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ ‹‹እንጀራዬ ይሆናል›› የሚል ግምት ግን አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ወደ ቀለም ትምህርት ያደላ ነበር፡፡

የመጀመርያ ሥራውም በተማረበት የኮምፒውተር ሳይንስ ሙያ፣ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግን የያዘውን የሥራ መስክ ወደ ጎን ብሎ ወደ ልብስ ስፌት ሙያው መመለስን ወሰነ፡፡ የነበረውን መሠረታዊ የልብስ ስፌት ክህሎት አንድ ዕርምጃ ወደፊት ሊያስኬድለት የሚችል የሙያ ሥልጠናም ተከታተለ፡፡ እናም ከምንም ተነስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ካፒታል ማፍራት ወደቻለበት የልጅነት ሙያው ተመለሰ፡፡

ሥራውን ከጀመረ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በ22 ሁለተኛ ሱቁንም ከፍቷል፡፡ የሆስፒታል፣ የፋብሪካ፣ የጥበቃ፣ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሞችና ሌሎች ዩኒፎርም የሚያስፈልጋቸውን የሥራ መስኮች ዩኒፎርም ተጫርቶ ያዘጋጃል፡፡ ተባራሪ ሥራዎችንም የሚሠራ ሲሆን፣ አብዛኛውን በማምረቻና በመኖሪያ ቤቱ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ ‹‹1,000 ልብስ የሁለት ቀን ሥራ ነው፤›› የሚለው አብርሃም፤ ቋሚ ሠራተኞች ባይኖሩትም ሥራ በተገኘ ቁጥርና በሠሩት መጠን እያሰበ የሚከፍላቸው ሠራተኞች ቀጥሮ እንደሚያሠራ ይናገራል፡፡ አንዳንድ ሥራዎችንም አቅሙ ካላቸው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለም ገልጿል፡፡

ሥራው ለበርካቶች የሥራ ዕድልና የተሻለ የገቢ አማራጭ ቢሆንም፣ የመሥሪያ ቦታ ከማግኘት ጀምሮ የተለያዩ ማነቆዎች ያሉበት መሆኑን በሥራው የተሠማሩ አስተያየት ይሠጣሉ፡፡ ተፈላጊውን ጥሬ ዕቃ ማለትም ጨርቅ፣ የጨርቁ ዓይነትና የቀለም ዓይነት፣ እንደ ቁልፍ ያሉ የማጠናቀቂያ ግብዓቶችን በበቂ ለማግኘት እንደሚቸገሩ በየስ ጋርመንት ተቀጣሪ የሆኑት አቶ አቤል ሙሴ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ሌላም የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለዘርፉ ዕድገት ሌላው እንቅፋት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አስፈላጊው ጥሬ ዕቃ በበቂ ቢሟላም ስፌቱ የተጠናቀቀና ደረጃውን የጠበቀ ካልሆነ ከደንበኛ ጋር የሚያጋጭ ይሆናል፡፡ በዩኒፎርም ጋርመንት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እንደ አቶ አቤል ያሉ በአማካይ በቀን ከ100 እስከ 500 የሚሆኑ ልብሶችን የሚሰፉ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ልብስ ከ10 እስከ 20 ብር ድረስ እንደሚታሰብላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...