Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይኼኔ ነው መሸሽ!

ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ በቀደም የሠፈራችን ወጣቶች ‹‹ሲቲ ይበላል፣ የለም ዩናይትድ…›› ብለው ብር ለማስያዝ ገና ሳይነጋ ቤቴ ድረስ መጡ። አምላክ ሲወዳችሁ ገና ፊታችሁን ሳትታጠቡ መንቀሳቀሻ አበል አምጥቶ እጃችሁ ላይ ቁጭ ያደርጋል። ‹‹መቼ ነው የምሰጣችሁ? ስላቸው፣ ‹‹ገና በሰኔ የእንግሊዝ ፕሪሚየም ሊግ ሲያልቅ ነው፤›› አለኝ ተወካያቸው። እኔም፣ ‹‹እግዜር ይስጥልኝ፤›› ብዬ አምስት ሺሕ ብሬን ቆጥሬ ተቀበልኩ። ሰው ቀላል ልማታዊ ሆኗል እንዴ? ይኼ የመታደስና አምራች ዜጋ የመሆን ሥልጠና ውጤት ብቻ እንዳይሆን። ዝም ብዬ ስጠረጥር ግን እሱ ይመስለኛል። በየአቅጣጫው እጅግ በጣም አምራች ዜጎች በዝተዋል። የዛሬ ሳምንት ከሰዓት በኋላ የሆንኩትን አልነገርኳችሁም። ጠዋት ጠዋት እያገኛችሁኝ ነዋ ምን ይደረግ?

ከሰዓት በኋላ ሠርግ ነበረብኝ፡፡ ከማንጠግቦሽ ጋር ወደ ሠርጉ ቤት አመራን። እኔ የማውቀው ሙሽሪትን ነው። ባልየው ገና ከአሜሪካ መምጣቱ ነው አሉ። እንዲያውም እንደ ትናንት ነው የገባው ሲሉም ሰምቻለሁ። እና አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እሺ አንበርብር?›› ብሎ ጨዋታ ሲጀምረኝ፣ ‹‹ለመሆኑ መቼ ተዋውቀው ነው? ቆይተዋል?›› አልኩት። ‹‹እንዴ አታውቅም እንዴ?›› አለኝ። ድንግጥ አልኩ። ምን ሳትኩ ብዬ ነዋ። ዘንድሮ እኮ ምን እንደሚስታችሁና ምንን እንደምትስቱ እኮ አታውቁም። ‹‹ምኑን ነው ያላወቅኩት?›› ስለው፣ ‹‹የምር መስሎሃል እንዴ? ለፕሮሰስ እኮ ነው የሚጋቡት። ‘ፌክ’ እኮ ነው፤›› ሲለኝ የት ልግባ?  ደግሞ ስሰማ የሠርግ ዝግጅቱ ዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር ፈሶበታል አሉ። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ዓይነት አምራችና ልማታዊ ዜጋ እንዲፈጠር ትፈልጋላችሁ? ንገሩኛ!

የማትነግሩኝ ከሆነ ደግሞ እኔ የምጨምርላችሁ ብዙ አለ። ‘አለ ገና አለ ገና’ አለ ዘፋኙ። ‹‹ግን ለምን ይሆን ጉዳችን እንዲህ የበዛው? ቀላል ተዝረከረክን እንዴ?›› ስለው የባሻዬ ልጅ ምን እንደሚለኝ ታውቃላችሁ? ምንም። ፀጥ ይላል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ራሱ መልስ ያጥረው ጀምሯል። ቃል ይጠፋበታል። ቃል ካሳጠረው ነገር አንዱ ምን መሰላችሁ? ‘ቀኝህ የሚሰጠውን ግራህ አይየው’ ስለሚል ነግሬያችሁ አላውቅም ነበር። ዛሬ ግን ግድ ይለኛልና ልንገራችሁ። እኔና ማንጠግቦሽ እንደ አቅሚቲ በውጭ የምንረዳው ልጅ አለን። ገና ከሕፃንነቱ አንስቶ የትምህርቱን ወጪ እየሸፈንን ያሳደግነው ልጃችን ነው። እና አሁን ኮሌጅ ይማራል። ሰው እያደገ ሲሄድ እንደምታውቁት ፍላጎቱ እየጨመረ ይሄዳል።

ገንዘብ መቀበል እንዳይለምድ ሠርቶ ማግኘት የሚችልበትን መንገድ ብናመቻች ብለን ስናስብ፣ ማንጠግቦሽ አንድ ሐሳብ መጣላት። የመጣላት ሐሳብ ስሙን ሳትጠቅስ በሶሻል ሚዲያ እዚሁ መዲና ውስጥ ሥራ ሊሰጡትና ሊያግዙት የሚችሉ ሰዎች ካሉ ብላ ጥሪ አቀረበች። ልብ አድርጉ። ሰላሳ ደቂቃ ሳይሞላ መልስ መጣላት። ሰውዬው ትልቅ ካፒታል እንዳለውና ታዳጊ ተማሪዎችን ማገዝ ሥራው እንደሆነ አጫወታት። አድራሻውን ወሰደ። ልጃችንን አገኘው፣ ጋበዘው አፅናናው። ከዚያስ አትሉም? ጠፋ! ጠፋ! ጠፋ! የባሻዬ ልጅ ነገሩን ከጅምሩ እስከ አስቂኝ ማጠቃለያው ይከታተል ስለነበር አንገቱን የደፋውና ቃላት ያጠረው በዚህ ምክንያት ነበር። እያደር  ሰው ማነሱና መጥፋቱ የታይታና የእኔነት ዝላይ መብዛቱ፣ በተለይ ለባሻዬ ‘ሆድ ይፍጀው’ ተብሎ የሚተው እንጂ የሚወራ አይደለም። እና እኔ ምለው እንዲህ ‘እየተፎጋገርን’ አይደለም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ መሠለፍ ይቅርና ፕላኔት ከሚቀይሩት ጎራ አንሠለፍም ነው የምትሉኝ?  

ታዲያላችሁ ሰሞኑን አንድ ቪላ አሻሻጬ ነበር። ገዢዎቹ ቤቱን ገብተውበት ሰንብተው ምሳ ጠሩኝ። በጥምቀትና በገና መሀል መቀላወጤ ለራሴ ገርሞኝ ተንሰፍስፌ እውጣለሁ። እየተበላ የመጀመሪያ ልጃቸው አዲሱ ቤቱ ውስጥ ቴሌቪዥኑ ላይ ተሰክቶ ኳስ ያያል። ‹‹ሲቲና ማንቼ ናቸው?›› ስለው፣ ‹‹ሊቨርፑልና ሲቲ። እኔ ሲቲ ነኝ፤›› አለኝ። ‹‹ማን እየመራ ነው?›› ስለው፣ ‹‹እኔ›› አለኝ። ሁለት ጊዜ ግራ ገባኝ። ትኩር ብዬ ሳያቸው ለካ ‘ማንቼዎቹም አርሴዎቹም’ አሻንጉሊት ናቸው። ነገሩ ጌም እንደሆነ ገባኝ። ‹‹ኧረ አንተ ልጅ በቃህ ዜና እንስማበት?›› ስትለው እናቱ፣ ‹‹አንዴ ጠብቁኝ ይኼን ጨዋታ ካላሸነፍኩ እባረራለሁ፤›› አላት። ‹‹ማን ነው የሚያባርርህ?›› ስለው፣ ‹‹የአርሴናል ቦርድ ነዋ። አሠልጣኛቸው እኔ ሆኛለሁ፤›› ሲለኝ አልቻልኩም ሳቄ አመለጠኝ። ነገሩም ዘመኑም ገረመኝ። ወይ ቴክኖሎጂ እያልኩ ሳስብ ምናለበት ሕይወትም እንደዚህ የ‘ሲሙሌሽን’ ጌም የዝውውር መስኮት ቢኖራት ብዬ ተመኘሁ። አስባችሁታል? በዕውን አልገፋ ያላችሁን በ‘ሲሙሌሽን’ ስታዘዋውሩት?

እኔ ለምሳሌ የማዘዋውረውን ላስቆጥረችሁ። አንደኛ ከእኛ በላይ አዋቂ ላሳር እያሉ የአየር ሰዓቱን የሚያጣብቡ ጥራዝ ነጠቆችን ወደ ቦታቸው አዘዋውራለሁ። ያውም በነፃ ዝውውር። ሁለተኛ አድማጭ መሆን ሲገባቸው እኛን አዳምጡን የሚሉትን ‘ኦቨር ቤንች’ አደርጋቸውና በሦስተኛ ደረጃ ሰማይ ዳመነ፣ ገና መጣ፣ ጥምቀት ደረሰ እያሉ በመሠረታዊ የምግብ ፍላጎቶች ላይ ያለከልካይና ያለመካሪ ዘካሪ እንዳሻቸው ዋጋ የሚያንሩትን ጫማ አሰቅላቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ህልም ነው። ታዲያ ሕፃን አዋቂው ወዶ መሰላችሁ ዓለም ስንት ሥራ በሚሠራበት የቴክኖሎጂ ውጤት ‘ጌም’ ሲቀጠቅጥ ውሎ የሚያድረው? ኑሮ ክራሽ ሲያደርግባችሁ መቆጣጣር ካልቻላችሁ ‘ካንዲ ክራሽ’ አስጭኑ እሺ!

የሆነው ሆነና ማምሻም ዕድሜ ነውና የሸቃቀልኳትን ቆንጥጨ ይዤ ከፊሉን ለማንጠግቦሽ የበዓል ወጪ እንዲሆን አስቤ፣ ከፊሉን ወደ ‘አካውንቴ’ ወርውሬ ወደ ሠፈር አዘገምኩ። ስደርስ ድብልቅልቅ ጠበቀኝ። በሐሳቤ ብዙ ነገር ይመላለሳል። ማን ዓይን በዓይን ተከድቶ ይሆን? የማን ዶሮ በረረ? (የዘንድሮ ዶሮ ሲያበር እንጂ ሲበር ይታያችሁ) እላለሁ። እህ ስል የአንድ ወዳጄ ታናሽ ወንድም ራሱን ሰቅሎ በገዛ ፈቃዱ ከዚህ ዓለም መሰናበቱን ሰማሁ። ደግሞ በቅርብ አውቀዋለሁ። የአርጋጅ አናጓጁ፣ ‹‹ምናለ በዓሉን በሰላም ቢውል?›› ሲልም እሰማለሁ።

‹‹አሁን እስኪ ቀኑን መዋል ያቃተውን ሰው በዓል ዋል ዋል ብሎ ነገር’ ብዬ ሳስብ ብሸቀት ይይዘኝ ይጀምራል። እንባና ትዝብት በህልውናዬ ሰርጥ እሰጥ አገባ ገጥመው መንፈሴ ደቀቀ። ባሻዬ ገና ያኔ ከቤት መውጣታቸው ነው። “የት ይደርሳል የተባለው ገና መንገዱን ሳይጀምር እንዲህ ሩብ መንገድ ላይ ሲታጠፍ፣ መንገዱን የጨረሱት ምን ይሉት ይሆን?›› ስል የባሻዬ ልጅ ሰማኝ። ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለሁ ነዋ፤›› ብሎ ተኮሳትሮ መለሰለኝ። የምይዝ የምጨብጠው ሲጠፋኝ ማንን ማፅናናት ማንን ማረጋጋት እንዳለበኝ ግራ ሲገባኝ የባሻዬን ልጅ ጎትቼ ይዤው ጠፋሁ። እንዲህ ያለውን የኑሮ ከንቱነት መበየን ካልቻሉ መሸሽም ጥበብ ነዋ!

በሉ እንሰነባበት። ባሻዬ፣ እኔ፣ ማንጠግቦሽና የባሻዬ ልጅ ሆነን ጥምቀተ ባህሩን ለማክበር ጎዳና ወጥተናል። ነጭ ለባሹን መቁጠር ቀርቶ ላስበውም ስላቃተኝ መንገዱ ላይ ወተት ተደፍቶ እንዳየች ድመት ዓይኔን በልጥጬ በመገረም እመለከት ነበር። ባሻዬና የባሻዬ ልጅ ተጠቃቅሰው ማንጠግቦሽን አካታው ‹‹ምነው ብርቅ ሆነብህ?›› ብለው ነገር ጀመሩኝ። ያልሰማሁ መስዬ ከመንገድ መንገድ ከግራ ቀኝ እየተሯሯጡ ታቦቱን የሚያጅቡ ወጣቶችን አያለሁ። የሰው ርብርብና ትብብር አንድነትና ህብር ቀለም ሳይ ብርሃናማ ሆኜ የኖርኩ አልመስልም። ባሻዬ ልጃቸውና ማንጠግቦሽ ‹‹ምን ሆኗል ሰውዬው?›› እያሉ ሲንሾካሾኩ እሰማለሁ። ‹‹አንተን እኮ የማናግረው ልጅ አንበርብር። ምን አይተህ ነው እንዲህ ቀልብህ የተገፈፈው?›› አሉኝ ባሻዬ። ‹‹ምን የማላየው ነገር አለ ባሻዬ። አይገርምም? እዩት እስኪ?›› አልኳቸው። ‹‹እኮ ምኑን ነው የማያው?›› ግራ ገባቸው። ‹‹ማንም ሳያግደን ማንም ሳያሰማራን እንዲህ አምረን ወጥተን በዓሉን በአጀብ፣ በመከባበር፣ በመቀባበል የምናከብር ሰዎች መሆናችን አይደንቅም?›› አልኳቸው። ‹‹አይ ይኼን ልጅ የሆነ ነገር ሳያቀምሱት አልቀሩም፤›› አሉ ባሻዬ ንግግሬ ስላልጣማቸው።

‹‹ድሮስ እንዴት ኖሯል የኖርነው? ንገረኛ? ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ብለው ቆጣ አሉ። ‹‹አይቆጡ ባሻዬ። እኔን እኮ እየገረመኝ ያለው እንዲህ ያለው ኅብራዊነት የጥምቀት፣ የገና፣ ወይም የእንቁጣጣሽ ወይ የረመዳን ጊዜ ብቻ መሆኑ እኮ ነው። ዛሬ ሲያልፍ ተመልሰን የትናንትና ሐሜትና ጎሰኝነታችን ይቀጥላል። እከሌ እኮ እንዲህ ያገኘው የእነንትና ወገን ስለሆነ ነው መባባላችንን ላንተው፣ የእናንተ ጊዜ የእኛ ጊዜ እያልን ጊዜ ለመግዛት ማድፈጣችን ላይቀር፣ በዚህ መንታ መንገድ ላይ ለቆመች አገራችን ልክ ጥምቀተ ባህሩ በአዲስ ሐሳብና መፍትሔ አጥምቀን ልንገላግላት ሲያሻን ለመልክ ብቻ መኖራችን አይገርምም? የሆታ ድምቀትና ወኔ አይሰለችም? ሳይገባን ማመን ከዚያ መፋረስ አይሰለቸንም? ካልገረመስ እስከ መቼ ነው የማይገርመን? ካልሰለቸስ እስከ መቼ ነው የማይሰለቸን?›› ስላቸው ማንጠግቦሽ ተቀብላ፣ ‹‹አቦ አትነጅሰን። በቀሚሳችን እንበጣጠስበት፤›› አለችኝ። ‹‹መልክ ብቻ!›› አለች አሉ ድምቢጥ ድመትን አይታ። ይኼኔ ነው መሸሽ አትሉም ታዲያ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት