በወርኃ ጥር የኢትዮጵያ አደባባዮች በበዓላት ደምቀው ይታዩበታል ከሚያሰኘው አንዱ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት መሆኑ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፍት ‹‹የአፍሪካው ኤጲፋኒያ›› (African Epiphany) በመባል በልዩ ልዩ ድርሳኖች የሚታወቀው የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በይፋ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከርሟል፡፡
ዓመታዊው ክብረ በዓል በአገሪቱና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን (ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) በምትገኝበት የዓለም ክፍሎች የዋዜማውን ከተራ ጨምሮ ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በማግስቱም የቃና ዘገሊላ በዓልም እንዲሁ ተከብሯል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ለፓርላማው ባቀረበው የመንፈቅ ዓመቱ የአፈጻጸም ሪፖርቱ የሦስት ቀናት በዓል የሆነውን በዓለ ጥምቀትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅቱ እየተገባደደ መሆኑንና እስከ ኅዳር መገባደጃ ድረስ 70 በመቶ መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የባህል አንትሮፖሊጂስቱ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራው ከሞላ ጎደል መጠናቀቁና አንዳንድ ቀሪ ነገሮች ቢኖሩም ሁሉም ነገር በሁለት ወር ውስጥ ተጠናቆ በዩኔስኮ ቀነ ገደብ መሠረት ከመጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት ማመልከቻው ይላካል፡፡
ዋዜማውን ከተራ (ጥር 10) እና ማግስቱን (ጥር 12) ቃና ዘገሊላን ይዞ በዓለ ጥምቀት በልዩ ድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነውና ጎንደር ከተመሠረተችበት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በልዩ አገባብ እየተከበረ ያለውን ሒደት ለመሰነድ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ቡድን እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም በአቶ ገዛኸኝ መሪነት ቀሪ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ ከባለሥልጣኑ ጋር ተባብረው እየሠሩ መሆኑን የሚገልጹት በመንበረ ፓትርያርክ የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት የሙዚየም መምሪያ ኃላፊው መልአከ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ ናቸው፡፡ አንዱ መሥፈርት የይመዝገብልን ፊርማ በመሆኑ የምዕመናንና የካህናት ፊርማ ከነማመልከቻው ተያይዞ መቅረቡን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
መልአከ ሰላም ሰሎሞን የክብረ በዓሉን አንድምታ እንዲህ ይገልጹታል፡- ‹‹ብዙ በዓላት አሉን፤ ጥምቀት የሚለይበት ከሃይማኖታዊ መሠረትነቱ ባሻገር የአደባባይ በዓል መሆኑ ነው፡፡ ሕፃንና አዋቂ፣ ሽማግሌም ደካማውና ብርቱው የሚታይበት ሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫዎቹም ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ፣ የኢትዮጵያዊነት ወዝ ያላቸው፣ ጠቀሜታቸው የጎላና እኛነታችንን የሚገልጹ ብዙ ባህሎች አሉበት፡፡ በሃይማኖታዊነቱ የጌታ መጠመቅ ለአኛ አርአያ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ መጠመቁን የምናይበት ትልቁ በዓላችን ነው፡፡ ለክርስትና ሕይወት የጥምቀት በዓል መሠረታዊ በዓል ነው፡፡ ››
የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ከበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው የሚሉት አቶ ወርቁ፤ መረጃዎች የማሰባሰብና ለመዝጋቢ አካላት ባህሉን የማሳየት ብሎም የማሳመን ሥራዎች በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል ከፍተኛ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ፡፡
በጎንደር ከሚሰነደው አከባበር በተጨማሪ በጠቅላይ ቤተክህነትና በሌሎችም አማካይነት የአኩስምን የንግሥት ሳባ መዋኛ ማይ ሹም፤ የላስታ ላሊበላን፣ የአዲስ አበባ ጃንሜዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በየባሕረ ጥምቀቱ የሚኖረውን ሥርዓት ስነዳ ይከናወናል፡፡ የማስመረጫ ሰነዱ ለዩኔስኮ የሚላክ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ለ2019 በዕጩነት ለማቅረብ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰነዱን አሟልቶ መላክ ይጠበቃል፡፡
በዓለ ጥምቀቱ ሲገለጽ
በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡
ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።
ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።
ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ (ለዘንድሮ እስከ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም.) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ‹‹አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ›› እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል። ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል።
ያኔ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ዱላ ወደ ረዥም ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት (ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ አዘንብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው… የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ ሠርክ መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሁለት ዓመት ወዲህ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላሊበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1,500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የአገሪቱ ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዓሉ መቼ ይመዘገብ ይሆን?
ኢትዮጵያ እስካሁን ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቿን (የመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት) በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ የገዳ ሥርዓት በኅዳር 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተደረገው የዩኔስኮ ጉባኤ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ዓምና ስምንት የአፍሪካ አገሮች አልጀሪያ፣ ማላዊ፣ ቦትስዋና፣ አይቮሪኮስት፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ሞሪሸስ ለዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሶቻቸው እንዲመዘገቡላቸው ቢያመለክቱም ዕድሉን ያገኙት ማላዊ፣ ኒስማ (Nsima, culinary tradition of Malawi) በሚባለው ባህላዊ ምግቧ፤ ሞሪሸስ ሙዚቃ፣ ዳንኪራና ዝማሬን ባካተተው ‹‹ሰጋ ታምቡር›› (Sega Tambour) በሚባለው ባህላዊ ሙዚቃዋ፤ አይቮሪኮስት ዛዑሊ በሚባለው የጉሮ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንኪራ (Zaouli, popular music and dance of the Guro communities in Côte d’Ivoire) አማካይነት መሆኑን የዩኔስኮ ድረ ገጽ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ለመወዳደር ያለፏትን ተከታታይ ዓመታት ዳግም እንዳያልፋት የምታደርገው የጥምቀት በዓልን እንዲመዘገብ የሚያስችለውን የማስመዝገቢያ ሰነዷን አዘጋጅታ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. (ማርች 31 ቀን 2018) በፓሪስ ሰዓት አቆጣጠር እስከ እኩለ ሌሊት ስትልክ ብቻ ነው፡፡