Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚኒስትሮች ምክር ቤት 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች ለተፈናቀሉ ማቋቋሚያ በጀት ተይዟል

ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተግባራዊ የሚደረግ 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰብስቦ የ2010 በጀት 320 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዚህ ግዙፍ በጀት ላይ 14 ቢሊዮን ብር እንዲጨመር በመወሰኑ፣ የበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ በ334 ቢሊዮን ብር የሚከናወኑ ሥራዎች ይኖሩታል፡፡

ምክር ቤቱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ያፀደቀው በጀት በአገሪቱ እየደረሱ ላሉ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ በአዳዲሶቹ አሥራ አንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ለማሳደግ፣ ለዲጂታል ቴሌቪዥን ሽግግር ፕሮጀክትና ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ቀሪ ክፍያዎችን ለመሸፈን የሚውል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የበጀት እጥረት ለገጠማቸው ባለበጀት መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ድጎማ እንደሚውል ታውቋል፡፡

ሆኖም ጥቅምት አጋማሽ ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችን ጠርቶ ባነጋገረበት ወቅት፣ በዚህ ዓመት ለየትኛውም መሥሪያ ቤት ምንም ዓይነት ተጨማሪ በጀት እንደማይመደብ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ሚኒስትሮችን፣ ዋና ዳይሬክተሮችን፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችንና ሌሎች ኃላፊዎችን መሥሪያ ቤታቸው ጠርተው ያነጋገሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ የ2010 በጀትን የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በቁጠባ እንዲጠቀሙና እንዲያሸጋሽጉ በመጠየቅ ተጨማሪ በጀት እንደማይመደብላቸው ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ በሚደረገው በጀት 81.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለመደበኛ ወጪዎች፣ 114.7 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች፣ 117.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለክልሎች በድጎማ የሚሰጥ ሲሆን፣ ሰባት ቢሊዮን ብር ደግሞ ለዘላቂ ልማት የሚውል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ተጨማሪ በጀቱ ሊፀድቅ የቻለው በዓመቱ መጀመርያ ላይ በፀደቀው በጀት ያልተካተቱ ጉዳዮች በመነሳታቸው ነው፡፡ ለአብነትም በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው ሰፊ ቦታ የሚሸፍነው ድርቅ ተጎጂዎች አሁንም መኖራቸውና የተወሰኑ አካባቢዎችም በተያዘው በጀት ዓመትም መረዳት ስለሚኖርባቸው ነው ተብሏል፡፡

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚያስፈልገው የ2010/2011 በጀት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም፣ በዚህ ዓመት በድጋሚ የማቋቋም ሥራ ይከናወናል ተብሎ ታቅዷል፡፡

‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካፀደቀው በጀት ውስጥ ለእነዚህ ሥራዎች የሚውል በጀት ተይዟል፤›› ሲሉ አቶ ምትኩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ በሙሉ ድምፅ ተወስኖ ተልኳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች