Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበኢትዮጵያ የሚታየውን የሠራተኞች ብዝበዛ ያጣጣለው የዓለም ሠራተኞች ኮንፌደሬሽን ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ እንዲደነገግ...

  በኢትዮጵያ የሚታየውን የሠራተኞች ብዝበዛ ያጣጣለው የዓለም ሠራተኞች ኮንፌደሬሽን ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ እንዲደነገግ ጠየቀ

  ቀን:

  • ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት አገሮች ዕጩ ተደርገዋል

  ለሁለት ቀናት በተካሄደውና የአፍሪካ ሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲደነገግላቸው የጠየቀውን ፎረም ያዘጋጀው የዓለም ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የሠራተኞች ብዝበዛን ከመንቀፉም በላይ አገሪቱ ለሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚደነግግ ሥርዓት እንድትዘረጋ ጠየቀ፡፡

  የዓለም የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሻረን ባሮው ከረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የአፍሪካ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ፎረም ሲከፍቱ እንደጠየቁት፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የወደፊቷ የጨርቃ ጨርቅ ማዕከል ስለመሆኗ ቢዘገብም፣ በሠራተኞች ረገድ ግን ብዝበዛ የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች በምሳሌ አሳይተዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ከሚገኙ ፋብሪካዎች አንዱን በጎበኙበት ወቅት ያጋጠማቸውን ሲገልጹም፣ የሦስት ልጆች እናት የሆነችውንና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ማሽን ኦፕሬተር በመሆን ለዓመታት እየሠራች የምትገኘውን ወይዘሮ የሺ የተባለች ሠራተኛ ታሪክ ምሳሌ አቅርበዋል፡፡ ወ/ሮ የሺና መሰሎቿ ኑሮን ለማሸነፍ ቢጣጣሩም በሚከፈላቸው ‹‹ለኑሮ የማይበቃ ዝቅተኛ ደወመዝ›› ሳቢያ ህልውናቸው ሥጋት ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ጸሐፊዋ ባሮው፣ መንግሥት የእነ የሺ ዓይነት ሠራተኞችን ሕይወት ለማሻሻል ዝቅተኛውን የደመወዝ ዕርከን መደንገግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  እንደ ባሮው ማብራሪያ የወ/ሮ ወርኃዊ ደመወዝ 600 ብር ወይም ከ20 ዶላር በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጉልበት ብዝበዛ የሚፈረጅ የክፍያ መጠን በመሆኑ የሠራተኞች ብዝበዛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እንደ የሺ ያሉ ሠራተኞች በበቂ ደረጃ ሊያኖራቸው የሚችል ደመወዝ የማግኘት መብት እንዳላቸው ሲገልጹም፣ ጥቅሙ ለአገሮች መሠረታዊ ህልውና ጭምር እንደሆነ በማስገንዘብ ነበር፡፡

  ዋና ጸሐፊዋ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ስለ ዝቅተኛ የደመወዝ ዕርከን አስፈላጊነት መነጋገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች አስፋላጊነት ላይ በተወያዩበት ጊዜም፣ የውጭ ኩባንያዎች የሠራተኞችን መሠረታዊ መብት ማክበርና መጠበቅ እንደሚገባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው የተናገሩት ባሮው፣ ለሠራተኞችና ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊው የመብት ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ መነጋገራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

  ዝቅተኛው የደመወዝ ዕርከን በኢትዮጵያ መቼ ይደነገጋል ለሚለው ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን አቶ ካሳሁን ፎሎ በሰጡት ምላሽ፣ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንና መንግሥትም በሠራተኛና አሠሪ ፖሊሲው ውስጥ ያካተተው አጀንዳ በመሆኑ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ መቼ ለሚለው ግን ጊዜው አይታወቅም ብለዋል፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂም ይኼው ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸዋል፡፡

  ሚኒስትሩ እንዳሉት መንግሥት ጥናት ጀምሯል፡፡ ተጠንቶና ውይይት ተደርጎበት፣ ‹‹ለይስሙላ ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ›› ድርድር ከተደረገ በኃላ ዝቅተኛው የሠራተኞች የደመወዝ ዕርከን እንደሚደነገግ ከመግለጻቸው በቀር፣ መቼ ሕጉ ሊወጣ እንደሚችል አልገለጹም፡፡ አቶ አብዱልፈታህ በፎረሙ ወቅት እንዳስጠነቀቁት፣ የሠራተኞች ማኅበራት የሚወከሉበት ዓለም አቀፍ ተቋም ዝቅተኛ የደመወዝ ዕርከን እንዲወሰን የሚያደርገው ዘመቻ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ የአገሮቹን ነባራዊ እውነታዎችና የኩባንያዎችን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ 

  የዓለም ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን የአፍሪካ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ክዋሲ አዱ-አማንክዋህ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ዝቅተኛ የሠራተኞችን የደመወዝ ዕርከን ለመደንገግ በሚደረገው ዘመቻ አስኳል እንዲሆኑ ስምንት አገሮች መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጋና፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋልና ዛምቢያ መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ሚስተር አዱ-አማክዋህ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ስምንቱ አገሮች የተመረጡት ንቁ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የተደራጁ የሠራተኛ ማኅበራት ስላሏቸው ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚታየው ተሞክሮ ወደ ሌሎቹም የአፍሪካ አገሮች እንደሚስፋፋና በመላው አፍሪካ ዝቅተኛ የደመወዝ ዕርከን እንዲበጅ ለማድረግ ስምንቱ አገሮች መነሻ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

  አቶ ካሳሁን ደግሞ፣ በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘው ሠራተኞችን የማደራጀት እንቅስቃሴ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም እየገባ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን በማኅበራት ማደራጀት እንደተጀመረ፣ ለዚህም የደቡብ ኮሪያው ሺንትስ ኩባንያ ቀዳሚው በመሆን ከ4,000 ሠራተኞች ጋር የኅብረት ስምምት እንደፈረመ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

  ኩባንያው በቅርቡ የተደረገውን የምንዛሪ ለውጥ መነሻ በማድረግ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ በመነሻ ደመወዙ ላይ የ200 ብር ጭማሪ ማድረጉ በአብነት እንደሚጠቀስ አስታውሰዋል፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚገኙ 42 ያህል ኩባንያዎች ውስጥ የተቀጠሩ ሠራተኞችን ጨምሮ፣ በሌሎችም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሠራተኞችን የማደራጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡

  በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች የአሠሪዎች ማኅበር ከመመሥረታቸውም በተጨማሪ፣ የሠራተኞችን መነሻ ደመወዝ ውስጥ ለውስጥ በመነጋገር እየወሰኑ እንደሚገኙ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ኩባንያዎችም በወር ከ600 እስከ 650 ብር እንደሚከፍሉ ታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን መንግሥት በቅርቡ ያረቀቀውን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በመቃወም ቅሬታውን ማሰማቱና ሥራ የማቆም አድማ እስከማድረግ የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሠራኞችን መሠረታዊ መብት ይጋፋል ያለውን ረቂቅ ሕግ የተቃወመው ኮንፌደሬሽኑ፣ በርካታ የመደራደሪያ ነጥቦችን በማቅረብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ በመሄድ መነጋገሩ አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከታቸው እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያሉትን ጨምሮ በርካታ ሚኒስቴሮች የሚሳተፉበት ድርድር ከኮንፌደሬሽኑ ጋር እየተካሄደ ነው፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img