Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከፀረ ሽብር ሕጉ ውስጥ ስድስት አንቀጾች እንዲሰረዙ የቀረበለትን ጥያቄ ኢሕአዴግ ውደቅ አደረገ

ከፀረ ሽብር ሕጉ ውስጥ ስድስት አንቀጾች እንዲሰረዙ የቀረበለትን ጥያቄ ኢሕአዴግ ውደቅ አደረገ

ቀን:

በአገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፀረ ሽብር ሕጉ ስድስት አንቀጾች እንዲሰረዙ የቀረበለትን ጥያቄ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገው፡፡

ኢሕአዴግን ጨምሮ አሥራ ስድስት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ሐሙስ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአራተኛ ጊዜ ድርድር ያደረጉ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ከፀረ ሽብር ሕጉ ሊሰረዙ ይገባል ብለው ያቀረቧቸውን ስድስት አንቀጾች ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ በመወከል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለተደራዳሪ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሰረዙ፣ እንዲሻሻሉና ተጨማሪ እንዲካተቱ ብለው ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይሰረዙ ተብለው የቀረቡት የፀረ ሽብር አዋጁ አካል የሆኑት ስድስት አንቀጾች ሕገ መንግሥቱን የጣሱ፣ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር የሚጋጩና የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ያጠበቡ አለመሆናቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ ያቀረቡት የመጀመርያው ጉዳይ በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ ዛቻን በተመለከተ የተቀመጠውን ጉዳይ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ዛቻን በተመለከተ መውጣት አለበት የተባለው እንዲወጣ አናምንም፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛው እንዲሰረዝ የተጠየቀው የፀረ ሽብር ጉዳይ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1ሀ ላይ የተቀመጠው ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት የሚለው ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው ግን፣ ‹‹ሐሰተኛ ሰነድ ያዘጋጀ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ እንደሆነ የሚለው የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች ሥልጣናቸውን ያላግባብ እንዲጠቀሙ ስለሚደረግ ይሰረዝ ነው፡፡ ሽብርን መርዳት ወንጀል ተደርጎ መወሰድ ስላለበት አይሰረዝም፤›› ብለዋል፡፡

ተደራዳሪ ፓርቲዎች በሦስተኛ ደረጃ እንዲሰረዝ የጠየቁት የፀረ ሽብር አንቀጽ 14 ላይ ያለውን ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው ይህንንም ኢሕአዴግ እንደማይቀበል አስረድተዋል፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬዲዮ፣ የኢንተርኔት፣ የፖስታና የመሳሰሉትን ግንኙነቶች መጥለፍ በተመለከተ የሚደነግግ በመሆኑ ተደራዳሪ ፓርቲዎች፣ ‹‹መጠለፍ የለባቸውም፡፡ ስለዚህ በዚህ አግባብ አንቀጹ መሰረዝ አለበት፤›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተሰጠው ምላሽም፣ እነዚህ መብቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 2 መከበር እንዳለባቸው የተደነገገ እንደሆነና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 14 መሠረት ጠለፋ የሚደረገው ፍርድ ቤት ሲፈቅድ እንደሆነና ይህ ደግሞ የዜጎችን መብት የሚጥስ እንዳልሆነ በኢሕአዴግ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በአራተኛ ደረጃ እንዲሰረዝ የተጠየቀው በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 21 ላይ ያለውና ከናሙና ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ናሙና ሲባል የእጅ ጽሑፍ፣ የጣት አሻራ፣ ፎቶግራፍ፣ ድምፅ ወይም የሰውነት ፍሳሽ ያካተተ ስለሆነ  የዜጎች ደኅንነት በሁለት መንገድ መጠበቅ አለበት፡፡ የመጀመርያው በምርመራ ወቅት የአካል ደኅንነት መጠበቅና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በውሳኔ አሰጣጥ ወይም ቅጣት አጣጣል ላይ ነው፡፡ ሰው በአካሉ ሊቀጣ ይችላል፡፡ እጁ ይቆረጥ፣ እግሩ ይቆረጥ ተብሎ ሊወሰንበት ግን አይችልም፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡

ፖሊስ ይህን ሲያደርግ ግን ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀም እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ተመጣጣኝ ኃይል የሚለው አሻሚ ስለሆነ ይህን በተመለከተ በቀጣይ ሕግ እናወጣለን፤›› ብለዋል፡፡

ከፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ የተጠየቀው አምስተኛው ጉዳይ አንቀጽ 23 ላይ ያለው የማስረጃ አቀራረብ የተመለከተ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ጠለፋ ይፈቀዳል ካልን በጠለፋው የተገኘው ሪፖርት ማስረጃ ሆኖ ለፍርድ ቤቶች ይቀርባል፡፡ ስለዚህ ይህ ሊሰረዝ አይችልም፡፡ ብቸኛ መረጃና ማስረጃ ግን ሊሆን አይችልም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ስድስተኛውና የመጨረሻው እንዲሰረዝ የተጠየቀው የፀረ ሽብር ሕግ አንቀጽ 25 ላይ መሰየምን በተመለከተ የተቀመጠ ነው፡፡ ተደራዳሪ ፓርቲዎች መሰየም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 እና ከዳኝነት ሥልጣን ጋር ይጋፋል የሚል መከራከሪያ አንስተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹በፍጹም አይጋፋም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቱ ሽብርተኛ ነው? አይደለም? ብሎ የመፈረጅ ሥልጣን በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ተሞክሮዎች እንዳሉ አቶ ጌታቸው አስታውሰው፣ በኢትዮጵያ ግን የሕዝብ ውክልና ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጣጣማል ብለዋል፡፡

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፀረ ሽብር ሕጉ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል አራቱ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሕአዴግን ጠይቀው ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው መሻሻል አለባቸው ተብለው በተጠየቁት ጉዳዮች ላይም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ እንዲሻሻሉ የጠየቁት የመጀመርያው ጉዳይ በፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‘ማንኛውም ሰው…’ ብሎ የሚጀምረው፣ ‘ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ወይም ተቋም’ ይባል የሚል ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው አባባሉ ችግር እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው የሚለው ድርጅት ወይም ተቋም የሚሉትን ያካትት የሚለው አባባል ችግር የለበትም፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 12 ላይ ሰው የሚለውን ትርጉም ያስቀምጣል፡፡ ሰው የሚለውን ሲተረጉም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ ሰው ማለት የተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅትንም፣ ተቋምንም ያካትታል ማለት ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ ብዙም ተቃውሞ የለንም፤›› ብለዋል፡፡

እንዲሻሻል የተጠየቀው ሁለተኛው ጉዳይ ያለ ፍርድ ቤት መያዝን የተመለከተ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ወይም እየፈጸመ ያለ ስለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠርን ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፖሊስ መያዝ ይችላል ይላል፡፡ ነገር ግን በንዑስ አንቀጽ 2 የተያዘው ሰው በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ብሎ ነው የሚያስቀምጠው፤›› ካሉ በኋላ፣ አደጋ እያደረሰ ያለ ሰው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የለም በማለት ወንጀል እየሠራ የሚተውበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ይህን ጉዳይ በሁለት መልክ መመልከት እንደሚቻል አቶ ጌታቸው አክለው፣ የመጀመርያው ተጠርጣሪው ያን ያህል አደጋ ለመጣል የማያስችልበት ሁኔታ ካለ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አውጥቶ የሚያዝበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ባሻገር ግን ሽብርተኝነት ለመፈጸም ሲዘጋጅ ወይም እየፈጸመ ያለ ግን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልያዝኩምና መጠበቅ አለብኝ ማለት ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ በሁለት መንገድ የሚታይበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ እንዲሻሻል የተጠየቀው ሦስተኛው ጉዳይ በአዋጁ አንቀጽ 6 ላይ የሰፈረው ቅጣትን የተመለከተ ሲሆን አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአዋጁ ከአንቀጽ 3 እስከ 12 የተቀመጡት የቅጣት ጉዳዮች ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንፃር ከነፍስ ግድያ በስተቀር ከአሥር ዓመት የበለጠ ቅጣት ሊያርፍባቸው አይገባም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በቀል፣ መዘጋጀትና ማሴርን በተመለከተ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ካየን የሞት ቅጣት ድረስ ያስቀጣል፡፡ ነገር ግን እኛ እዚህ ላይ ከቅጣት አንፃር የተወሰኑ መደራደሮች ልናደርግ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

ተደራዳሪ ፓርቲዎች ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው አንቀጽ 22 ላይ የተቀመጠው መረጃ የመስጠት ግዴታን የተመለከተ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ይህ የሚያሳየው የመተባበር ግዴታን መጣስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ የሕዝብን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ወንጀልን የሚያበረታታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያንን ለመከላከል በሚደረገው ግዴታ አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ አንቀጽ 22 መሻሻል የሌለበት መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ተደራዳሪ ፓርቲዎች በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ቢካተቱ ብለው ያነሷቸው ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በሕገ መንግሥቱ እንደተካተቱና ምላሽ እንደተሰጠባቸው አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡

እንዲሰረዙ፣ እንዲሻሻሉና ተጨማሪ እንዲካተቱ ተብለው በቀረቡ ጉዳዮች ላይ አቶ ጌታቸው ምላሽ ከሰጡ በኋላ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ድርድር እስከሆነ ድረስ ሰጥቶ መቀበል እንዳለ የጠቆሙት ተደራዳሪ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ምንም ነገር የመስጠት ፍላጎት እንደሌለው ትችት ሰንዝረዋል፡፡ ኢሕአዴግም ፀረ ሽብር ሕጉን በተመለከተ ከዚህ ዙር በላይ መደራደር እንደማይፈልግና ወደ ቀጣዩ አጀንዳ መግባት ተገቢ እንደሆነ ሐሳብ አቅርቦ፣ በአብዛኛዎቹ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ኢሕአዴግ የፀረ ሽብር ሕጉን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ የፓርቲዎች አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ፣ ለሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ ተይዞ የዕለቱ ድርድር ተጠናቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...